“የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድንን ጥያቄ በድጋሚ ለመቀበል አላቅማማም” ናኦል ተስፋዬ

ውልደቱ እና እድገቱ ስዊድን ነው፤ የ15 ዓመቱ የመስመር ተከላካይ ናኦል ተስፋዬ። ባለፈው ዓመት ከማንቸስተር ሲቲ እና ሊድስ ዩናይትድ ጋር ስሙ ሲነሳ የነበረው ይህ ተጫዋች በቀድሞ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ አግባቢነት መጥቶ ስለተሳተፈበት የሴካፋ ዋንጫ እና ስለ ቀጣይ እግር ኳስ ህይወቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በሴካፋ የነበረህ ቆይታ ምን ይመስል ነበር?

ሴካፋ ላይ መሳተፍ በተለይም ለኔ ጥሩ ልምድ ነበር። የአፍሪካ እግር ኳስ የአጨዋወት ዘይቤን ለማየት እና ከአውሮፓ አንፃር ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አይቼበታለሁ። ሆኖም ጉዳት ነበረብኝ። ከዛ ውጭ በጣም አሪፍ ነበርን፤ እስከ ፍፃሜ ደርሰን በዩጋንዳ ነው የተሸነፍነው። በዛ ውድድር ሁለተኛ መውጣት ግን ትልቅ ስኬት ነበር። የሴካፋው ዋንጫ አንስተን ወደ አፍሪካ ዋንጫ አለማለፋችን ግን በጣም ነው የሚያስቆጨው።

ባለፈው ዓመት ስምህ ከትላልቅ የአውሮፓ ክለቦች ይነሳ ነበር። ጉዳዩ የት ደረጃ ደረሰ?

እኔ እግር ኳስ ላይ ብቻ ነው ማተኮር የምፈልገው።
በወኪሎቼ ሙሉ እምነት አለኝ። በሚፈልጉኝ ክለቦች ዙርያ ያለኝን ፍላጎት ገልጬላቸዋለው። በዛ ላይ እኔ ገና 15 ዓመቴ ነው። በፊፋ ህግ ከ16 ዓመት በታች ዕድሜ ያለው ተጫዋች ማስፈረም አይፈቀድም።

አሁን በምን ደረጃ ትገኛለህ?

አሁን በዝውውር ሂደት መሃል ነው ያለሁት። እዚ ስዊድንም፤ ከሀገር ውጭ ያሉት ክለቦች ጋርም እየተነጋገርን ነው። በቅርቡ አንድ ክለብ እቀላቀላለው ብዬ አስባለው። በርካታ የተመለከቱኝ ፈላጊ ክለቦች አሉ። ጉዳዩ ሂደት ላይ ነው።

ቀጣይ በዋና ቡድን ምርጫህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነው ወይስ የስዊድን ?

ከስዊድን እና ኢትዮጵያ አንዱን መምረጥ ከባድ ነው። ግን በቀጣይ ያለውን አማራጭ በደምብ ካየው እና ለኔ ጥሩ ነገር ካላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጥያቄ በድጋሚ ለመቀበል አላቅማማም፤ በጠቃላይ ግን የሚመጣው ነገር ወደፊት ማየት ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *