ቅዱስ ጊዮርጊስን በሊቀ-መንበርነት ለረጅም ጊዜያት የመሩት አብነት ገ/መስቀል የካፍ ቋሚ ኮሚቴ አባል ሆነው መመረጣቸውን ክለቡ በፌስቡክ ገፁ ዘግቧል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ዜናውን ይፋ ያደረገው በዚህ መልኩ ነው፡፡
‹‹ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አቶ አብነት ገብረመስቀል የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ፕሬዚዳንትን የአፍሪካ ክለቦች ውድድርን በበላይነት በሚመራው የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው እንዲሰሩ የመረጣቸው መሆኑን ነሐሴ 20 ቀን 2006 ዓ ም በፃፈው ደብዳቤ አሳውቋል።
ካፍ አቶ አብነት ገብረመስቀልን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በቀጥታ መምረጡ ለሃገራችን ስፖርት ክለቦች ሁሉ ፈር ቀዳጅ ተግባር ሲሆን እርሳቸውም በአህጉራዊው መድረክ የበለጠ ተሳትፎ በማድረግ ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ታላቅ ድርሻ እንደሚያበረክቱ ይታመናል። አቶ አብነት ገብረመስቀል በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ካፍ ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበርን በመወከል የአፍሪካ ታላላቅ ክለቦች ጉባኤ ላይ የመወያያ ፅሑፍ ማቀረባቸው አይዘነጋም።
አቶ አብነት ገብረመስቀል የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበርን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ ከሚያደረጉት ያላሰለሰ ጥረትና ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ ስፖርት ዕድገት በማበርከት ላይ ከሚገኙት ተጨባጭና በተግባር የሚታይ ታላቅ አስተዋፅዖ ጎን በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በቋሚ ኮሚቴ ውስጥ እንዲያገለግሉ በመመረጣቸው የተሰማንን ልባዊ ደስታ እየገለጽን የተቃና የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው እንመኛለን
።