አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በዱራሜ የእግር ኳስ አካዳሚ በመጎብኘት ድጋፍ አድርገዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ዱራሜ ከተማ በመገኘት በስፍራው የሚገኘው የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከል የጎበኙ ሲሆን ለታዳጊዎቹ የማነቃቂያ ንግግር እንዲሁም የቁሳቁስ ድጋፍን አድርገዋል፡፡

በከንባታ ጠምባሮ ዞን ስር ከሦስት ዓመታት በፊት የተከፈተው እና በ6 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው  የዱራሜ የታዳጊዎች የእግር ኳስ አካዳሚ በቀጣዮቹ ዓመታት ተስፈኛ ወጣቶችን ለማግኘት ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል። የስልጠና ማዕከሉ በቅርቡ ሙሉ የግንባታ ሂደቱን የሚጀምር ሲሆን የሴቶች እና የወንዶች የመኝታ ክፍሎች፣ መመገቢያ አዳራሾች እንዲሁም ከስልጠናው ባሻገር እዛው ሊማሩ የሚችሉበትን የትምህርት ተቋም ግንባታም ያጠቃለለ ነው ተብሏል።

በአሁኑ ሰዓት ግንባታው እስከሚጀመር እና በሙሉ ወደ ስራ እስከሚገባ ድረስ የከተማ አስተዳደሩ የሰጠው የመጫወቻ ሜዳን በመጥረግ ታዳጊዎቹ ልምምዳቸውን በከፊል መጀመር ችለዋል፡፡ እድሜያቸው ከ13-15 የሚሆኑ 60 ወንዶች እና 20 ሴቶችን በመያዝ በተመደቡ አሰልጣኞች ልምምድ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከወዲሁም ዞኑን ወክለው የሚጫወቱ 8 ሴት ተጫዋቾች አበርክቷል፡፡ አካዳሚውን በቴክኒኩ ረገድ እንዲታገዝ  በማሰብ በዞኑ ውክልና ተሰጥቶት የካፍ ኢንትራክተር አንተነህ እሸቴ በመምራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህን አካዳሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በስፍራው በመገኘት ለታዳጊዎቹ አበረታች ንግግር እና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ አሰልጣኝ አብርሀም ድጋፉን ካደረጉ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት “እንደዚህ አይነት አካዳሚዎችን ማበረታታት ያስፈልጋል። እርግጠኛ ነኝ ዱራሜ ውስጥ እንዲህ አይነት አካዳሚ አለ ብሎ የሚያስብ የለም። መጥተህ ስትመለከት ግን በጣም ትገረማለህ። ለእግር ኳሱ እድገት ትልቁ ሀብት ሜዳ ነው፡፡ አካዳሚ ለመገንባትም ቢሆን ሜዳ በብዛት ያላቸው ክልሎች እና ዞኖች በደንብ ሊያስቡበት ይገባል። ” ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በአዲስ አበባ የጀመሩት አካዳሚዎችን የመጎብኘት እና የስራ መመሪያዎችን የመስጠት ተግባርን በመቀጠል በየክልሉ እየተዟዟሩ ለመመልከት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ በስተመጨረሻም የዞኑ ኃላፊዎች በተገኙበት ለአሰልጣኙ የማስታወሻ ሽልማቶችን ያበረከቱ ሲሆን ለተደረገላቸው አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *