ከፍተኛ ሊግ | ደሴ ከተማ ሰባት ተጨዋቾችን ሲያስፈርም የአምስት ተጨዋቾችን ውል አድሷል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በመወዳደር ላይ የሚገኘው እና ባሳለፍነው ዓመት ወደ ሶስተኛው የኢትዮጵያ የሊግ እርከን (አንደኛ ሊግ) ሊወርድ ጫፍ ላይ ደርሶ የተረፈው ደሴ ከተማ በቀጣይ በከፍተኛ ሊጉ ተጠናክሮ ለመቅረብ በርከት ያሉ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ እየቀላቀለ ይገኛል።

በዚህም መሰረት ክለቡ ሰባት ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ መቀላቀሉ ተሰምቷል። ክለቡ የመጀመሪያዎቹ ፈራሚ አድርጎ ወደ ክለቡ የቀላቀላቸው የነቀምቶቹን ቻላቸው መንበሩ፣ አላዛር ዝናቡ፣ ደረጄ ነጋሽ እና ግዛው ሸንቁጤ ሲሆኑ ከፈራሚዎቹ አንፃር ክለቡ የአጥቂ እና የተከላካይ ክፍሉን ለማጠናከር ያለመ ይመስላል። ከነቀምቶቹ አራት ተጨዋቾች በተጨማሪ የመሃል ተከላካዩ አሸናፊን ከገላን ከተማ አስመጥቷል።

በ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጥቂት ጨዋታዎችን (6) በማሸነፍ ከሱሉልታ ከተማ ጋር የሚስተካከሉት ደሴዎች ጨዋታን የማሸነፍ ችግራቸውን ለመቅረፍ አሁንም ገበያው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ስንታየው እሸቱን ከከፋ ቡና እንዲሁም የቀድሞ ተጨዋቻቸው የነበረውን አብደላ እሸቱን ከአውስኮድ ዳግም በመመለስ ቡድናቸውን እያዋቀሩም ይገኛሉ።

ክለቡ አዳዲስ ተጨዋቾችን ከማስመጣት ጎን ለጎን የነባር ተጨዋቾችንም ውል እያደሰ ይገኛል። አዲስዓለም ዘውዱ፣ እስካድማስ ከበደ፣ ብርሃኑ በላይ፣ አንዋር መሐመድ እና ሰለሞን ውል ያደሱ ነባር ተጨዋቾች ናቸው።