የ2007 ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ወር ውላቸውን ለማደስ በቃል ደረጃ የተስማማቸው ተጫዋቾችን ውል በፌዴሬሽን ተገኝቶ አስፈርሟል፡፡
የ2 አመት ኮንትራት በመፈረም ውላቸውን በይፋ ያደሱት ደጉ ደበበ ፣ አለማየሁ ሙለታ ፣ ምንያህል ተሸመ እና በኃይሉ አሰፋ ናቸው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጫዋቾች ውል እደሳ በተጨማሪ አስቻለው ታመነን ለማስፈረም መስማማማቱንና በቀናት ውስጥ በይፋ ኮንትራት እንደሚፈርም ለመጀመርያ ጊዜ ይፋ አድርጓል፡፡ የብሄራዊ ቡድናችን ተከላካይ ለክለቡ መፈረሙን በተለያዩ ጊዜያት ቢናገርም ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም ነበር፡፡
በፖርቱጋል የሙከራ ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙት ሳላዲን በርጊቾ እና ናትናኤል ዘለቀ ሲመለሱ ኮንትራት እንደሚፈርሙ ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ናትናኤል በክለቡ አዲስ አሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማን እቅድ ውስጥ ያለ ሲሆን አሰልጣኙ ናትናኤል ቅዱስ ጊዮርጊን ባይለቅ ምርጫቸው እንደሆነ ተሰምቷል፡፡ ናትናኤል ወደ ፖርቱጋል ከማቅናቱ በፊት ውሉን ለማደስ ከስምምነት ቢደርስም ዝውውሩ ከተሳካ በነፃ ዝውውር ቅዱስ ጊዮርጊስን ይለቃል፡፡ በተመሳሳይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ኮንትራቱ የተጠናቀቀው ሳላዲን በርጊቾ የሙከራ እድሉ ሳይሳካ ከተመለሰ ውሉን ለማደስ መስማማቱን ክለቡ አስታውቋል፡፡
በተያያዘ ዜና ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ የዝውውር መስኮት ተጨማሪ ተጫዋች ከሃገር ውስጥ እንደማያስፈርም አስታውቋል፡፡ ይህንን ተከትሎም ከክለቡ ጋር ለረጅም ጊዜ ስሙ ሲያያዝ የቆየው የቡናው አስቻለው ግርማ ለጊዮርጊስ የመፈረም እድሉ የመነመነ ሆኗል፡፡
ቅዱሰ ጊዮርጊስ ከሃገር ውስጥ ተጨማሪ ተጫዋች እንደማያስፈርም ቢያስታውቅም ከውጭ ሃገር ተጫዋች ለማስፈረም እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታውቋል፡፡ የሚመጡት ተጫዋቾች ከምን ሃገር እንደሆነ ባይታወቅም አሰልጣኝ ኩፕማን ከሰሩበት ጋና ሊሆን ይችላል ተብሏል፡፡
©Soccerethiopia.net