አቶ ኢሳይያስ ጂራ የትግራይ እና አማራ ክለቦች የእርስ በእርስ ጨዋታዎቻቸውን በየሜዳቸው እንደሚያደርጉ ተማምነዋል

– በሁለቱ ክልል በሚገኝ ሜዳ የእርስ በእርስ ጨዋታ ከተደረገ 375 ቀናት ተቆጥሯል።


በኢትዮጵያ የውስጥ ውድድሮች ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየውን ያህል ፈታኝ ጊዜያት አሳልፎ አያውቅም። ለዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየው የስታድየም ስርዓት አልበኝነት ከሀገሪቱ ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተደምሮ ወደ ፖለቲካዊ የብሔር ቅራኔ መልኩን በመቀየር ክስተቶችን በእግርኳሳዊ ህግጋት ለመዳኘት አስቸጋሪ ሲሆን ተስተውሏል።

በእነዚህ ጊዜያት ከታዩና መስመር ለማስያዝ ፈታኝ ከነበሩ ጉዳዮች ዋንኛው በትግራይ እና አማራ ክልል የሚገኙ ክለቦች መካከል የሰፈነው ውጥረት ነው። ኅዳር 23 ቀን 2010 ወልዲያ ላይ በወልዲያ እና መቐለ ከተማ መካከል ሊደረግ ከነበረው ጨዋታ ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ ከስታድየም ውጪ በተከሰተ ግጭት ጉዳት ከደረሰ በኋላ ጨዋታው ጥር 9 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ተከናውኗል። ከዛ ክስተት ወዲህ በሁለቱ ክልል ክለቦች መካከል የተደረጉ 7 ጨዋታዎችም የተከናወኑት በአዲስ አበባ ስታድየም ነበር። በከፍተኛ ሊጉ 17 ጨዋታዎች መካሄድ ከነበረባቸው በተቃራኒው በአዲስ አበባ የተለያዩ ሜዳዎች እና አዳማ ላይ ሲከናወን በአንደኛ ሊጉ ምድብ ሐ ላይ በጋራ ተደልድለው የነበሩት የሁለቱ ክልል ክለቦች ጨዋታውን ለማድረግ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ምድብ በሦስት የተለያዩ ንዑስ ምድቦች ተከፍሎ ለየብቻ ጨዋታቸውን አድርገዋል። በዚህም ኅዳር 9 ቀን 2010 ለመጨረሻ ጊዜ በከፍተኛ ሊጉ ባህር ዳር ከተማ ከ አክሱም ከተማ ካደረጉት ጨዋታ በኋላም የሁለቱ ክልል ክለቦች የእርስ በዕርስ ጨዋታቸውን በየሜዳቸው ካደረጉ 375 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ አዲሱ የ2011 የውድድር ዘመን ሲጀመር ምላሽ ከሚያሻቸው ጥያቄዎች መካከል ዋንኛው አምና በገለልተኛ ሜዳ እንዲደረጉ የተወሰኑ ጨዋታዎች ዘንድሮስ እጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል የሚለው ነበር። በፕሪምየር ሊጉ አራት የትግራይ እና ሁለት የአማራ ክልል ክለቦች የሚገኙ እንደመሆኑ የጨዋታዎች ቁጥር ከፍ የሚል በመሆኑ መርሐ ግብሮቹን በየሜዳቸው የማድረግ ፈተናን ለመወጣት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለወራት የዘለቀ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

 

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት ግንቦት ወር ላይ የተረከቡት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ያለፉትን ወራት ችግሩን ለመፍታት ስለተደረገው ጥረት እና ቀጣይ ጉዳዮች የሰጡትን ሰፊ ማብራርያ እንዲህ አቅርበነዋል።

በአንድ ሀገር ውስጥ በሚኖሩ ማኅበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ በእግር ኳሱ ዙሪያ ተሳታፊ የሆኑ አካላት እየተራራቁ ውድድር ማድረጋቸው ከባድ ነገር ነው። በ2010 በነበረው ውድድር ዓመት ላይ የታየው ነገር ግልፅ ነው፤ ውድድሩን መደረግ ባለበት ቦታ ለማከናወን ከባድ ነበር። መፍትሄውም ጌዜያዊ ነበር፤ በሰዓቱ ውድድሩን ለማከናወን እና ለማጠናቀቅ በነበረው ጥረት በጊዜው የተደረገው ትክክል ነበር። ነገር ግን እንዲህ አይነቱ ጉዳይ በቀጣይ መቀጠል የለበትም የሚል ፅኑ እምነት ነበረኝ። የዛሬ ዓመት ክለቦቹ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በነበረ ስብሰባ ላይ ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም በጊዜው በነበረው ሁኔታ ክለቦቹም የመረጡት በገለልተኛ ሜዳ ለማከናወን ነበር።

አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ከጅምሩ ይህን ነገር መስመር ማስያዝ እንዳለብን ተማምነን ነው ስራ የጀመርነው። ነገሮችን በእግር ኳሳዊ አስተሳሰብ ማየት መቻል አለብን በሚል እሳቤም ጭምር ነው። በመጀመርያ ያደረግነው ከስፖርት ኮሚሽን ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት በማድረግ መገባባት ላይ መድረስ እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በእየርከኑ በማስቀመጥ ከሁለቱ ክልል ኃላፊዎች ጋር በካፒታል ሆቴል ስብስባ ማድረግ ነበር። ከሁለቱም ክልሎች ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ፣ የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ፣ የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት እና የፀጥታ ዘርፍ በተወጣጡ የበላይ አመራሮች መካከል የተደረገው ስብሰባ መልካም የሚያስብል እና ተስፋ ያለው ምላሽ ከሁለቱም ወገን የተሰማ በመሆኑ ለሁለቱም ክልል ከላይ የመጣውን ሰላማዊ መግባባት በተዋረድ ወደ ስር በመወስድ በክልሉ የሚገኙትን ክለቦች፣ የክለብ ባለድርሻ አካላትን፣ የክለብ ደጋፊዎችን፣ የስፖርቱን ማኅበረሰብ ማሳታፍ በሚያስችል መልኩ ውይይት እንዲደረግ በዛም ላይ የብሔራዊ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ በተጋባዥነት ተገኝቶ ግብዓቶችን እንዲወስድ አቅጣጫ አስቀምጠን ነበር የተለያየነው።

በዚህም መሰረት የትግራይ ክልል ውቅሮ ላይ ባደረገው ስብሰባ ሁሉንም ባለድርሻ አካላቶች በመጥራት እንዲሁም የብሔራዊ ፊዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቱን በመጋበዝ ውይይት አድርገዋል። በውይይቱም ክለቦችም ሆነ ክልሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ስፖርቱ ምን ያህል እንደተጎዳ ያስተዋለ ሲሆን ክልሉም ሆነ ክለቦች ማግኘት የሚችሉት የነበረውን ጥቅም እንዳጡ አያይዘው ገልፀዋል። በማህበራዊ ትስስር ላይ የፈጠረውን ጥላሸት ማፅዳት እንዳለባቸው መተማመን ላይ ደርሰዋል ፤ ምን ሁኔታዎች ማሟላት እንዳለባቸው አያይዘውም ተዋያይተውል።

በአማራ ክልል የተደረገው ስብሰባ በሁለት ቦታዎች ላይ የተደረገ ነበር። በጎንደር እና ደብረ ብርሃን ከተሞች በተደረጉ ስብሰባዎችም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በመገኘት ጠቃሚ ግብዓቶችንም መውሰድ ችሏል። ስብሰባው በትግራይ ክልል ከተደረገው ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ሀሳቦች የፈለቁበት ነበር ፤ ሁለቱም ክልሎች በሜዳቸው የመጫወት እና እግር ኳስን ቅድሚያ በመስጠት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልፀዋል። በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ጥናታዊ ፅሑፍም ቀርቦ ነበር። በ2010 መነሻ ችግሮችን የቃኘው ይህ ጥናታዊ ፅሑፍ በ2011 እንዴት መቅረፍ እንደሚቻልም አትቷል። ከመፍትሄው ውስጥ አንዱ አቅጣጫ የነበረው በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉት አመራሮች በጋራ ወይም በተናጠል ስለ ጉዳዩ መግለጫ ቢሰጡ የሚል ነበር። ይህን እንደ አንድ ግብዓት በመውሰድ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሐብታሙ ሲሳይ እንዲሁም የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው እንዲሁም እኔ ወደ ሁለቱም ክልል አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር ባለፈው ሳምንት በማምራት ውይይት አድርገናል። በዚህም በጎ ምላሽ አግኝተን ጨዋታዎች በየክልሎቹ እንዲደረጉ የሚስፈልገውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አያይዘው ገልፀዋል። ከሁለቱም ክልል አስተዳዳር በጎ ምላሽ አግኝተናል። በዚህም መሰረት ቀጣይ ጨዋታዎች በየሜዳቸው ይከናወናል።

በአማራ ክልል አስተዳደር የተሰጠው ምላሽ በአጭሩ ኃላፊነቱን ክልሉ እንዲሚወስድ ይህ ዓይነቱ ነገር ለሀገራችን እንደማይጠቅማት ስፖርቱ ደግሞ ከምንም በላይ ከዚህ ገለልተኛ መሆን እንዳለበት ገልፀው ማንኛውም ተጫዋችም ሆነ የስፖርቱ ባለድርሻ አካል ወደ ክልሉ በሰላም ገብቶ በሰላም እንዲወጣ ፍላጎታቸው መሆኑ ተገልጾ ለዚህም ክልሉ የሚጠበቅበትን ዝግጅት እንደሚያደርግ ፤ ይህንን ለማረጋገጥ ከተፈለገ በተናጠልም ሆነ በጋራ መግለጫ ለመስጠት ፍቃዳቸውን ማግኘት ተችሏል።

በትግራይ ክልል በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ቀደም ብለው ዝግጅት ያደረጉ ሲሆን ጥሰት በሚፈፅሙ በክልሉ ውስጥ ባሉ ክለቦች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ቀደም ባሉት ጨዋታዋች ላይ ማስተላለፋቸውን ገልፀው ክልሉ ለረብሻም ሆነ ለሁከት ምንም ትዕግስት እንደሌለው ተገልጿል። የክልሉ አስተዳደር የሚፈልገበትን ቅድመ ሁኔታዋች ማሟላት እንደሚችል ተገልጿል።

በቀጣይ ችግሮች እንዳይከሰቱ…

የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ዘርፈ ብዙ ነው ጉዳዩ የክለቦች ብቻ አይደለም ፤ ብዙ ተያያዥ ነገሮች አሉ። በክረምቱ ወራት ቀደም ብለን መስራት የጀምረነው ስራ ውስጥ አንደኛው የዲሲፕሊን መመሪያችን ላይ ነበር። ያለንን መመሪያ መነሻ በማድረግ የፍትህ አካላቶችን እንዲሁም የስፖርቱ ባለሙያዎችን በመስብስብ ውይይት እየተደረገ ይገኛል። ውይይቱ ክለቦችንም ያካትታል። ይህን መመሪያ ለመለወጥ ብዙ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ነው ፤ ሁሉንም ክለቦችም ሆነ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላትን በዕኩል ዓይን ማየት ለማስቻል ተሞክሯል። ከዚህም በተጨማሪ በዲስፕሊን እና ይግባኝ ሰሚ ኮሜቴ ያለውን የህግ ትርጓሜ ወደ አንድ ለማምጣት በጋራ ውይይት አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ በዳኞቻችን እና ለኮሚሽነሮቻችን የተግባር እና የኀልዮት ስልጠና በተሻሻሉ ህጎች ላይ በመስጠት እንዲሁም ጨዋታዎችን በመቅረፅ የነበረውን የዳኝነትም ሆነ የተጫዋቾች ስነ ምግባር ለማስተዋል በቁርጠኝነት ተነስተናል።

የባለሜዳ ቡድን ኃላፊነት…

ከሁለቱም ክልሎች እና ከክለቦች ጋር በነበረን ውይይት ኃላፊነቱ ወደ ክልሉ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ በፀጥታው ረገድ የሚደረግ ጥበቃ የሚኖር ሲሆን ክለቦች ስፍራው ድረስ በመሄድ በመቀበል የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችንን ጠብቆ ማስሄድ እንደሚያስፈልግ በመግለፅ ጭምር ተነጋግረናል። የደጋፊ ቁጥር ውስንነት የሌለው ሲሆን ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው እንግዳው ቡድን የደጋፊውን ቁጥር በማሳወቅ ቦታ ይያዝለታል። እንግዳው ቡድንም በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ አጥብቆ መስራት አለበት። ከዚህ በተጨማሪም የብሔራዊ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ በቦታዎቹ ላይ በመገኘት የበኩላቸውን ይወጣሉ።

በስተመጨረሻ…

ባለን አቅም በቅንነት እየተንቀሳቀስን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ፍፁም ሰላማዊ ውድድር ማየት ነው የምንፈልገው። እኔ ድምፅ አግኝቼ ወደዚህ ቦታ ስመጣ እግርኳሱ አንድ እርምጃ ከፍ ለማድረግ ታምኖብኝ ነው። ሁሉም የስራ አስፈፃሚ ይህን ለማሳካት የቡካላችንን እንወጣለን። ለሁሉም ነገር መሳካት ደሞ ትልቁ እና ዋናው ጉዳይ ሰላም ነው። ይህን ማስፈን ደግሞ የኛ ኃላፊነት ነው። በመስከረም ወር ላይ አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ጉዳይ ለመፍታት የቻልን ሲሆን በቀጣይ የሌሎችንም ጉዳይ ለመፍታት የምንቀሳቀስ ይሆናል። ሲዳማ ከወላይታ ድቻ ፣ ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመሳሳሉትን ታች ድረስ በመውረድ ሰላም ማምጣቱ የሚከናወን ይሆናል። ሚዲያውም ሁሌም ስለ ሰላም ቢናገር ፣ ቢያግባባ የተሻለ ነገር ነው ብዬ ነው የማምነው። የ2011 የሰላም ውድድር ዘመን የምናይበት ዓመት እንዲሁንልኝ ምኞቴ ነው።


የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በቀጣይ ሳምንት በሚደረጉ የአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥሉ ኅዳር 30 ቀን 2011 መቐለ ላይ መቐለ ሰባ እንደርታ ከባህር ዳር ከተማ እንዲጫወቱ መርሐ ግብር ተይዞለታል። በታቀደለት ጊዜ እና ቦታ የሚከናወን ከሆነም በጨዋታው የሚከሰተው ክስተት በቀጣይ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች ላይ ከሚያሳርፈው ተጽዕኖ አንጻር እጅግ ተጠባቂ መርሐ ግብር ነው።