ታደለ መንገሻ ወደ አርባምንጭ ከነማ አምርቷል

የክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር የመወያያ ርእስ ከነበሩት ተጫዋቾች አንዱ የነበረው ታደለ መንገሻ ሳይጠበቅ ወደ አርባምንጭ ከነማ አምርቷል፡፡

ክለቡ እንዳስታወቀው ከታደለ መንገሻ ጋር ያደረጉት ድርድር በስኬታማ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን የተጫዋቹ በፌዴሬሽን ተገኝቶ በይፋ መፈረም ብቻ ይቀራል፡፡ አርባምንጭ ከነማ ለአጥቂ አማካዩ በ2 አመት ከ1.8 – 2 ሚልዮን ብር (በወር ከ 75 – 80 ሺህ ብር) ለመክፈል ተስማምቷል፡፡

ታደለ መንገሻ የደደቢት ኮንትራቱ ማለቁን ተከትሎ በደደቢት ለመቆየት አልያም ለኢትዮጵያ ቡና ፊርማውን ለማኖር ድርድሮች ሲያደርግ እንደመቆየቱ የቀጣይ የውድድር ዘመን ማረፍያው ከሁለቱ ክለቦች እደማይዘል ተገምቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ባሳለፍነው ሳምንት አበባው ቡታቆን በከፍተኛ የደሞዝ መጠን ያስፈረመው አርባምንጭ ተጫዋቹን የግሉ አድርጎታል፡፡

አርባምንጭ ከነማ በተቀዛቀዘ ሁኔታ የዝውውር ገበያውን ተቀላቅሎ በአንድ ሳምንት ልዮነት ትልልቅ ስም ያላቸው ተጫዋቾችን በማስፈረም የተጫዋቾች የሀገሪቱ የደሞዝ ጣርያን አሻሽሎታል፡፡ የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተቀዛቅዘው ወደ ዝውውር ገበያው የገቡበትን ምክንያት አስረድተዋል ‹‹ መጀመርያ አካባቢ ትኩረት አድርገን ስንሰራ የነበረው የተጫዋቾችን ኮንትራት በማደስና ተጫዋቾች እንዳይለቁ በማግባባት ላይ ነበር፡፡ እስካሁን የለቀቁት ተጫዋቾች 2 ብቻ ሲሆኑ የ7 ተጫዋቾቻችንን ኮንትራት ማደስ ችለናል፡፡ ሌሎች ኮንትራታቸውን የምናድስላቸውም ተጫዋቾችም ይኖራሉ፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ታደለ እና አበባው
ታደለ እና አበባው (c) Tadu Mengesha

አርባምንጭ ከነማ ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ 4 ተጫዋቾችን ከብሄራዊ ሊጉ ክለቦች ለማስፈረም የተስማማ ሲሆን ወጣት ተጫዋቾችንም ከወጣት ቡድኑ አሳድጓል፡፡ በቅርቡም የተጫዋቾቹን መፈረም ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ነሃሴ 23 ለመጀመር ያቀደ ሲሆን የአየር ሁኔታውን አይተው በአርባምንጭ ከተማ አልያም በአጎራባች ከተሞች ዝግጅት እንደሚጀምሩ ክለቡ አስታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *