ሪፖርት | አዳማ በግማሽ ደርዘን ጎሎች ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

ከ25ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መሀከል አንዱ የነበረው የአዳማ ከተማ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታ በባለሜዳው ፍፁም የበላይነት በ 6 -1 ውጤት ተጠናቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በ24ኛው ሳምንት ባደረጓቸው ጨዋታዎች ይዘው ከቀረቧቸው ቡድኖች መጠነኛ ለውጥ አድርገዋል። አዳማ ከተማ ይርጋለም ላይ የ1-0 ሽንፈት ከገጠመው ቡድኑ ውስጥ በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ተስፋዬ ነጋሽን በአንዳርጋቸው ይላቅ ሲቀይር ሚካኤል ጆርጅ እና 5 ቢጫ ካርድ ያለው ዳዋ ሁቴሳ በአዲስ ህንፃ እና ቡልቻ ሹራ ተተክተዋል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በታዩት ሁለት ለውጦች ደግሞ በተከላካይ መስመር ላይ የተደረጉ ሲሆኑ ተስፋዬ መላኩ እና በወላይታ ድቻው ጨዋታ በግራ መስመር ተከላካይነት የጀመረው ተክሉ ታፈሰ በግርማ በቀለ እና ዘካርያስ ቱጂ ተቀይረዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ በፍጥነቱ ዝግ ያለ ቢሆንም የአዳማ ከተማ የበላይነት የታየበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመያዝ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሜዳ ላይ ጊዚያቸውን ያሳለፉት አዳማዎች ወደ ሳጥን ውስጥ ዘልቀው መግባት ቢከብዳቸውም ተደጋጋሚ ጥቃት ከመሰንዘር ግን አልቦዘኑም። በ5ኛው ደቂቃ በረከት ደስታ በ8ኛው ደቂቃ ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው ያደረጓቸው ሙከራዎችም ከሳጥን ውጪ የተደረጉ ነበሩ። ባለሜዳዎቹ አዳማዎች በከንዓን ማርክነህ ጨዋታ አቀናባሪነት ታግዘው ከመጫወት በተጨማሪ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮችን በመጫን እና ከሚሰሯቸው ስህተቶች በመነሳት ተደጋጋሚ የማዕዘን ምቶችንም ማግኘት ችለው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በመስመር ተሰላፊዎቹ የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም ያደርግ የነበረው ጥረት ለእንግዶቹ ከባድ ፈተና ሆኗል። በተለይም የበረከት ደስታ እና ሱራፌል ዳኛቸው እንቅስቃሴ ለዐወት ገ/ሚካኤል እና ዘካርያስ ቱጂ ተደጋጋሚ ችግር ሲፈጥርባቸው ነበር።

ሙሉ ለሙሉ በራሳቸው ሜዳ ላይ ሆነው ሲከላከሉ የቆዩት ኤሌክትሪኮች ወደ አዳማ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ለመድረስ 29 ደቂቃዎችን ጠብቀዋል። ኄኖክ ካሳሁን እና አዲስ ነጋሽ ለተከላካይ መስመራቸው ቀርበውና በጎን ተጣምረው የመከላከል ሀላፊነታቸው ላይ ትኩረት ባደረጉበት በዚሁ አጋማሽ ወደ ዲዲዬ ለብሪ ይጣሉ የነበሩ ኳሶች በሱሊማን መሀመድ ጥረት ሲከሽፉባቸው ቆይተዋል። አልሀሰን ካሉሻም በአዲስ ህንፃ እና ኢስማኤል ሳንጋሪ የቅርብ ርቀት ቁጥጥር ይደረግበት የነበረ በመሆኑ ፍሪያማ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም። 29ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ከአዲስ ነጋሽ የተላከለትን ረጅም ኳስ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ አብርዶ በመግባት ያደረገው ሙኩራ በፔንዜ ጥረት ጎል ከመሆን ዳነ እንጂ የኤሌክትሪክ ብቸኛ ሙከራ ግብ ወደ መሆኑ ተቃርቦ ነበር። 
በሂደት የጨዋታ ፍጥነታቸውን በመጨመር በራሳቸው ሜዳ የሚያስጥሏቸውን ኳሶች ለቡልቻ ሹራ በመላክ እና የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች ክፍተት በሚፈጥሩበት ቅፅበት ፈጥነው በመግባት ጫናቸውን የቀጠሉት አዳማዎች በመጨረሻዎቹ 15 ዳቂቃዎች እጅግ በርትተው ታይተዋል። 32ኛው ደቂቃ ላይ ከበረከት የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ሞክሮ ያልተሳካለት ከንዓን ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ የዕለቱን የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል። ከንዓን በቀኝ መስመር ከዘካርያስ ጀርባ በመግባት ከሱራፌል በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ከሱልማን አቡ ፊት በአግባቡ ተቆጣጥሮ ነበር በተረጋጋ አጨራረስ ኳስ እና መረብን ያገናኘው።  43ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከማዕዘን ምት የተነሳች ኳስ በተከላካዮች ስትመለስ ተነጥሎ ቆሞ የነበረው ሱራፌል ዳኛቸው በአስገራሚ ምት በቀጥታ ሁለተኛ ግብ አድርጓታል። አዳማዎች በድጋሜ ወደ ሳጥን ውስጥ ከተጣለ ኳስ በአዲስ ህንፃ አማካይነት ሶስተኛ ግብ ለማግኘት ተቃርበው የነበረ ቢሆንም አጋጣሚው በሙከራው በነበረው ግጭት ለሱሌይማን አቡ ጉዳት ምክንያት በመሆን ብቻ አልፏል።

ከእረፍት መልስ የነበረው የጨዋታ ሂደት በፍጥነት ከመጀመሪያው የተሻለ እና አምስት ተጨማሪ ግቦችን ያስመለከተን ነበር። በሁለት ግቦች ልዩነት እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩት ኤሌክትሪኮች ኄኖክ ካሳሁንን በተክሉ ታፈሰ በመቀየር ነበር የተመለሱት። ከዚህ ውጪም ቡድኑ አልሀሰን ካሉሻን ከአዲስ ነጋሽ ጋር በመጣመር እና የጥልቅ አማካይነት ሚናን በመስጠት እንዲሁም በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የተከላካይ መስመሩን ወደ መሀል አስጠግቶ መጫወትንም ምርጫው አድርጎ ነበር። እነዚህ ውሳኔዎች የግብ ናዳ ሊያወርዱ እንደሚችሉ ምልክት መስጠት የጀመሩት ግን ገና በመጀመሪያዎቹ 10 ደቂቃዎች ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ቡልቻ ሹራ እና በረከት ደስታ በሁለት አጋጣሚዎች የኤሌክትሪክን የተከላካይ መስመር አልፈው ከዮሀንስ በዛብህ ጋር ተገናኝተው በማይታመን መልኩ ስተዋል። ሆኖም ከ60ኛው ደቂቃ በኃላ የተገኙት ዕድሎች የመከኑ አልነበሩም።
ኤሌክትሪኮች በተሻለ ደረጃ ኳስ ይዘው በአዳማ ሜዳ ላይ መቆየት እየቻሉ የነበረ ቢሆንም የሚቀሟቸው ኳሶች ግን መልሰው በራሳቸው ላይ አደጋን ይፈጥሩ ነበር። በተመሳሳይ ጥቃት የተገኘው የ61ኛው ደቂቃ አጋምሚም በተከላካዮች ቢመለስም በረከት ደስታ ከጥቂት ሜትሮች ርቀት ላይ ግብ አድርጎታል። ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ በረከት ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ከንዓን ማርክነህ ብዙ ሳይቸገር በግንባሩ በመግጨት ለቡድኑ አራተኛውን ለራሱ ደግሞ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል። በሁለቱ ጎሎች መሀከል ግን ተክሉ ተስፋዬ በአዳማ ተከላካዮች መዘናጋት ከዲዲዬ ለብሪ የደረሰውን ኳስ ወደ ጎል ቀይሮ የኤሌክትሪክ ብቸኛ የማስተዛዘኛ ግብ ባለቤት ሆኗል። 68ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩን በግርማ በቀለ ቀይረው የኃላ ክፍተታቸውን ተደጋጋሚ ስህተት ለማረም የሞከሩት ኤሌክትሪኮች አሁንም የአዳማን መልሶ ማጥቃት መቀነስ አልቻሉም።

አዳማዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ አመዝነው በመከላከል ከሚያስጥሏቸው ኳሶች በፍጥነት ወደ ማጥቃት ዞኑ እየደረሱ ከጨዋታ ውጪ በሆነ አቋቋም እና ባልተመጠኑ ቅብብሎች ልዩነቱን ከዚህ በላይ ማስፋት የሚችሉባቸውን ዕድሎች አምክነዋል። ሆኖም የቡድኑ በራስ መተማመን መጨመር የመሀል ተከላካዮቹ ሙጂብ እና ምኞት በማጥቃት ሂደቱ ላይ በቀጥታ እስክሳተፉ ድረስ ከፍ ያለ ነበር። 82ኛው ደቂቃ ላይ የትቆጠረውም ግብ ከተከላካዮች ጀርባ ሲጣል በብዙ ርቀት ከተሳፋዬ መላኩ ጀርባ ተነስቶ ቀድሞ በመድረስ በግምት ከ30 ሜትር በላይ ሮጦ አስገራሚ ግብ ያስቆጠረው የአጥቂነት ልምዱ ያለው የመሀል ተከላካዩ ሙጂብ ቃሲም ነበር። ዐወት ገ/ሚካኤል በሱሊማን መሀመድ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የመጨረሻ ደቂቃ ፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ ሚካኤል ጆርጅ ስድስተኛ ጎል አድርጎት የጨዋታው ፍፃሜ ሆኗል። ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ነጥቡን 36 አድርሶ 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከነበረበት በአንድ ደረጃ ዝቅ ብሎ ወደ 15ኛነት ወርዷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ

ከፈጣሪ በመቀጠል ለዛሬው ውጤት ያበቃን በተጨዋቾቹ መሀል ያለው ፍቅር እና አንድነት ነው። ይህን ጨዋታ ለማሸነፍ የነበራቸው ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነበር። ይህ ቁርጠኝነታቸውም በቀጣይ ጨዋታዎች ውጤት እንደሚያመጣልን እንጠብቃለን።

ም/አሰልጣኝ ቦጋለ ዘውዴ

የወራጅ ቀጠና ውስጥ እንዳለ ቡድን ዛሬ በጣም የወረደ ጨዋታ ነው የተጫወትነው። በቀሩት አምስት ጨዋታዎች ቡድኑን ለማትረፍ ጥረት እናደርጋለን። ባለፉት ሳምንታት መጠነኛ ማሻሻል ያሳየነው በዚሁ ቡድን ነበር። መሀል ተከላካይ ቦታ ላይ የፍጥነት ችግር የነበረ ቢሆንም ምንም ልናደግ አንችልም። ያሉን ተጨዋቾች እነዚህ ብቻ ናቸው።