ቅደመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ

ከትናንት በስትያ ጀምሮ እየተካሄዱ የሚገኙት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ መከላከያን እና ወላይታ ድቻን በሚያገናኘው ጨዋታ ይቋጫሉ። በዚህ ጨዋታ ላይ የሚነሱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

ጎንደር ላይ ከፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርቶ የተመለሰው መከላከያ ድቡብ ፖሊስን የረታውን ወላይታ ድቻን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ነገ 11፡00 ላይ ይጀምራል። ጨዋታው ሁለቱም ተጋጣሚዎች በያዝነው የውድድር ዓመት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የሚያደርጉት ሁለተኛ ጨዋታቸው ነው። ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫው ከተሰናበቱ በኋላ በሊጉም በወልዋሎ ተረተው የነበሩት መከላከያዎች ጎንደር ላይ ያሳኩት አንድ ነጥብ ወደ ተረጋጋው አጀማመራቸው እንደሚመልሳቸው ይታሰባል። ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻሉም እስከ ስምንተኛ ደረጃ ድረስ ከፍ የማለት ዕድል ይኖራቸዋል። በሊጉ ጅማሮ ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አግኝተው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ከቀጣዬቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦችን ማሳካታቸው አነናቅቷቸዋል። ነገንም በተመሳሳይ የኳኋን በድል ካሳለፉ መሪው ሀዋሳን በሁለት ነጥብ ልዩነት ከሚከተሉት ሦስት ክለቦች ጋር መስተካከል ይችላሉ።

መከላከያ አማኑኤል ተሾመ እና አቅሌሲያስ ግርማን በጉዳት ሳቢያ ለነገው ጨዋታ የማይጠቀም ሲሆን ቴዎድሮስ ታፈሰም የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ ላይ በተመለከተው የቀይ ካርድ በቅጣት የማይሰለፍበት የመጨረሻ ጨዋታው ይሆናል። በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ ኃይማኖት ወርቁ እና እርቂይሁን ተስፋዬ ከጉዳት ቢመለሱም ለነገው ጨዋታ የማይደርሱ ሲሆን ጉዳት ላይ የነበሩት ሌሎቹ ተጫዋቾች አምበሉ ተክሉ ታፈሰ እና ኄኖክ አርፌጮ ግን ማገገማቸው ታውቋል።

በጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች የተለያየ ዓይነት አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። በዚህም መከላከያ እንደተለመደው የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን በመውሰድ በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚው ሜዳ ለመግባት ሲሞክር ድቻዎች በአንፃሩ ክፍተቶችን በመዝጋት ለብቸኛው አጥቂያቸው የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚጥሩ ይታሰባል። በጦሩ በኩል ከሁለቱ አጥቂዎች ጀርባ የሚኖረው የአራቱ አማካዮች ጥምረት ነፃነት ሊኖራቸው ከሚችሉት የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች እገዛ ጋር ተዳምሮ ከድቻ የመሀል ክፍል ጀርባ ክፍተቶችን ለማግኘት የሚጥርበት የጨዋታ ሂደት በእጅጉ ወሳኝ ይሆናል። አራቱን አማካዮቻቸውን ወደ ኋላ ስበው እንደሚቀርቡ በሚጠበቁት ድቻዎች በኩል ደግሞ ኳሶች በሚቀሙባቸው ቅፅፈቶች ሁለቱን መስመሮች ባማከል ሁኔታ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ከግብ ክልሉ ርቆ ሲከላከል መረጋጋት የማይታይበትን የጦሩን የኋላ ክፍል እንደሚፈትኑ ይታሰባል። በጥቅሉ የጨዋታው እንስቃሴ ጥሩ የሚባል ፉክክር የማስተናገድ ዕድሉ የሰፋ ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነቶች እና እውነታዎች

– እርስ በእርስ በተገናኙባቸው 10 የሊግ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ 11 ግቦችን አስቆጥሮ 5 ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ከ4 አቻ ውጤቶች መመዝገብ ውጪም መከላከያ አንድ ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው 6 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

– አዲስ አበባ ላይ 5 ጊዜ ተጫውተው ድቻ ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የመከላከያ ብቸኛ ድልም አዲስ አበባ ላይ የተመዘገበ ነው።

– ባለፉት አራት የእርስ በርስ ግንኙነታቸው መከላከያ በአንዱም ጨዋታ ጎል አላስቆጠረም።

– አምና አዲስ አበባ ላይ በ17ኛው ሳምንት የተገናኑኙበት ጨዋታ ያለግብ የተጠናቀቀ ነበር።

ዳኛ

– በሦስተኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር ደቡብ ፖሊስ እና ደደቢት የተገናኙበትን ጨዋታ መርቶ ሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ያሳየው ሀብታሙ መንግስቴ በዚህ ጨዋታ ላይ በመሀል ዳኝነት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አበበ ጥላሁን – ታፈሰ ሰረካ

በሀይሉ ግርማ

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት ማሞ

ዳዊት እስጢፋኖስ

ፍቃዱ ዓለሙ – ምንይሉ ወንድሙ

 

ወላይታ ድቻ (4-1-4-1)

ታሪክ ጌትነት

እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ – ያሬድ ዳዊት

በረከት ወልዴ

ፀጋዬ አበራ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ኄኖክ ኢሳያስ – እዮብ ዓለማየሁ

አንዱዓለም ንጉሴ