ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ አራት – ክፍል ሁለት)

በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የአራት ሁለተኛ ክፍል እንዲህ ይቀርባል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

ለ<ዉንደርቲም> ከባድ ፈተና እንደምትሆን የታሰበችው እንግሊዝ በኅዳር ወር 1932 ብሔራዊ ቡድኗን ይዛ ወደ ኦስትሪያ አቀናች፡፡ በእርግጥ በወቅቱ ብሪታኒያ የዓለም ምርጥ ቡድን ባትሆንም ለእግርኳሱ እድገት ባበረከተችው አዎንታዊ አስተዋጾኦ በበርካታ ሀገራት ዘንድ የገዘፈ ከበሬታን አትርፋ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት በሜዳዋ ባካሄደቻቸው ጨዋታዎች በአንዱም የመሸነፍ ዕጣ አልገጠማትም፡፡ ይሁን እንጂ በ1929 ስፔን በዋና ከተማዋ ማድሪድ እንግሊዝ ላይ የ7-1 ድል ስትጎናጸፍ የእግርኳስ መስራቿ ሃገር ደካማ ጎን ገሃድ ወጣ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ግን ነገሮች የተገላቢጦሽ ተጓዙና ስፓኒያርዶቹ በሃይብሪ 7-1 ተደቆሱ፡፡ የዉንደርቲም እና እንግሊዝ ጨዋታ ከመደረጉ በፊት አብዛኛዎቹ ኦስትሪያውያን ቀደም ሲል ስኮትላንድ ላይ ባሳኩት ድል ሳቢያ ከፍተኛ በሆነ የተስፈኝነት ስሜት ውስጥ ሰጠሙ፡፡ ዘወትር ሁኔታዎችን በአሉታዊ ገጽታ ለመመልከት ዝግጁ የሆነው ሜይዝል ግን ስጋት ገባውና ወደ ቀድሞ ጓደኛው እና አማካሪው ጂሚ ሆጋን ፊቱን መለሰ፡፡ 

በእንግሊዝ ነገሮች እንዳሰበው ያልሄዱለት ሆጋን በ1921 ወደ ሲውዘርላንድ አቀና፡፡ በበርን ከተማ በመጀመሪያ ከያንግ ቦይስ ቀጥሎም ከሉዛን ጋር ሶስት ዓመታትን አሳለፈ፡፡ ከዚያም ወደ ቡዳፔስት ተመለሰና በቀድሞ መጠሪያው <ኤም.ቲ.ኬ.> ሲባል ቆይቶ ኋላ ላይ <የሃንጋሪያ እግርኳስ ክለብ> በሚል ስያሜ የሚታወቀው የሃገሪቱ አንጋፋ ክለብ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ፡፡ በሃንጋሪ ጥቂት ቆይታ ካደረገ በኋላ የጀርመን እግርኳስ ፌዴሬሽንን በአማካሪነት ሊያገለግል እንዲሁም <ኤስ.ሲ. ድሬስደን>ን ለማሰልጠን ተስማምቶ ወደ ሃገሪቱ አመራ፡፡ ከዘመናት በኋላ ምዕራብ ጀርመን በ1954 የአለም ዋንጫ ባለድል ስትሆን የሴፕ ኸርበርገር ረዳት አሰልጣኝ የነበረውና በ1974 ደግሞ ራሱ በዋና አሰልጣኝነት የአለም ዋንጫ አሸናፊ የሆነው ኼልሙት ሾን በድሬስደን አንደኛው የሆጋን ሰልጣኝ ነበር፡፡ ሆጋን በቴክኒካዊ ክህሎት ያደጉ ተጫዋቾች የሚታገዝ  ውበት ያለው እግርኳስ የሚኖረው ተቀባይነት ከፍ ያለ ስለመሆኑ ሰፊ ንቃት እየፈጠረና በዚሁ የአጨዋወት ዘይቤ ላይ ጠንክሮ በመስራት የእንግሊዝ እግርኳስ በሌሎች አውሮፓዊያን ሃገራት ፈጣን የሆነ የመዘመን ብልጫ እንደሚወሰድበት አረጋገጠ፡፡  

