ወልዋሎ በውድድር ዓመቱ ከሽረ በድል የተመለሰ የመጀመርያው ቡድን ሆኗል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ሽረ ላይ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባለሜዳው ስሑል ሸረን 1-0 በመርታት ወደ ድል ተመልሷል፡፡

ሽረ ባሳለፍነው ሰኞ ደደቢትን ከረታው ስብስባቸው የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በጅላሎ ሻፊ እና ኢብራሂማ ፎፋና ምትክ ሳሙኤል ተስፋዬ እና ሸዊት ዮሐንስን ሲጠቀሙ ወሎዋሎዎች በበኩላቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳቸው ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ አብዱራህማን ፉሴይኒን በኤፍሬም አሻሞ ምትክ በአሰላለፋቸው አካተዋል።

ተመጣጣኝ እና እጅግ ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ የነበሩት ወልዋሎች 30ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የጨዋታውን የማሸነፊያ ግብ አግኝተዋል፡፡ ከብርሀኑ አሻሞ ኳሷን የነጠቀው የሽረው አብዱሰላም አማን ወደ ራሱ የግብ ክልል ለግብ ጠባቂው ሐብቶም ቢሰጠኝ አቀብሎት ሐብቶም በእግሩ ለማውጣት ሲሞክር ኳሷ እዛው ግብ ክልል ውስጥ አየር ላይ በመቅረቷ ከግቡ ትይዩ የነበረው ሪችሞንድ አዶንጎ ከጉዳት መልስ ግብ አስቆጥሮ ለወልዋሎ ከሜዳው ውጭ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስገኝቷል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አስገራሚ ክስተት ተስተናግዷል። በዚህም የወልዋሎው ግብ ጠባቂ አብዱላዚዝ ኬይታ እና ተከላካዩ ቢኒያም ሲራጅ እርስ በእርሳቸው ገና ከሜዳ ሳይወጡ ግጭት ፈጥረዋል፡፡

ለሶከር ኢትዮጵያ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን በዚህ መልኩ ሰጥተውናል፡፡

ገብረኪሮስ አማረ – ስሑል ሽረ

” ጨዋታው ደርቢ ከመሆኑ አኳያ ጫና ይበዛበታል ብለን አስበን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው፡፡ በጣም ተጭነን ነበር የተጫወትነው፡፡ በመጀመሪያው አርባ አምስትም ነበር በጊዜ ለመጨረስ ያሰብነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ጥሩ ሊባሉ አጋጣሚዎችን አግኝተናል። በጭንቅላት ሊቆጠሩ የሚችሉ ዕድሎችን ብናገኝም በአግባቡ አልተጠቀምንባቸውም፡፡ እኛው ራሳችን ገና በጊዜ ግብ ጠባቂያችን በፈጠረው ስህተት ሊያገቡብን ችለዋል። እየመራን እረፍት ወጣን፤ ከዛ በኃላ ከእረፍት ስንመለስም ከደጋፊያችን ጋር ሆነን ተስፋ ሳንቆርጥ የኳስ ብልጫ እየወሰድን ጥሩ ኳስ ለመጫወት ችለናል። ተነሳሽነታችን ጥሩም ነበር፡፡ ግን ሰዓት እየገደሉ ጨረሱ፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን የዛሬው ጨዋታ ለኛ ውጤቱ አይገባንም፡፡

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወልዋሎ

“በጣም ጥሩ እና ጥሩ እንቅስቃሴ ነበረበት። እኛ ተጠንቅቀን የገባንበት ነበር። ምክንየያቱም ሽረ በሜዳው የመጨረሻ ጨዋታው ነው። ሁለት ከሜዳው ውጪ በቀጣይ ስለሚያደርግ የመጨረሻ የሜዳ ላይ ጨዋታው እንደመሆኑ ከበድ ሊለን እንደሚችል እናውቃለን፡፡ በሜዳው ከባድ እና ለማንም ቡድን ተሸንፎ ስለማያውቅ ተጠንቅቀን ነበር የተጫወትነው፤ ጥሩ ጨዋታ ነበር ማለት ይቻላል ትኩረት ከመስጠታችን አኳያ ፡፡ ጥሩ ኳስን የሚጫወት ቡድን ነው። የሽረ ደጋፊዎች በጣም ላመሰግናቸው እወዳለሁ ጨዋ ደጋፊ ነው፡፡ በውጤቱም ደስ ብሎኛል፡፡ በሽረ ግብ ጠባቂ ስህተት የተቆጠረች አጋጣሚ ብትሆንም ልምዳችንን ነው የተጠቀምነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *