ፌደሬሽኑ ከEBC ጋር በደረሰው ስምምነት ዙርያ ከክለቦች ጋር ይወያያል

( ዜናው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት የተላከ ነው)

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) ጋር በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ዙሪያ ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ጋር ነገ ከጠዋቱ 4፡00 ጀምሮ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ውይይት ያካሂዳል፡፡

በውይይቱ ፌዴሬሽኑና EBC የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን በቀጥታ የተሌቭዥን ስርጭት አማካኝነት በመላ ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ ነሃሴ 6/2007 ዓ.ም የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ አስመልክቶ ስለ ስምምነቱ ፋይዳና ሂደት ገለፃ የሚደረግ ሲሆን ከፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ በክለቦች መብትና ተጠቃሚነት ዙሪያም ግልጽ ውይይት ይካሄዳል፡፡

ስምምነቱ ይፋ መደረጉንና መፈረሙን ተከትሎ ከተለያዩ በላድርሻ አከላት የተነሱት ጥያቄዎች በተለይም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በደብዳቤ አቋሙን የገለጸበት አግባብ ተቀባይነት እንዳለው ታምኖበታል፡፡ ነገ ከጠዋቱ 4፡00 ጀምሮ የሚካሄደውና የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ፕሬዝዳንቶች እና ስራ አስኪያጆች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ስምምነቱን አስመልክቶ ሊነሱ የሚችሉትን ጥያቄዎች በመቀበል የማስተካካያ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ክለቦች የውይይቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አስተላልፋል፡፡

ፌዴሬሽኑና ኢቢሲ አለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጨዋታዎችን በቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ዓላማዎች በዋነኝነት የወጣቱን ትውልድ የእግር ኳስ ስፖርት ተነሳሽነት ማሳደግ፣ የብሔራዊ እና አገር ውስጥ ውድድሮችን የቀጥታ ስርጭት ተደራሽነት ማረጋገጥ እንዲሁም ለእግር ኳስ ስፖርት ዘላቂና አስተማማኝ እድገት አመቺ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ እንደሚመሰረት መገለጹ ይታወሳል፡፡

ማስታወሻ፡- በውይይቱ የሚሳተፉት የፌዴሬሽኑ የስራ ሃላፊዎችና የክለቦች ተወካዮች ብቻ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *