ሪፖርት | ባህር ዳር በሀሪስተን ሔሱ ድንቅ ብቃት በመታገዝ ከጅማ አንድ ነጥብ ይዞ ተመልሷል

ከዛሬ የ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ጅማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር እና ባህር ዳር ከተማ የተገናኙበት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ወደ አዲስ አባባ አቅንቶ ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈው ስብስብ ውስጥ ግብ ጠባቂው ዳንኤል አጄይ በግል ጉዳይ ወደ ኔዘርላንድ ማቅናቱን ተከትሎ ጉዳት ላይ የነበረው ዘሪሁን ታደለን ለማሰለፍ ሲገደድ ጉዳት አጋጥሞት የወጣው ዐወት ገብረሚካኤልን በኤልያስ አታሮ በመቀየር በ4-3-3 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብቷል። በባህዳር ከተማ በኩል ወደ ሶዶ አቅንተው ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ የተጠቀሙትን የመጀመሪያ አስራ አንድ ስብስብ ሳይቀይሩ በተመሳሳይ 4-3-3 አሰላለፍ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት።

የዕለቱ ጨዋታ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው አጋማሽ የቡድኖቹን አቋም የተለየ ገፅታ የተመለከትንበት ነበር።
በመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ጅማ አባ ጅፋሮች በተጋጣሚያቸው ላይ በጨዋታም ሆነ በሙከራ ረገድ ፍፁም ብልጫ ወስደው ነበር። ቡድኑ ለወሰደው ብልጫ መሀል ሜዳ ላይ የተሰለፉት አክሊሉ ዋለልኝ ፣ መስዑድ መሐመድ እና የይሁን እደሻው ጥምረት ትልቅ ድርሻም ነበረው። በተለይ የመስመር አጥቂዎቹ አስቻለው ግርማ እና ዲዲዬ ለብሪ የባህዳርን የተከላካይ መስመር በተደጋጋሚ እዲፈትኑ ከአማካዮቹ የሚነሱ ኳሶች አስተዋፅዖ ነበራቸው።


በ5ኛው ደቂቃ ዋለልኝ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን መስዑድ በደረቱ አቀዝቅዞ ከሳጥ ውጪ ወደ ግብ ሞክሮ ሀሪስተን እንደምንም አውጥቶበታል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አስቻለው በግራ መስመር ሁለት ተከላካዮችን አታሎ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ማማዱ ሲዲቤ ሞክሮ በድጋሜ ሀሪስትን እንደምንም ሲመልሰው ሳጥን ውስጥ የነበረው ዲዲዬ ለብሬ በድጋሚ ሞክሮ ሀሪስተን ከወደቀበት ተነስቶ በማዳን አጋጣሚው ወደ ግብነት እንዳይቀየር አድርጓል፡፡

ጥቅጥቅ ብለው የሚከላከሉት ባህርዳሮች የጅማዎችን ጫና ለመቋቋም በራሳቸው የሜዳ ክፍል ላይ የተወሰነ እንቅስቃሴ ነበራቸው። የመስመር አጥቂዎቹ ግርማ ዲሳሳ እና ወሰኑ ዓሊ ከማጥቃቱ ይልቅ ወደ ኃላ በመሳብ መከላከሉ ላይ ተጠምደውም አርፍደዋል። ይህ ደግሞ የመሀል አጥቂው ጃኮ አረፍት ብዙ ጊዜውን በጅማ ተከላካዮች መሀል እዲያሳልፍ አስገድዶታል፡፡ ከአስረኛው ደቂቃ በኃላ ጅማዎች ኳስን የማንሸራሸር ዕድሉ ቢኖራቸውም በአዳማ ሲሶኮ እና ይሁን እደሻው በተደጋጋሚ ከርቀት ካደረጓቸው ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ውጪ የባህርዳርን የተከላካይ መስመር በማለፍ የጠሩ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቆይተዋል።

በ22ኛው መሱዑድ እና አክሊሉ በአንድ ሁለት ቅብብል በቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ ካደረጉት ቅብብል መስዑድ ወደ መሀል ያሻገረውን ኳስ በአቋቋም ከሀሪሰን ፊት ለፊት የነበረው ዲደር ሊብሬ አገባ ተብሎ ሲጠበቅ ኳሱን በተቃራኒው በመግጨቱ ወደ ኃላ የመለሰው ለቡድኑ የተሻለ ዕድል ነበር። በ24ኛው ደቂቃ ዲዲዬ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው አስቻለው በግንባሩ ሲሞክር ሀሪስተን በጥሩ ብቃት ግብ ከመሆን ሲያድነው የተመለሰውን ኳስ ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል። በ35ኛው ደቂቃ ደግሞ የጅማዎችን የመሀል ሜዳ በጥሩ ብቃት ሲመራ የነበረው መስዑድ በግምት ከ35 ሜትር ርቀት በባህር ዳር ተከላካዮች መሀል ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ አስቻለው ግርማ ለሀሪስተን ያሳቀፈበት አጋጣሚም ግልፅ እና የሚያስቆጭ ነበር ፡፡

በ45ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ይሁን ያሻገረውን ኳስ አስቻለው ሞክሮት ሀሪስተን ቢመልሰውም በብዛት በአቋቋም ችግር በርካታ አጋጣሚዎች ያለፉት የነበረው እና በዚህ ቅፅበት በቅርብ ርቀት የነበረው ማማዱ ሲድቤ አስቆጥሮ ጅማዎች 1-0 መምራት ችለዋል። ባህር ዳሮች ማማዱ ከጨዋታ ውጪ ነው በማለት ቅሬታ ያሰሙ ሲሆን ጨዋታውም በዚሁ ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ በተቃራኒው ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበራቸው የበላይነት በባህር ዳሮች የጨዋታ ብልጫ ተተክቷል። ባለሜዳዎቹ በእቅስቃሴም ሆነ በትንፋሽ ወርደው ታይተዋል። በ49ኛው ደቂቃ ደረጀ መንግስቱን በዳግማዊ ሙሉጌታ ከቀየሩ በኃላ በመስመር የማጥቃት አማራጫቸውን በማድረግ ግርማ ዲሳሳ እና በወሰኑ ዓሊ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒው ወደ ፊት በሚሄዱበት ጊዜ የአባ ጅፋር ተከላካይ መስመር መረጋጋት ተስኖት ይታይ ነበር። አጥቂው ጃኮ አረፋትም ወደ መሀል በመሳብ ከኳስ ውጪ የሚያደርገው እቅስቃሴ የጅማን ተከላካይ ሲረብሽ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩን ቦታውን እንዲለቅ እና መላኩ ወልዴን በማገዝ ጃኮን ማርክ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት የቀኝ ተከላካይ ክፍሉን ክፍት እንዲሆን አድርጎታል። በዚህም የተገኘውን ክፍተት በመጠቅም በ58ኛው ደቂቃ በግራ መስመር ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ግርማ ዲሳሳ ከኤልያስ አህመድ የተሰጠውን ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት ቀጥታ ዘሪሁን ታደለ ፊት ለፊት እኪደርስ ኳስን ለማስጣል የተጠጋው የጅማ ተከላካዮች ባለመኖራቸው የገኘውን አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ባህር ዳርን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡


ከግቡ መቆጠር በኃላ በመልሶ ማጥቃት ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በተደጋጋሚ ወደ ጅማ ግብ ክልል መድረስ የቻሉት ባህር ዳሮች በ66ኛው ደቂቃ ወሰኑ ዓሊ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ዘርይሁንን ጨርፎ በግቡ ቋሚ ሲመለስ ከ70ኛው ደቂቃ በኃላ ጨዋታው በጉሽሚያ እና በተደጋጋሚ የዳኛ ፊሽካ ሲቆራረጥ ታይቷል። ጅማዎች በሜዳቸው እንደመጫወታቸው መጠን አጥቅተው መጫወት ሲኖርባቸው በአሰልጣኞች በኩል የተደረጉት ቅያሪዎች ውጤታማ አልነበሩም። ጥሩ በመቀሳቀስ ዕድሎችን እየፈጠረ በነበረው በመስዑድ ምትክ የመከላከል ባህሪ ያለው ንጋቱ መግባቱ እንዲሁም ጥሩ ኳስ ሲያደራጅ የነበረው ይሁንን ቀይሮ በመግባት ኳስ ሳይነካ ጨዋታው የተጠናቀቀው ቢስማክ አፒያ ቅያሪ ጅማ አባ ጅፋር ከዕረፍት መልስ ለተወሰደበት ብልጫ በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ጅማዎች ከእረፍት መልስ ከፈጠሯቸው የግብ ዕድሎች መካከል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በማማዱ ሲዲቤ ሁለት ሙከራዎች አድርገው በሀሪስተን ድንቅ ብቃት ተመልሶባቸው ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *