የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ ተጀመረ


በአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ለሦስት ቀናት የሚሰጠው የአሰልጣኞች ስልጠና ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አዳራሽ ተጀመረ።

ፌዴሬሽኑ በ2011 ሊተገብራቸው ካሰባቸው እቅዶቹ መካካል አንዱ የሆነው የአሰልጣኞች ስልጣና ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ መሰጠት ሲጀምር በስልጠናው ከ30 በላይ የሚሆኑ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ የፕሮጀክት ፣ የወንዶች አንደኛ እና ከፍተኛ ዲቪዚዮን አሰልጣኞች ተካፋዮች ሆነውበታል።

የዕለቱን ስልጠና በንግግራቸው የከፈቱት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ኃይለየሱስ ፍስሃ በአዲስ አበባ በሚገኙ አሰልጣኞች ዘንድ ተመሳሳይ ስልጠናዎች በሁሉም የዕድሜ እርከኖች እንዲሰጡ በመፈለግ እና አዳዲስ የተሻሻሉ የእግርኳስ ስልጠናዎችን እንዲያውቁ በማሰብ የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ስልጠና እንደሆነ ገልፀው ” ለሦስት ቀናት በሚኖራቸው ስልጠና ጠቃሚ ዕውቀት እንደምታገኙበት በማመን ስልጠናውን ለመስጠት ያላቸውን ጊዜ አጣበው ለተገኙልን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ስም ከልብ እናመሰግናለን። በቀጣይ ተመሳሳይ የሆኑ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ እናደርጋለን።” በማለት ተናግረዋል።


በመቀጠል የዛሬውን ስልጠና የሰጡት አብርሃም መብራቱ በመግቢያ ንግግራቸው “የስልጠና መርሆችን ሳናውቀው በልማድ ልምምዶች እየሰጠን ውጤት እየራቀ ፣ ትውልድ እየጠፋ ነው። የሀገራችንም እግርኳስ እየተጎዳ ነው። እውቀትን መሰረት ያደረገ ስልጠና ልንሰጥ ይገባል። በየትኛውም ዓለም የሚገኙ አሰልጣኞች ተመሳሳይ የሆነ የስልጠና መርህ ነው የሚከተሉት። ነገር ግን ልምምዱን የሚሰጡበት መንገድ እና የጨዋታ አቀራረባቸው ነው ልዩነቱ። ስለዚህ በተለምዶ ከሚሰጡ ኮፒ ከተደረጉ ዥንጉርጉር ስልጠናዎች በመውጣት ተመሳሳይ የሆኑ ስልጠናዎች መስጠት ይገባናል።” ብለዋል።

በማስከተል በተለያዩ የእግርኳስ መርሆዎች ዙርያ ለአምስት ሰዓት በንድፈ ሀሳብ እና በቪዲዮ የተደገፈ ስልጠና ለሰልጣኞች የተሰጠ ሲሆን በዋናነት በልምምድ ወቅት መሰጠት የሚገቡ መሰረታዊ የስልጠና መርሆች ላይ አተኩሯል። የፍጥነት፣ የአካል ብቃት ስልጠና እንዴት ይሰጣል? የልምምድ እቅዶች እንዴት ይዘጋጃሉ? ልምምዱ የሚሰራበት ቦታ ሜዳ፣ ልምምዱን የሚሰሩ ተጫዋቾች እነማን ናቸው? የሜዳ ላይ የምንጠቀመው ስንት ተጫዋቾች መሆን አለባቸው? እንዲሁም ስልጠናውን ለመስጠት የሰልጣኞቹ ዕድሜ፣ ልምድ፣ አቅምን፣ የተጫዋቾቹ ችሎታን ምንያህል መሆን አለበት የሚሉት ተተንትነዋል።


የሜዳ ላይ ትግበራን በተመለከተ የአሰልጣኞች እና የተጫዋቾች በግልፅ መረጃን ስለመለዋወጥ፣ የማጥቃት እና የመከላከል አሰለጣጠን፣ የተጫዋች ማርክ አደራረግ፣ የቦታ አጠባበቅ፣ ከኳስ ውጭ የሆኑ ተጫዋቾችን የመቆጣጠር ፣ በማጥቃት ጊዜ ሜዳውን ስለማስፋት እና ስለ ማጥበብ፣ በማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ኳሶች እንዳይበላሹ ስለማድረግ፣ በማጥቃት ታክቲክ የተጋጣሚ ቡድን የተደበቁ ነገሮችን ስለማውጣት፣ ጎሎች እንዲቆጠሩ ለአጥቂዎች እና ሌሎች ተጫዋቾች የመጫወት ነፃ ሚና ስለመስጠት፣ ግብጠባቂን የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ስለማስገባት፣ በአሰልጣኙና በተጫዋቾቹ መካከል ያለው እውቀት በአዕምሮ ብቻ ሳይሆን በተግባር እንዴት መገለፅ እንዳለበት ሰፋ ያሉ ትምህርቶች ስልጠናው በዛሬው ውሎ አካቷል።

በመጨረሻም የጥያቄ እና የመልስ ውይይቶች ከተነሱ በኋላ የቪዲዮ ትንታኔ ከቀረበ በኋላ የግማሽ ቀን ስልጠናው ሲገባደድ በቀሩት ሁለት ቀናት ተጨማሪ ስልጠናዎች በመስክ እና በንድፈ ሀሳብ የሚሰጥ ይሆናል።


ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ስልጠና በንድፍ ሀሳብ ትምህርቶችን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና የቴክኒክ ዳሬክተሩ መኮንን ኩሩ እንዲሁም የአካል ብቃት ስልጠናዎችን በቴክኒክ ኮሚቴው አባል አለባቸው አማካኝነት የሚሰጡ ይሆናል።

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቀጣይ መሰል የሆኑ ስልጠናዎችን ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች እንዲሁም ለሴቶች ቡድን አሰልጣኞች እንደሚሰጥ ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *