ወላይታ ድቻ አሸናፊ በቀለን በዋና አሰልጣኝነት ቀጠረ

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የአሰልጣኝ ቅጥር በማውጣት ሲያወዳድር የቆየው ወላይታ ድቻ አሸናፊ በቀለን በዋና አሰልጣኝነት ሾመ።

ከአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ጋር ቀሪ የስድስት ወራት ኮንትራት እየቀራቸው በስምምነት የተለያዩት ድቻዎች ከአሰልጣኙ ስንብት በኋላ በምክትል አሰልጣኙ ደለለኝ ደቻታ እየተመሩ ቅዱስ ጊዮርጊስን የመጀመሪያውን ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ድል ማድረጋቸው ይታወሳል። ከአንደኛው ዙር ፍፃሜ በኋላ ክለቡ ባወጣው የአሰልጣኝነት ቅጥር ማስታወቂያ መሠረት ከተወዳደሩት አስራ አምስት አሰልጣኞች ያለፉትን ሁለት ሳምንታት ሲፎካከሩ ቆይተው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በከፍተኛ ውጤት የክለቡ ዋና አሰልጣኝ በመሆን መሾማቸውን አቶ አሰፋ ሆሲሶ የወላይታ ድቻ ስራ አስኪያጅ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በመልቀቅ በኤሌክትሪክ ያልተሳካ ዓመትን በማሳለፍ ክለቡ ወደ ከፍተኛ ሊግ ከወረደ በኋላ የለቀቁት አሰልጣኝ አሸናፊ ያለፉትን አምስት ወራት ካለ ክለብ ከቆዩ በኋላ እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በወላይታ ድቻ በዋና አሰልጣኝነት ይዘልቃሉ፡፡ የቀድሞው የባንክ፣ መከላከያ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ አሰልጣኝ የቡድኑን አቋም በማሻሻል ከወራጅነት ስጋት የማላቀቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል።

በተያያዘ ወላይታ ድቻ ለመሀል ተከላካዩ እርቅይሁን ተስፋዬ ከአቋም መውረድ ጋር በተያያዘ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤን ሰጥቷል፡፡ በቅርቡ ከአንድ ተጫዋች ጋር የተለያየው ክለቡ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ እና በቀጣይ ችግር ጎልቶ ለሚታይባቸው ተጫዋቾች ተመሳሳይ ርምጃን ሊወስድ እንደሚችልም ሰምተናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *