የአሰልጣኞች አስተያየት | ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 ፋሲል ከነማ

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በስተመጨረሻ የተደረገው የጊዮርጊስ እና ፋሲል ጨዋታ 1-1 የተጠናቀቀ ሲሆን የክለቦቹ ዋና አሰልጣኞችም ጨዋታውን አስመልክቶ ተከታዮቹን አስተያየቶች ሰጥተዋል።

” ወደዚህ የመጡት ነጥብ ለመጋራት ነው” ስትዋትር ሀል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታውን ለማሸነፍ ስንሞክር የነበርነው እኛ ብቻ ነን። ወደዚህ የመጡት ነጥብ ለመጋራት ነው። በሁለተኛው አጋማሽ ግብ ጠባቂያችን አንድም ኳስ አልተሞከረበትም ፤ ምክንያቱም ለማጥቃት አልሞከሩም። እኛ ሦስት እና አራት አጋጣሚዎችን ፈጥረን ኳስ በመሆኑ ሳንጠቀም ቀርተናል። በውጤቱ ብበሳጭም በተጫዎቾቼ ግን በፍፁም ቅር ልሰኝ አልችልም። የሚገርም መነሳሳት እና የአሸናፊነት መንፈስ ነበራቸው። ስለዚህ እነሱን በፍፁም አልወቅስም። በሁለተኛው አጋማሽ ምርጥ እግር ኳስ ተጫውተናል። በመጀመሪያው አጋማሽ አጥቂዎቻችን በነሱ ተከላካዮች እና ተከላካይ አማካዮች መሀል ተይዘው ነበር ፤ ከዕረፍት መልስ ግን የኳሱን ፍጥነት ጨምረናል እነሱም የተሻለ ነፃ ሆነዋል ሙከራዎችንም አድርገናል። የተሻጋሪ ኳሶቻችን ጥራት ቢስተካከል ደግሞ የተሻለ ይሆን ነበር።”

ስለተጋጣሚያቸው አቀራረብ

“ቡድኖች ወደዚህ ይመጡ እና በ4-3-3 ጨዋታውን ይጀምራሉ ፤ ከዛም ከኳስ ውጪ ወደ 4-5-1 ይሄዳሉ በጥልቀትም ይከላከላሉ በመውደቅ ሰዓት ለመግደልም ይሞክራሉ። ለተጫዋቾቼ የጭንቅላት ጉዳት ካልሆነ በቀር የተጋጣምሚ ተጫዋቾች ሲወድቁ ጨዋታቸውን እንዲቀጥሉ ነግሬያቸው ነበር። ”

” ሳላዲን እና አቤልን የመሰሉ አጥቂዎች ይዞ ከዚህ በላይ ገልበን እንድንጫወት አስቦ ከሆነ ራሱን ነው መጠየቅ ያለበት” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ውጤቱን ከዕቅዳቸው አንፃር እንዴት እንደተመለከቱት

” አቅደን የመጣነው ጨዋታውን አሸንፈን ለመመለስ ነው። ተስተካካይ ጨዋታዎች ቢኖሩንም ቅዱስ ጊዮርግስ መሪ በመሆኑ ካላሸነፍን በፉክክሩ ውስጥ መቆየት እንደማንችል እናውቅ ነበር ፤ ስለዚህ ነጥብ ይዘን ለመመለስ ነበር ፍላጎታችን። ሀሳባችን ባይሳካም በውጤቱ ብዙም አልተከፋውም። ”

በስትዋርት ሀል አስተያየት ዙሪያ

“አሰልጣኙ በኔ መልበሻ ክፍል ውስጥ አልነበረም ይህን በምን ሊያውቅ ይይችላል?የአጨራረስ ጉዳይ እንጂ ከነሱ በተሻለ ብዙ ወደ ግብ የደረስነው እኛ ነበርን። በርግጥ ሳላዲን እና አቤልን የመሰሉ አጥቂዎች ይዞ ከዚህ በላይ ገልበን እንድንጫወት አስቦ ከሆነ ራሱን ነው መጠየቅ ያለበት። ፍላጎታችን የነበረው ማሸነፍ ነው ግብ በማግባትም ቀዳሚ የነበርነው እኛ ነን። የገባብንም በትንሽ ስህተት ነበር። ከዛ ውጪ ከእረፍት በፊት አንድ የግብ ሙከራ ነው የነበራቸው። በሚዲያ ፊት ተጋጣሚን ዝቅ ማድረግ ግን ደስ የሚል ነገር አይደለም። በርግጥ በሁለተኛው አጋማሽ በነበረን አቀራረብ ወደ ኋላ ተስበን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነበር ሀሳባችን ፤ የነጥብ ልዩነቱ እንዲሰፋ መፍቀድ ስላልነበረብን። መከላከል በራሱም አንድ የጨዋታ አካል ነው። ምህረት የሌላቸው ፈጣን አጥቂዎች እያሏቸው ሰፊ ክፍተት ለነሱ መስጠትም አልነበረብንም። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *