ከፍተኛ ሊግ ሀ | ባህርዳር በግስጋሴው ሲቀጥል አአ ሽንፈት አስተናግዷል 

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በ17ኛ ሳምንት ቅዳሜ በተደረገ ጨዋታ ከተቋረጠበት ሲቀጥል እሁድ ሶስት ጨዋታዎች በምድብ ሀ ተካሂደዋል። ባህርዳር መሪነቱን ሲያጠናክር አዲስ አበባ ከተማ ከመሪው ባህርዳር የራቀበትን ሽንፈት አስተናግዷል።

ኦሜድላ ሜዳ ላይ አአ ከተማን ያስተናገደው የካ 1-0 አሸንፏል። በመጀመርያው ዙር ከነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በሁለተኛው ዙር መሻሻል እያሳዩ የሚገኙት የካዎች ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን በራሳቸው የሜዳ ክፍል አመዝነው ሲጫወቱ አአ ከተማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ጎል ለማስቆጠር ተጭነው ቢጫወቱም በዘጠና ደቂቃ ውስጥ ግን ግልፅ የጎል አጋጣሚ መፍጠር የቻሉት በሁለት አጋጣሚ ነበር። 20ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዮ ሚሊዮን ሰለሞን በጥሩ ሁኔታ ወደ ሳጥኑ ውስጥ ሰብሮ በመግባት ለአጥቂው ፍቃዱ አለሙ አቀብሎት ወደ ጎል ቢመታውም ተከላካዮቹ ተረባርበው ያወጡት ፤ በሌላ በኩል 27ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ አለሙ ከግብ ጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ አገባው ሲባል ወደ ኋላ ለሙሀጅር መኪ አቀብሎት ሙሀጅር ወደ ጎል ሲመታው ተከላካዮች እንደምነም ተደርበው ያወጡት ኳስ ተጠቃሽ ነበር። ከዚህ ወጭ ኳሱን ተቆጣጥሮ ከመያዝ ውጭ የየካዎችን ጠንካራ መከላከልን ሰብሮ በመግባት የጎል አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም ። በአንፃሩ የካዎች በተደራጀው የመከላከል ስራቸው ውስጥ 31ኛው ደቂቃ ላይ ንጉሴ ጌታሁን ከርቀት መቶ ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በቀላሉ የያዘበት እና 34ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ንጉሴ ጌታሁን መቶት የግቡ አግዳሚ ገጭቶ የወጣው ነበር ።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጉልበት እና የሀይል አጨዋወት በዝቶ የታየበት ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ አአ ከተማዎች የተከላካይ ቁጥራቸውን በመቀነስ የአጥቂ ቁጥራቸውን ጨምረው ይልቁንም አዲስ ፈራሚያቸውን ናይጄራዊ አጥቂ ላኪ ሳኒን ቀይረው በማስገባት በሙሉ ኃይላቸው ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም አንድም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የረባ ግልፅ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ። ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለማግኘት የገቡ የሚመስሉት የካዎች የመከላከል አደረጃጀታቸው እና የመጫወት ፍላጎታቸው አስገራሚ ነበር ። በመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው በተለይ የመስመር አጥቂው ዮናስ ሰለሞን በግሉ የሚያደርገው ጥረት ለአአ ከተማ ተከላካዮች ፈተና ነበር ። ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲገመት 90ኛው ደቂቃ ላይ በዕለቱ በየካዎች በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዮናስ ሰለሞን በቀኝ መስመር ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ ሳጥኑ በመግባት መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አሸናፊ ምትኩ ወደ ጎልነት ቀይሮ የማታ የማታ ለየካ ድል አስጨብጧል። ጎሉ ሲቆጠር የየካ ተጨዋቾች እና የቡድን አባላት ደስታቸውን በአስገራሚ ሁኔታ ሲገልፁ የአአ ከተማ ተጨዋቾችን ድንጋጤ ውስጥ የከተተች ሆና አልፋለች። ጨዋታውም በየካ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ መድን በሜዳው ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ መድኖች ጨዋታው በተጀመረ በ9ኛው ደቂቃ በሚካኤል በየነ ግብ መሪ መሆን ችለዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ አልፎ አልፎ ከሚታዩ የግብ ሙከራዎች ውጪ በመሃል ሜዳ የረጋ እንቅስቃሴ ሲታይበት መድን በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል መድረስ ቢችልም መጨረሻው የሜዳ ክፍል ያል በሚሰሩ የውሳኔ ስህተቶች ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል፡፡ 
በሁለተኛው አጋማሽ ፌደራል ፖሊስ በጨዋታው እንቅስቃሴ የተሻሉ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ሁለት ያለቀላቸውን እድሎች አምክነዋል፡፡ የፖሊሱ ግብ ጠባቂ ሳሙኤል ነጋሽ በአደጋ ክልሉ ውስጥ ዮናታን ብርሃኔ የሞከረውን ኳስ ሲያወጣ መድን 2-0 ማድረግ የምትችል እድል ሚካኤል ሳይጠቀምበት ሲቀር ፖሊሶች በበኩላቸው በደጀኔ አምዴ የሞሩት ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል፡፡ የመድን ተከላካይ ክፍል መዳከሙን እና በቀላሉ ለስህተት ተጋላጭ መሆኑን ተከትሎ በ84ኛው ደቂቃ ፖሊሶች በጥሩ እንቅስቃሴ ያገኙትን እድል ሊቁ አልታየ ግብነት ቀይሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በዚሁ ምድብ ሱሉልታ ላይ አክሱም ከተማን ያስተናገደው ሱሉልታ ከተማ 1-1 ተለያይቷል። ሱሉልታዎች በኤርሚያስ ዳንኤል ጎል እስከ ጨዋታው መገባደጃ ድረስ መምራት ቢችሉም ቢንያም ደበሳይ በ88ኛው ደቂቃ እንግዶቹ አክሱሞችን አቻ አድርጓል።  

ቅዳሜ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ መሪው ባህርዳር ከተማ መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው ወሎ ኮምቦልቻን አስተናግዶ 3-0 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። ባህርዳር አለምአቀፍ ስታድየም በተደረገው ጨዋታ አምበሉ ደረጄ መንግስቴ በ9ኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ጎል ሲያስቆጥር ሙሉቀን ታሪኩ በ14ኛው እንዲሁም ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በ81ኛው ደቂቃ ሌሎቹን የማሸነፍያ ጎሎች አስቆጥረዋል።

የምድብ ሀ ቀጣይ ጨዋታዎች

ማክሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2010
ነቀምት ከተማ 09:00 ለገጣፎ ለገዳዲ
ሽረ እንዳ. 09:00 ኢኮስኮ
ደሴ ከተማ 09:00 ቡራዩ ከተማ
ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን 2010
አውስኮድ 09:00 ሰበታ ከተማ