ሪፖርት | ደቡብ ፖሊስ ሳይጠበቅ ከኢትዮጵያ ቡና ሙሉ ሦስት ነጥብ ወሰዷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመውረድ ስጋት የተጋረጠበት ደቡብ ፖሊስ ከሜዳው ውጪ ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 በመርታት የዓመቱ ሁለተኛ ድሉን አሳክቷል።

ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ሽንፈት ያስተናገዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት በጅማ አባ ጅፋር ከተረታው ቡድን በተከላካይ ስፍራ ላይ ጉዳት ባስተናገደው ተመስገን ካስትሮ ምትክ ወንድይፍራው ጌታሁንን እንዲሁም በተካልኝ ደጀኔ ምትክ ኃይሌ ገብረተንሳይን ሲተኩ በተመሳሳይ በአማካዩ ካሉሻ አልሀሰን ምትክ አጥቂው ሱሌይማን ሉክዋን በመቀየር ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል፡፡ በአንጻሩ በሳምንቱ አጋማሽ የአሰልጣኝ ቅያሬ ያደረጉት ደቡብ ፖሊሶች ባሳለፍነው ሳምንት በመቐለ በሜዳው ከተሸነፈው ቡድን ውስጥ ግብ ጠባቂያቸው ዳዊት አሰፋን በሀብቴ ከድር እንዲሁም ኤርሚያስ በላይ ፣ መስፍን ኪዳኔ እና አዲስዓለም ደበበን አስወጥተው በምትካቸው ዮናስ በርታ ፣ በረከት ይስሀቅ እና ዘላለም ኢሳያስን አስገብተዋል፡፡ 

በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከራሳቸው ሜዳ ክፍል ኳስን መስርተው ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ፤ ምንም እንኳን በደቡብ ፖሊስ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ጫና እምብዛም ባይደረግባቸውም ኳሶቹ ወደ መሀል ሜዳ ከደረሱ በኃላ ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል ፤ በአንጻሩ ደቡብ ፖሊሶች ኳስ በቁጥጥራቸው ስር ስትገባ በፍጥነት ወደ መስመር በማውጣት ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ሙከራ አድርገዋል፡፡ 

በ7ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሀንስ የተነጠቀውን ኳስ የተሻ ግዛው ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሄኖክ አየለ ያመከናት  የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ነበረች፡፡ በ16ኛው ደቂቃ ወንድይፍራው ጌታሁን በቀላሉ ማራቅ የሚችለው ኳስ ወደ ውጪ በመውጣቱ ደቡብ ፖሊሶች ካገኙት የማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ በኢስማኢል ዋቴንጋ ደካማ የጊዜ አጠባበቅ ታግዞ ዘሪሁን አንሼቦ ነጻ አቋቋም ላይ ሆኖ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ፍፁም የሆነ የጨዋታ በላይነትን ወስደው መጫወት ችለዋል ፤ ነገር ግን በ23ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ሳምሶን ጥላሁን ባጋጠመው ጉዳት የተነሳ በዳንኤል ደምሴ ተቀይሮ ከሜዳ ሊወጣ ተገዷል፡፡

ያልተጠበቀ ግብ በማስተናገዳቸው ጫና ውስጥ የገቡ የሚመስሉት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ጫናውን በሚያሳብቅ መልኩ በርካታ ግላዊ የሆኑ የቅብብል ስህተቶችን ሲሰሩ ተስተውሏል፡፡ ያም ቢሆን ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች በ26ኛው ደቂቃ ኃይሌ ገ/ተንሳይ ከመሀል ያሻማውን የቅጣት  ምት ሱሌይማን ሎክዋ በደረቱ አውርዶ ሊመታ ሲል ወንድይፍራው ቀድሞ ደርሶ ወደ ግብ የላከው ኳስ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት በኢትዮጵያ ቡና በኩል የተደረገ የመጀመሪያው ሙከራ ነበር፡፡ በ30ኛው ደቂቃ ከሁለቱ አጥቂዎች ሎክዋና የኃላሸት ጀርባ የተሰለፈው አቡበከር ናስር በጥልቀት ወደ ኃላ ተስቦ ያስጀመረውን ኳስ ኃይሌ ከቀኝ መስመር ሲያሻማ  አቡበከር በፍጥነት ደቡብ ፖሊስ ሳጥን ውስጥ ደርሶ በግንባሩ ገጭቶ የሞከራትን ኳስ የግቡ ቋሚ ሊመልስበት ችሏል፡፡


ጫና መፍጠራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ቡናዎች በ32ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደምሴ ያሾለከለትን ኳስ አቡበከር በፍጥነት ተከላካዮችን አምልጦ ወደ ግብ የሞከረው እና የደቡብ ፖሊሱ ግብ ጠባቂ ሀብቴ ከድር ያዳነበት እንዲሁም በ36ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደምሴ ከግራ ያሻማውን ኳስ አቡበከር በደረቱ ተቆጣሮ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጭ ተብሎ የተሻረበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ በ37ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ደቡብ ፖሊሶች ካገኙት የማዕዘን ምት የተገኘውን ኳስ ዮናስ በርታ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት ሳይጠበቅ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ያሳደገች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ በአንድ ደቂቃ ልዩነትም አቡበከር ናስር ከግራ መስመር የተሻገለትን ኳስ በደረቱ ተቆጣጥሮ እጅግ ማራኪ የሆነች የመቀስ ምት ግብ በማስቆጠር በሁለቱ ግቦች የተደናገጡ የሚመስሉትን የቡድኑ አባላት እና ደጋፊዎችን ተስፋ ያለመለመች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

2ለ1 እየተመሩ ከመልበሻ ቤት የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሁለተኛውን አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ መነሳሳት ነበር የጀመሩት። በተለይም በ50ኛው ደቂቃ አቡበከር ከመስመር ወደ ኃላ ያቀበለውን ኳስ የኃላሸት ከግቡ የቅርብ ርቀት ወደ ግብ የላከው ቢልከውም በቀላሉ በግብ ጠባቂው የተያዘበት እንዲሁም በ59ኛው ደቂቃ ኃይሌ ከግራ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት ወንድይፍራው አግኝቶ ወደ ግብ አቅጣጫውን ቢያስቀይራትም አቡበከር ለጥቂት ሳይደርስባት የባከነችው ኳስ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከጅምሩ አንስቶ ወደ ኃላ ማፈግፈግን ምርጫቸው ያደረጉት ደቡብ ፖሊሶች ለተጋጣሚያቸው ጥቃት ተጋልጠዋል። ነገር ግን በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነው ሲጫወቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ይህን ጫና ለመቋቋም እንደተቸገሩ በሚያሳብቅ መልኩ በተቃራኒ የግብ ክልል ሲቃረቡ የሚሰጡት ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ጨዋታውን ይበልጥ አክብዶባቸዋል፡ የኃላሸት ፍቃዱ ፣ ቃልኪዳን ዘላለም እና ፍፁም ጥላሁንም ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች በተለይ የደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾች በተደጋጋሚ እየወደቁ ሰዓት ለማባከን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። እስከመጨረሻው ደቂቃ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ቡናዎች በ91ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ቃልኪዳን ዘላለም ከደቡብ ፖሊስ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ በቀጥታ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡ አግዳሚ ሊመልስበት ችሏል፡፡ ጨዋታው በደቡብ ፖሊሶች የ2ለ1 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና ለሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ሽንፈት ሲያስተናግድ በአንጻሩ ላለመውረድ እየታገሉ የሚገኙት ደቡብ ፖሊሶች የዓመቱ ሁለተኛ ድላቸውን አስመዝግበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *