ስሑል ሽረ ከሁለት ተጫዋቾች ጋር ተለያየ

በሊጉ የመጀመርያ ተሳትፎውን እያደረገ የሚገኘው ስሑል ሽረ በክረምቱ ካስፈረማቸው ሁለት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት መለያየቱ ተረጋግጧል። 

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኄኖክ ካሳሁን ቡድኑን ከለቀቁት መካከል አንደኛው ነው። በደደቢት፣ አዳማ ከተማ፣ ጅማ አባቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫውቶ ያሳለፈው ኄኖክ ወደ ሽረ ያመራው በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሲሆን በቡድኑ አመዛኝ የሊግ ጨዋታዎች ላይ ከመሰለፉ ባሻገር ሙሉጌታ አንዶም እና ሐፍቶም ቢሰጠኝ ባልተሰለፉባቸው ጨዋታዎች ላይም አምበል ሆኖ መርቷል። ተጫዋቹ ከሽረ ጋር በስምምነት ለመለያየት እንደ ምክንያት ሆኖ የቀረበው በአንዳንድ ጉዳዮች ከክለቡ ጋር በፈጠረው ልዩነት መሆኑ ታውቋል። 

ኪዳኔ አሰፋ ሌላው ከሽረ ጋር የተለያየ ተጫዋች ነው። የመስመር አማካዩ ለሦስት የውድድር ዘመናት የተጫወተበት ጅማ አባ ቡናን ለቆ በዚህ ዓመት ወደ ሽረ መምጣቱ የሚታወስ ሲሆን እንደ ኄኖክ ሁሉ ከክለቡ ጋር ባለመስማማቱ እንደተለያየ ተሰምቷል። 

ስሑል ሽረ የአንደኛው ዙር ሲጠናቀቅ በሚከፈተው የሀገር ውስጥ ዝውውር መስኮት ተጠቅሞ ቡድኑን ለማጠናከር አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማምጣት ከወዲሁ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ሰምተናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *