ሲዳማ ቡና ቅሬታ አቀረበ

ሲዳማ ቡና የህዳሴው ግድብ ዋንጫ ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ ውድድሩ እንደተቋረጠ የተገለፀበት መንገድ ክለቡን ለከፍተኛ ኪሳራ የዳረገ መሆኑን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ሳሳሞ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዋንጫ ጨዋታ ለ8ኛ ጊዜ በአራት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች መካከል መካሄድ ከጀመረ በኋላ የአዳማ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ መጠናቀቅን ተከትሎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ” ይህ ውድድር በዛሬው ዕለት ተጠናቋል። ለሁሉም ተሳታፊ ቡድኖች እና ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምስጋናችንን እናቀርባለን።” በማለት የውድድሩን መቋረጥ ትላንት መግለፁ ይታወቃል።

በዚህ ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑት የሲዳማ ቡና እግርኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ሳሳሞ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ተናግረዋል ” ይህ ውድድር ትልቅ ዓላማን ያነገበ የሀገር ጥሪ መሆኑን ተቀብለን በማክበር ነው ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በዚህ ውድድር ለመሳተፍ የመጣነው። በሲዳማ ቡና እና በኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በሁለቱ ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረ ምንም አይነት ግጭት የለም። ጨዋታውን እስከ መጨረሻው እንደምንጫወት ጠብቀን ሳለ ምክንያቱ ባልተገለፀ ሁኔታ ጨዋታው ተቋርጧል። እናመሰግናለን ተብለን መበተኑ ለክለቡም ሆነ ይህን ዓላማ አክብሮ ለመጣ ደጋፊዎቻችን ትልቅ ኪሳራ ነው። በማንኛውም መልኩ ይህ ውድድር የህፃናት ጨዋታ አይደለም። ውድድር ሳይጠናቀቅ ምን ዓላማ አሳክተን እንደመጣን ሳይታወቅ በማናቀው ሁኔታ ውድድሩ መቋረጡ የተሰማንን ከፍተኛ ቅሬታ እየገለፅን እስካሁን ውድድሩ እንደተቋረጠ የደረሰን መረጃ የለም። የደረሰብንንም ኪሳራ ማንን እንደምንጠይቅ አናውቅም።” በማለት ተናግረዋል።


ለ8ኛ ጊዜ በተደረገው በዚህ ውድድር አወዳዳሪው አካል አስቀድሞ በመርሐግብር አወጣጥ ላይ ችግር የነበረበት ከመሆኑም በላይ በሲዳማ ቡና እና በኢትዮጵያ ቡና መካከል በተካሄደው ጨዋታ በደጋፊዎች መካከል የተፈጠረውን መጠነኛ ችግር ለመፍታት የጸጥታ አካላት የወሰዱት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ ብዙ ደጋፊዎችን ለጉዳት የዳረገ ሆኖ መጠናቀቁ አሳዛኝ ድርጊት ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *