በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሁለቱ ኢትዮጵያውያንን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በግብፅ ፕረምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ሁለቱ ኢትዮጵውያን የሚገኙባቸው ኤል ጎውና (ጋቶች ፓኖም) እና ስሞሃን (ዑመድ ኡኩሪ) ያገናኘው ጨዋታ ቅዳሜ ምሽት ተከናውኖ አንድ አቻ ተጠናቋል።

ከቅርብ ግዜ ወዲህ በተመሳሳይ የውጤት ማጣት ላይ የሚገኙት ሁለቱ  ክለቦች ይሄን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተው ነበር የጀመሩት። ኤል ጎውና ሽመልስ በቀለ በአምበልነት የሚመራው ፔትሮጀትን ካሸነፈ በኋላ እስካሁን ድረስ ሙሉ ሶስት ነጥብ ሳያገኝ ሲቆይ ስሞሃም ባለፉት ሳምንታት ተከታታይ ሶስት ድሎች አስመዝግቦ በሊጉ አናት ላይ ከተቀመጠ በኋላ ከሀራስ ኤል ሁዳድ ፣ ኤል ኤንታግ ኤል ሀርቢ እና ዳክልይ ሶስት ተከታታይ የአቻ ውጤት አስመዝግቦ ነበር ወደ ዛሬው ጨዋታ የገቡት።

በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢታይም ከባለሜዳዎቹ በተሻለ ስሞሃዎች በሁለት አጋጣሚዎች ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል በተለይም ዑመድ ኡክሪ ከሺሎንጎ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለ አንድ ተገናኝቶ ያመከነው ለግብ የቀረበ ነበር። እስከ 25′ ደቂቃ ድረስ ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳያረጉ የቆዩት ባለሜዳዎቹ ኤል ጎውናዎች በ25 ደቂቃ ላይ በቺካታራ እና መሃመድ ኣቡ ጋብር ሙከራዎች ቢያደርጉም ሃይታን መሃመድን የፈተኑ አልነበሩም።

ቀስ በቀስ የጨዋታው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወደ እጃቸው ያስገቡት ባለሜዳዎቹ ኤልጎውናዎች የመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በርከት ያሉ የጎል እድሎች ፈጥረዋል በተለይም የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ኢስላም ሮሻድይ ከመስመር የተሻማችለት ኳስ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ ቋሚ የመለሰችለት በኤል ጎውና በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነው።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ኤል ጎውና ወደ ስሞሃ ግብ ክልል ቀርበውብ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ሶምሃዎች በአንፃሩ ለወትሮ የሚለዩበት የኳስ ፍሰት ሳያሳዩ በመከላከል ተጠምደው ነበር። በዚህ መሐል ነበር መሃመድ ናዲ ከመስመር ያሻማት ኳስ ተጠቅሞ ጋቶች ፓኖም ሲመታት ግብ ጠባቂው የመለሳት ኳስ አህመድ መግዲ አክርሮ መቶ አስቆጥሯት ባለሜዳዎቹን እየመሩ ወደ ዕረፍት እንዲያመሩ አስችሏል።

ከዕረፍት መልስ ዑመድ ኡኩሪን በኒሲምባ ቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ስሞሃዎች ከመጀመርያው አጋማች በተሻለ ተጭነው በመጫወት በርከት ያሉ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር። በተለይም መሃመድ ሃምዲ ከ ሺሎንጎ የተላከለት ኳስ ተጠቅሞ ያልተጠቀመበት ፣ ሸሪፍ ረዳ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እና አህመድ መግዲ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት የሚጠቀሱ ሙከራች ናቸው። በ71ኛው ደቂቃ ላይ በሳጥኑ ጠርዝ በኒሲምባ የተሰራው ጥፋት ተከትሎ የተገኘው ቅጣት ምት መሃሙድ ሙአዝ መቶ በማስቆጠር ስሞሃዎችን ሽንፈት ከማስተናገድ የገላገለች ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ምላሽ ለመስጠት አጥቅተው የተጫወቱት ኤል ጎናዎች ብዙም ሳይቆዩ ግብ ለማስቆጠር ተቃርባው ነበር ካሜሮናዊው ጆናታን ነጋውም ኣክርሮ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ ሲመልስበት ጋቶች ፓኖም የተመለሰው ኳስ ተጠቅሞ ያረገው ሙከራም ለግብ የቀረበ ነበር። ውጤቱ በአቻ መጠናቀቁ ተከትሎ ስሞሃ ተከታታይ አራተኛ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ ኤል ጎና በበኩሉ ከባለፈው በ ኤል ጋይሽ ከደረሰበት የአምስት ለባዶ ሽንፈት አገግሞ አንድ ነጥብ ማስመዝገብ ችሏል።

በቀጣይ የዑመድ ኡክሪ ሶምሃ እና የሽመልስ በቀለ ፔትሮጀት ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚጫወቱ ይሆናል።