ሴቶች 1ኛ ዲቪዚዮን | ንግድ ባንክ በሰፊ ጎል አሸንፎ ወደ መሪነቱ ተመልሷል


የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 13ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ አምስት ጨዋታዎች ሲቀጥል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ መሪነት የተሸጋገረበትን፣ ኤሌክትሪክ በመሳሳሉ የገፋበትን ድሎች አስመዝግበዋል። አዳማ እና መከላከያ ደግሞ ከሜዳቸው ውጪ ነጥብ ጥለዋል።

የአአ ስታድየም ውሎ

(በዳንኤል መስፍን)

ብዙም የሚስብ እንቅስቃሴ ባለተመለከትንበት 09:00 ጨዋታ ኤሌክትሪክ ጥረትን 1-0 አሸንፏል። በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች ውስጥ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሁለት አጋጣሚ ወርቅነሽ መልመላ ከሳጥን ውጭ የግብ ዕድል እንደመፍጠሯ ጨዋታው ተጋግሎ ይቀጥላል ተብሎ ተገምቶ ነበር። ሆኖም ምንም የተሳካ የጎል ሙከራም ሆነ ሳቢ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሳንመለከት ለግማሽ ሰዓት ያህል ቀጥሏል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለአጥቂዎች በተሻለ የጎል አጋጣሚዎች መፍጠር የሚያስችሉ ኳሶችን አማካይ ክፍሎች የሚያደርስ አለመኖሩ አጥቂዎች በተደጋጋሚ ከሳጥን ውጭ ኳሶችን በመመታት የጎል ሙከራ ሲፈጥሩ ተመልክተናል።

ለዚህም ማሳያ በጥረት በኩል 29ኛው ደቂቃ እየሩሳሌም ተሾመ፣ እንዲሁ 36ኛው ደቂቃ ትዕግስት ወርቁ ከሳጥን ውጭ የፈጠሩት የግብ ዕድል ሲጠቀስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል መሳይ ተመስገን ተከላካዮችን በማለፍ 44ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ የፈጠረችው የጎል አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን 34ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌትሪክ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅማ የጥረቷ አጥቂ ትመር ጠንክር ነፃ ኳስ ከግብጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ሳትጠቀም የቀረችው ኳስ የሚያስቆጭ ነበር።

ከእረፍት መልስ ጥረቶች ኳሱን ተቆጣጥረው የግብ ዕድል ለመፍጠር በተሻለ ሁኔታ ወደፊት በመሄድ ጫና ፈጥረው እየተጫወቱ ባለበት ሂደት 68ኛው ደቂቃ የመስመር አጥቂ ዓለምነሽ ገረመው ተቀይራ ከገባችው ሜሮን አብዱ በጥሩ መንገድ የተሰጣትን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይራ ኢትዮ ኤሌትሪኮችን ቀዳሚ ማደረግ ችላለች። ጥረቶች ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተደጋጋሚ ወደ ፊት ቢሄዱም ምንም መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በሁለተኛው ዙር መሻሻልን እያሳዩ የሚገኙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት ያደረጉት መከላከል ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 1 – 0 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል።

የ11:00 የአዲስ አበባ ስቴዲየም ሁለተኛ ጨዋታ በባንክ 7-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ እንስቶች ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት የሚያደርጉት ጥረት በጎል ሙከራ ያልታጀበ መሆኑ የጨዋታው ደቂቃ በገፋ ቁጥር የመውረድ ሁኔታ እንዲታይባቸው አድርጓቸዋል። ንግድ ባንኮች ጨዋታውን በጥንቃቄ በመቆጣጠር በተለይ በዛሬው ጨዋታ የመስመር አጥቂነት ሚና የተሰጣት ቡርቱካን ገብረክርስቶስ የምትፈጥረው የግብ ዕድል ስኬታማ ነበር። 23ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተመታውን ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊስዋ ተከላካይ አበዛሽ ሜጊሶ በራሷ ጎል ላይ አስቆጥራ ንግድ ባንኮች ቀዳሚ መሆን ቻሉ። በመጀመርያው ጎል የተነቃቁት ንግድ ባንኮች ብዙም ሳይቆዩ 26ኛው ደቂቃ ረሂማ ዘርጋው ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት የሰጠቻትን ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ተረጋግታ ሁለተኛ ጎል አስቆጥራለች።

የንግድ ባንክን አጨዋወት መቆጣጠር ጊዮርጊሶች መቋቋም የተሰመናቸው ሲሆን 29ኛው ደቂቃ ሌላ ጎል መሆን የሚችል ዕድል ብርቱካን ገብረ ክርስቶስ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ይሁን እንጂ 36ኛው ብርቱካን በጥሩ መንገድ ያቀበለቻትን ረሂማ ዘርጋው የግል ብቃቷን ተጠቅማ የንግድ ባንክን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ ችላለች። የንግድ ባንክ የበላይነት ጎልቶ እየታየ በቀጠለበት በዚህ ጨዋታ 42ኛው ደቂቃ በአንድ ሁለት ቅብብል በመግባት በብዙነሽ ሲሳይ አማካኝነት አራተኛ ጎላቸውን አስቆጥረዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ክፍል ላይ ያመሹት ንግድ ባንኮች ሌሎች ጎል ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን ብርቱካን እና ረሂማ ዘርጋው ሳይጠቀሙ ቢቀሩም 62ኛው ደቂቃ ላይ ብዙዓየሁ ታደሰ የቀድሞ ክለቧ ላይ ከሳጥን ውጭ ግሩም ጎል አስቆጥራ የጎል መጠኑን አምስት ስታደርስ በ65ኛው ደቂቃ በህይወት ደንጊሶ ቄንጠኛ ጎል አስቆጥረው የግብ መጠናቸው ወደ ስድስት ከፍ አድርገዋል።

ከስድስተኛው ጎል በኋላ ጨዋታው ቀዝቀዝ ያለ መልክ ሲይዝ 81ኛው ደቂቃ ላይ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ያቀበለቻትን ረሂማ ዘርጋው በአግባቡ ተጠቅማ ለቡድኗ የማሳረጊያ ለራሷ ሁለተኛ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው 7-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ 1-1 አዳማ ከተማ

(በቴዎድሮስ ታከለ)

ሀዋሳ ላይ የሊጉ መሪ ሆኖ ሀዋሳ ከተማን የገጠመው አዳማ ከተማ ለረጅም ደቂቃ ያህል ሲመራ ቆይቶ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረበት ግብ ነጥብ ተጋርቷል። ጥሩ አጀማመር ባልተስተዋለበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ለመድረስ ቢቸገሩም አዳማ ከተማዎች በሁሉም ረገድ ተሽለው የታዩበት ነበር። በተለይ በመስመር በኩል ሜዳውን ወደ ጎን ለጥጠው ከእፀገነት እና ሰርካለም በሚነሱ ኳሶች ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል። 13ኛው ደቂቃ እፀገነት ብዙነህ ስታሻማ ሴናፍ ዋኩማ አክርራ የመታችውን የሀዋሳ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት አጋጣሚ  ቀዳሚ ሙከራ ነበረች፡፡ በሀዋሳዎች በኩል በመጀመሪያው ዙር ሀዋሳን ማገልገል ሳትችል ቀርታ የነበረችው መሳይ ተመስገን ከሁለቱም መስመሮች እየገባች ጥሩ እንቅስቃሴ ብታደርግም ኳሶቹ በቀለሉ ሲባክኑ ተስተውሏል። 18ኛው ደቂቃ ላይ ሳራ ኬዲ ከርቀት መትታ ወደውጭ የወጣባት ኳስ በሀዋሳ በኩል የምትጠቀስ ጠንካራ ሙከራ ነበረች።

በ23ኛዉ ደቂቃ በግምት 30 ሜትር ርቀት ላይ  የተገኘውን የቅጣት ምት አማካይዋ  አልፊያ ጃርሶ በአግባቡ በመጠቀም የሀዋሳ ግብ ጠባቂ አባይነሽ ኤርቀሎ ስህተት ታክሎበት አዳማን መሪ ማድረግ ችላለች፡፡ ከግቧ በኋላ ተጭነው ለመጫወት ሙከራን ያደረጉት ሀዋሳዎች ሁለት አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻሉም፤ 32ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን ከሜዳው አጋማሽ በረጅሙ ወደ ግብ የላከችውን ኳስ አረጋሽ ጋር ደርሶ ለመቅደስ አቀብላት በቀላሉ ያመከነችሁ እንዲሁም 36ኛው ደቂቃ ምርቃት ከነፃነት ጋር በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ክልል ገብተው ነፃነት በቀላሉ ያመከነቻቸው ኳሶች የሚጠቀሱ መከራዎች ናቸው፡፡

በሁለተኛዉ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳዎች በአዳማ ላይ ብልጫን ማሳየት የቻሉበትን እንቅስቃሴ ማሳየት ሲችሉ አዳማዎች የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን በመጠኑም ቢሆን ለመሞከር ጥረት አድርገዋል፡፡ ገና ወደ ሜዳ ከገቡ ሁለት ደቂቃን እንዳስቆጠሩ ሀይቆቹ  ከመሀል ወደ ቀኝ መስመር ነፃነት መና ያሻገረችላትን ኳስ ምርቃት ፈለቀ ወደ ግብነት ለወጠችሁ ሲባል በቀላሉ ኳሰን አስረዝማ በመግፋቷ ሊወጣባት ችሏል፡፡ ግብ ለማስቆጠር በተለይ አማካይ ክፍሉ ላይ መቅደስ ማሞን እና ወርቅነሽ መሰለን አስወጥተው እታለም አመኑንና ቅድስት ቴካን ወደ ሜዳ ካስገቡ በኃላ በአማካይ ክፍሉ ላይ የነበረባቸውን ድክመት ያረሙት ሀዋሳዎች ቶሎ ቶሎ ወደ አጥቂዎች ኳስን በማድረስ ለአዳማ የተከላካይ ክፍል ፈተና ሆነዋል። 60ኛዉ ደቂቃ ተከላካይዋ ቅድስት ዘለቀ ከሳጥን ዉጭ አክርራ የመታችዉ እና አግዳሚውን ለትሞ የተመለሰው እና 72ኛዉ ደቂቃ መሳይ ተመስገን  ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ ልካ የአዳማዋ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ይርጋሽዋ በግሩም ሁኔታ አውጥታባታለች፡፡ ከመጀመሪያው አጋማሽ ደከም ብለው የገቡት አዳማዎች ከመልሶ ማጥቃት 85ኛዉ ደቂቃ ላይ ሳራ ነብሶ ሴናፋ ዋኩማ አመቻችታ ብታቀብላትም ነፃ የማግባት እድሏን ኳስ ከእግሯ አምልጦ በመውጣቱ ምክንያት ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ የጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ነፃነት መና ከመሀል የሜዳው ክፍል ወደ ግራ በኩል የጣለችውን ኳስ በግሩም አጨራረስ ተከላካይዋ አረጋሽ ፀጋ ሀዋሳን አቻ ማድረግ ችላለች፡፡ ሀዋሳዎች የመጨረሻ የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ላይም ስንታየው ማቲዎስ ከግብ ጠባቂዋ እምወድሽ ጋር ተገናኝታ ያመከነችዉ ግብ ሀዋሳ አሸንፎ ሊወጣ የሚችልበት አጋጣሚ የነበረች ብትሆን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ዲላ ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ጌዲኦ ዲላ ያለ ግብ ጨዋታውን ሲያጠናቅቅ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከመከላከያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል። ለድሬዳዋ አይዳ ዑስማን 33ኛው ደቂቃ ላይ ቡድኗን መሪ ብታደርግም ከአስር ደቂቃዎች በኃላ አረጋሽ ከልሳ መከላከያን አቻ ያደረችዋን ግብ ከመረብ አዋህዳለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *