ሪፖርት | ወልዋሎ በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድሉን አስመዝግቧል

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈቶች ያስተናገደው ወልዋሎ ኤፍሬም አሻሞ ባስቆጣራት ብቸኛ ግብ ደቡብ ፖሊስን በማሸነፍ የመጀመርያ ድሉ አስመዝግቧል።

ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት በመቐለ 70 እንደርታ ከተሸነፉበት ስብስብ በረከት ተሰማን በቢንያም ሲራጅ ፣ አስራት መገርሳን በብርሃኑ አሻሞ፣ ፕሪንስ ሰቨሪንሆን በአብዱራህማን ፉሴይኒ፣ አማኑኤል ጎበናን በዋለልኝ ገብሬ  ተክተው ሲገቡ እንግዶቹ ደቡብ ፖሊሶች በበኩላቸው ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋን በፍሬው ገረመው ፣ ሳምሶን ሙልጌታን በዘነበ ከድር፣ ብሩክ  ኤልያስን በብርሃኑ በቀለ፣ ኄኖክ አየለን በብሩክ አየለ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። 

ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች በሚያደርጓቸው ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች የጀመረው ጨዋታው  በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በወልዋሎዎች ሙሉ ብልጫ የታየ ሲሆን ያልተደራጀው የደቡብ ፖሊስ የመከላከል አደረጃጀትም በተደጋጋሚ ጊዜ ሲጋለጥ ተስተውልዋል። በተለይም አበባው ቡታቆ የተሰለፈበት የግራ መስመርን በመጠቀም ወልዋሎዎች ይህን ክፍተት ተጠቅመው ያለቀላቸው የግብ እድሎች ፈጥረዋል። እንየው ካሳሁን አሻምቶት አዶንጎ በግንባሩ ገጭቶ ያልተጠቀመበት እና ዋለልኝ ገብሬ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ አብዱልራሕማን ፉሴይኑ ባጠበበበት አቅጣጫ አንድ ለአንድ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያመከነው ወርቃማ እድል በወልዋሎ በኩል የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ብርሃኑ ቦጋለ በሁለት አጋጣሚዎች ከቅጣት ምት ያረጋቸው ግሩም ሙከራዎች ሌሎች የሚጠቀሱ የግብ እድሎች ነበሩ።

በጨዋታው የመጀመርያው አጋማሽ ወደ ግብ ክልላቸው ቀርቦ ከመከላከል ባሻገር እንደ ቡድን ለማጥቃት ያልደፈሩት ደቡብ ፖሊሶች ከቆሙ ኳሶች ውጭ በክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ የጠራ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም። አበባው ቡታቆ በሁለት አጋጣሚዎች የሞከራቸው ለግብ የቀረቡ የቅጣት ምቶች እና መስፍን ኪዳኔ ከማዕዘን አሻምቶ ደስታ ጊቻሞ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት ኳስ ደቡብ ፖሊሶች ከፈጠሯቸው እድሎች መካከል ይጠቀሳሉ። በ29ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ በቀለ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያገኘው ኳስ መቶ አብዱልዓዚዝ ኬታ በቀላሉ ያዳነው ሙከራም የሚጠቀስ ነው።

በ36ኛው ደቂቃ ላይ አፈወርቅ ኃይሉ በግራ መስመር በኩል በግሩም ሁኔታ ተጫዋቾች አልፎ ያሻገረውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ በማስቆጠር ወልዋሎን መሪ ማድረግ ችሏል። ጎሉ ከተቆጠረ በኋላም በተደደጋጋሚ የደቡብ ፖሊስን ግብ የፈተሹት ወልዋሎዎች በጭማሪ ደቂቃ በአዶንጎ ሙከራ ቢያደርጉም ወደ ግብነት ሳይቀየር የመጀመርያው አጋማሽ በወልዋሎ መሪነት ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና ብዙም ሳቢ ያልሆነው የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ ሬችሞንድ አዶንጎ ላይ ያነጣጠረ ቀጥተኛ አጨዋወት ለመተግበር የሞከሩት ወልዋሎዎች በዚ አጨዋወት ጥቂት የጎል እድሎች ቢፈጥሩም ለተከላካይ መስመር ሽፋን እንዲሰጡ ከጥልቅ መስመር እንዲነሱ ከተደረጉት ሁለቱ የመሃል አማካዮች በሚነሱ ረጃጅም ኳሶች የጎል እድሎች ለመፍጠር ሞክረዋል። በተለይም ኤፍሬም አሻሞ እና የፊት አጥቂው አዶንጎ ያልተጠቀሙባቸው እድሎች በተመሳሳይ አጨዋወት የመጡ ነበሩ። ከዚ ውጭ አዶንጎ ከመስመር  በግሩም ሁኔታ  ያሻገረው ኳስ ተጠቅሞ ነፃ አቋቋም የነበረው አብዱልራሕማን ያልተጠቀመበት ኳስ ለጎል የቀረበ ነበር።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ አጥቅተው ለመጫወት የሞከሩት ደቡብ ፖሊሶችም ሁለት ያለቀላቸው የግብ እድሎች ፈጥረው ነበር። በረከት ይስሃቅ አክርሮ መትቶ ለጥቂት የወጣችው እና ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ብሩክ ኤልያስ በቢንያም ሲራጅ እና ግብ ጠባቂው ያለመናበብ ያገኛትን ኳስ ሞክሮ አብዱልዓዚዝ ኬይታ የመለሳት በደቡብ ፖሊስ በኩል አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ። የቀድሞ ክለቡን የገጠመው ብሩክ አየለ በመጨረሻው ደቂቃ ያረገው ሙከራም ደቡብ ፖሊሶችን አቻ ለማረግ ከተቃረቡት ሙከራዎች ይጠቀሳል።

ጨዋታው በወልዋሎ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ቢጫ ለባሾቹ ደረጃቸውን ወደ አስረኛ ከፍ ማድረግ ችለዋል።


የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ – LINK