የሆጋን እግርኳሳዊ ምልከታ መነሻው ላይ በጥርጣሬ የመታየት ሁኔታ ገጠመው፡፡ በርካታ ሀገር በቀል አሰልጣኞች ሆጋን ጀርመንኛ ቋንቋ ላይ ያለበትን ክፍተት እና አንደበተ-ርቱዕ አለመሆኑን በተመለከተ ቅሬታዎችን ማቅረብና ማጉረምረም ሲጀምሩ የሃገሪቱ እግርኳስ ማህበር አመራሮች ለግምገማ ይረዳቸው ዘንድ ሆጋን ሰልጣኝ-አሰልጣኞቹን ያለ አስተርጓሚ እንዲያስተምራቸውና እንዲያማክራቸው ጠየቁት፡፡ መጀመሪያ ላይ በታዘዘው መሰረት ጥያቄውን ለማስተናገድ ሲጥር  ከበደው፡፡ አሰልጣኙ ራሱን የእግርኳስ ልሂቅ አድርጎ ከማየት ይልቅ እንደ ቋንቋ ምሁር ሆኖ በመቅረቡ የከፋ ትዝብት ውስጥ ወደቀ፡፡በእግርኳሱ አለም አዕምሮአዊ ብቃት ያለው ፋይዳ  ከፍተኛ ስለመሆኑ አጽዕኖት ሰጥቶ ሰብካቸው፡፡ ጨዋታው በአካላዊ ፍልሚያ የበላይነት ለማግኘት የሚያስፈልገውን ጉልበት ብቻ የሚጠቀም ስፖርት ሳይሆን በህብረት ስራና ምክክር ውጤት የሚገኝበት እንደሆነ ድንግርግር ባለ ስሜት ውስጥ ሆነው ለሚያደምጡት ታዳሚዎቹ አብራራላቸው፡፡ ይህን ሲል አድማጮቹ በሙሉ በንቀት ሳቅ አጀቡት፡፡ ሆጋንም ወዲያው የአስር ደቂቃ ዕረፍት ጠይቆ ከመድረኩ ወረደ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ የቦልተን ወንደረርስ ትጥቁን ለብሶ ወደ መድረኩ ተመለሰ፡፡ ጫማውን እና ካልሲውን አወላልቆ ሲጨርስ አስራ አራት ሜትር በሚርቅ እኩል በእኩል የተከፋፈለ ከእንጨት የተሰራ ግድግዳ ላይ ጠንካራ ምቶችን በቀኝ የባዶ እግሩ እየመታ በማሳየት ሶስት-አራተኞቹ የጀርመን ተጫዋቾች ኳስን በአግባቡ መቀባበል እንደማይችሉ አስረዳ፡፡ ኳሷ ግድግዳውን ተላትማ ስትመለስ በግራ እግሩ እየነረታት በሁለት እግሮች እኩል መጫወት መቻል ያለውን ጠቀሜታ መግለጹን ተያያዘው፡፡ ከብዙ ጠንካራ ምቶች በኋላ ግድግዳው ለሁለት ተሰነጠቀና የሆጋን ሐሳብ ትክክለኛ መሆኑን አረጋገጠለት፡፡ ከዚያም ስለእግርኳስ ትምህርት የመስጠት ተከታታይ ጉዞዎችን ማድረግ ተጠበቀበት፡፡ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ድሬስደን አካባቢ ብቻ አምስት ሺህ ለሚጠጉ ተጫዋቾች ስለ እግርኳስ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ትንታኔዎችን ሰጠ፡፡ በ1974 ከዚህ አለም በሞት ሲለይ የጊዜው የጀርመን እግርኳስ ማህበር ዋና ጸሃፊ ሃንስ ፓዝላክ ፍራንክ ለተባለው የሆጋን ልጅ አባቱ በጀርመን <የዘመናዊ እግርኳስ መስራች> እንደነበር የሚገልጽ ደብዳቤ ጻፈለት፡፡

በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ያልተመቸው ሆጋን ጀርመንን ለቆ ወደ ፓሪስ ተሰደደ፡፡ በዘመኑ የሃገሪቱን ብር ወደ ሌሎች ቦታዎች ይዞ ለመጓዝ የሚከለክለውን እገዳ ለማምለጥ በጀርመን ያጠራቀመውን ገንዘብ ቦላሌ መሳይ ሱሪው ውስጥ ጠቅጥቆ በመስፋት ከሃገሪቱ ለመውጣት ሞከረ፡፡ በፈረንሳይ በከዋክብት ተጫዋቾች የተሞላው ቡድንን ስነ-ስርዓት ማስያዝ ተቸገረና ወደ ሉዛን ተመለሰ፡፡ በሉዛንም የግብ እድሎችን በአግባቡ የማይጠቀሙ ተጫዋቾች ላይ ቅጣት እንዲተላለፍባቸው አጥብቆ ከሚፈልገው የክለቡ ሊቀ መንበር ጋር ፍጹም መግባባት አቃተው፡፡ ሑጎ ሜይዝል ሲጠራውም አዲስ ፈተናን የመጋፈጥ ሐሞቱ ፈሶ ነበር፡፡ 

ኦስትሪያ ደግሞ እንደ ሆጋን ያለ የተጫዋቾቿን ተሰጥዖ የሚያጎለብት እና ለተፈጥሮአዊ ክህሎታቸው ማረጋገጫ የሚሰጥላት ገለልተኛ  የሆነ ሰው እጅጉን ያስፈልጋት ነበር፡፡ በለንደን ከእንግሊዝ ጋር ከመጫወታቸው አስራ አምስት ቀናት በፊት በህመም ምክንያት ከምርጥ ብቃቱ  የወረደውን ሲንድለር የያዘችው ኦስትሪያ ከቪየና የተውጣጡ ተጫዋቾች ስብስብን 2-1 ለመርታት ከፍተኛ ትግል አደረገች፡፡ ጉዳዩ በጣም አናዳጅ ከመሆኑ ሌላ በአዶልፍ ቮግል እና በፍሪየድሪክ ጋስችዌይድል ላይ ግልጽ የአካል ብቃት ችግር ታየ፡፡ የሆነ ሆኖ የኦስትሪያውያን ግጥሚያውን የማሸነፍ ጉጉት ጣሪያ ነካ፡፡ በርካታ ሰዎች በሄልደንፕላዝ ተሰባስበው በሶስት ድምጽ ማጉያ መሳሪያዎች የሚተላለፈውን የቀጥታ ስርጭት ለመከታተል ቦታውን አጨናነቁ፡፡ የሃገሪቱ ፓርላማ የፋይናንስ ኮሚቴ አባላትም ጨዋታው እንዳያመልጣቸው ሲሉ መደበኛ ስብሰባቸውን በትነው ጆሯቸውን ወደ ድምጽ ማጉያዎቹ ቀሰሩ፡፡ 

ዉንደርቲሞች ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ አልጀመሩም፡፡ በመጀመሪያዎቹ ሃያ ስድስት ደቂቃዎች እንግሊዛውያኑ 2-0 የመምራት አጋጣሚ ፈጠሩ፡፡ ሁለቱንም ግቦች የብላክፑሉ አጥቂ ጂሚ ሃምሰን አስቆጠረ፡፡ ለእረፍት ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ሲንድለርና አንቷን ሻል በጥሩ ውህደት የፈጠሩትን እድል ካርል ዚሼክ በአግባቡ ተጠቀመበትና ኦስትሪያ አንድ ግብ አገባች፡፡ በዚህ የግብ ልዩነት በከፍተኛ ጫና እየተካሄደ በነበረው ጨዋታ ላይ ዋልተር ናውሽ አክርሮ የመታውን ኳስ የግቡ ቋሚ መለሰበት፡፡ ከዚያም እንግሊዞቹ ከተወሰደባቸው ብልጫ አገገሙ በማጥቃት ሒደት ውስጥ ሳሉም የቅጣት ምት አገኙ፡፡ ኤሪክ ሃውተን የመታት ቅጣት ምት አንቷን ሻልን ደርባ አቅጣጫዋን በመቀየር ስትደበሰበስ ሩዲ ሄደንን አልፋ የኦስትሪያ መረብ ውስጥ ተመሰገች፡፡ እንግሊዝ 3-1 ኦስትሪያ፡፡ ጥቂት ቆየና ሲንድለር በእንግሊዞች የመከላከያ ክልል በአስገራሚ ምሉዕነት የተቆጣጠራትን ኳስ እርጋታን በተላበሰ አጨራረስ አሳምሮ ወጤቱን 3-2 እንዲሆን አስቻለ፡፡ ይሁን እንጂ በጨዋታው ላይ አመርቂ ብቃት ለማሳየት ሲጥር የታየው ሳም ክሮክስ በመጨረሻ ተሳክቶለት እንግሊዝ 4-2 እንድትመራ አደረገ፡፡ ኦስትሪያኖቹ ኳሱን ሲቀሙ ወደኋላ አፈግፍገው ከኳሱ ጀርባ በሚሆኑበት ልማዳቸው እንግሊዞችን ግራ በማጋባት ተጽዕኖ ለመፍጠር ሞከሩ፡፡ በአጫጭርና የተወሳሰቡ ቅብብሎቻቸው እየታገዙ ተጋጣሚያቸው ላይ ከፍተኛ ብልጫ ቢወስዱም ወደፊት የመግፋት እና የማጥቃት የበላይነታቸውን ወደ ስኬት በመቀየር ረገድ የታየባቸው ድክመት ዋጋ አስከፈላቸው፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ከማዕዘን የተሻማን ኳስ ተጠቅሞ ሺዤክ ጎል አገባ፡፡ ግቧ የተገኘችው ከረፈደ ስለነበር በጨዋታው አጠቃላይ ውጤት ላይ የፈጠረችው ልዩነት አልነበረም፡፡ ኦስትሪያኖቹ 4-3 ተረቱ፡፡ በጨዋታው ባሳዩት ብቃት ሀሳበ ሰፊነት እንደነበራቸው አሰመሰከሩ፡፡ ምናባዊው የእግርኳስ አቀራረብ ቅኝታቸው በደንብ ታየላቸው፡፡ <ዴይሊ ሜይል> ጋዜጣም “ክስተት!” ሲል አወደሳቸው፡፡ <ዘ-ታይምስ> ደግሞ አስገራሚ የቅብብል ክህሎታቸውን በተመለከተ ቅኔ ዘረፈላቸው፤ “የሞራል ልዕልና ባለድሎች!” የሚል ሙገሳም ቸራቸው፡፡ 

ከሁለት ዓመታት በኋላ “የቪየና ምርጥ አስራ አንድ” ይባል እንጂ በመሰረቱ የኦስትሪያ ብሄራዊ ቡድን የሆነ የሃገሪቱ ተጫዋቾች ስብስብ በሃይብሪ አርሰናልን ገጠመ፡፡በወቅቱ ፊፋ በብሄራዊ  ቡድኖችና በክለቦች መካከል የሚካሄዱ  ጨዋታዎችን እውቅና ካለመስጠቱ በተጨማሪ መደረጋቸውንም ይቃወም ነበር፡፡ እንግዳው ቡድን 4-2 ተሸነፈ፡፡ እንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ሮላንድ አለን በ<ኢቪኒንግ ስታንዳርድ> ጋዜጣ ላይ ተሸናፊዎቹን የሚያበረታታ ጽሁፍ አወጣ፡፡ ” ኦስትሪያዎች በመሸነፋቸው ሊቆጩ አይገባም፤ ምንም አይደል! እነርሱ ያላቸውን ጉብዝና በሙሉ ወደ ተሻለ ነገር ሲቀይሩ፣ በእግርኳስ ማሸነፍ ያለውን ዋጋ ወደ ተደራጀ ስርዓት ለመለወጥ ሲጥሩ ይበልጥ ጨዋታውን እየተላመዱና አጨዋወቱም እየተዋሃዳቸው ሄዷል፡፡ ይህን ሲያደርጉ ሁሉም ሰው ቁጭ ብሎ በጥሞና ማስታወሻ እንዲወስድ የማድረግ አቅም ነበራቸው፡፡” ሲል ስለዘመነው እግርኳሳቸው ምስክርነቱን አስቀመጠ፡፡ በእርግጥ  መልዕክቱ ግድግዳው ላይ በግልጽ ሰፍሯል፤ ይሁን እንጂ ማስታወሻውን በእንግሊዝ ማንም ሊያነበው ዝግጁነት አላሳየም፡፡ 

ይልቁንም ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ጨዋታዎች
አልፎአልፎ የሚጠቀሰውን ” የአውሮፓ ሃገራት እግርኳስ ቡድኖች በሜዳው ቀመት የመጨረሻ ሲሶ ላይ ስልነት ይጎድላቸዋል፡፡” የሚል አባባል እርግጠኛነት ያሳየ ነበር፡፡ ጉዳዩን ወደ ኦስትሪያ ስናመጣው አባባሉ የተወሰነ እውነታ እንደያዘ እንረዳለን፡፡ በሰፊው ማህበረሰብ ዘንድ ያለው ኳስን እግር ስር የማቆየት ግንዛቤ ጥርት ያለ አይደለም፡፡ የሜይዝል ሃሳባዊ ስያሜዎች ላይ የሚሰጡ ማብራሪያዎች እንኳ ችግሩን ሊፈቱ አልቻሉም፡፡ ” መሃከለኛው አውሮፓ ውስጥ ላለነው የብሪታኒያ እግርኳስ የማጥቃት ሒደቱ የሚመራበት ሁኔታ ከውበትና ጥበባዊ ይዘት አንጻር እጅግ ደካማ ይመስለናል፡፡ እነርሱ ግቦችን የማስቆጠር ኃላፊነት ለመሃል አጥቂው (Center- Forward) እና ከመስመር ለሚነሱት ሁለቱ የክንፍ አጥቂዎች (Wing Forwards) ሰጥተዋል፡፡ ከመሃል አጥቂው ግራና ቀኝ የሚገኙት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside Forwards) ደግሞ ከማጥቃት ድርሻቸው ይልቅ አማካዮች ሆነው ተከላካዮችንና አጥቂዎችን የማገናኘቱን ሚና እንዲወጡ ተመድበዋል፡፡ እኛን በመሳሰሉ አውሮፓውያን ጋር ግን የመሃል አጥቂው በቴክኒካዊ ልህቀቱ እና በታክቲካዊ ግንዛቤው ምክንያት የጨዋታ መሪ ዘዋሪ ነው፡፡ በእንግሊዝ እኮ የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች የሚሰሩትን ስህተት እንኳ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲያውል አይፈቀድለትም፡፡” ሲል ሜይዝል አብራራ፡፡ 

ሑጎ ሜይዝል ብራታኒያውያኑ እግርኳስ የሚጫወቱበትን ፍጥነት ያሞካሻል፡፡ የእርሱ ቡድን ተጫዋቾች በእንግሊዞቹ ተጫዋቾች ከፍተኛ ፍጥነት እንደተደናበሩና ግራ እንደተጋቡም ሳይሸሽግ ይናገራል፡፡ ” ቅብብሎቻቸው ፈጣንና ረዘም ያሉ ቢሆኑም ለታሰበላቸው ተጫዋቾች ከመድረስ አንጻር የምጣኔ ትክክለኝነት ህጸፅ ይስተዋልባቸዋል፡፡ ስለዚህም የእንግሊዝ ተጫዋቾች ይህን ችግር ሃይልና ፍጥነትን ባዋሃደው የማጥቃት አጨዋወታቸው ሊያካክሱ ሞክረዋል፡፡” ብሎ በእንግሊዛውያን እና በተቀረው የአውሮፓ ክፍል እግርኳስ መካከል ያለውን ልዩነት አስቀመጠ፡፡ በዚህም ሳቢያ የተለመደው የእግርኳስ አቀራረብ ዘይቤ ክፍፍል መስመር ተሰመረ፡፡ የእንግሊዞቹ እግርኳስ ተክለሰውነት ላይ የተመረኮዘ፣ አካላዊ ጉሽሚያን የሚያበረታታ፣ ፈጣንና ሃይልን የቀላቀለ ጨዋታ፥ የአህጉሪቱ ሌሎች ሃገራት እግርኳስ ደግሞ ለተጫዋቾች ቴክኒካዊ ክህሎት ቦታ የሚሰጥ፣ እርጋታን የሚያስቀድም እና ምናልባትም ሞራላዊ ወኔ የሚገድለው ሆኖ ተፈረጀ፡፡ 

ኦስትሪያ እንግሊዝን እንድታሸንፍ ሜይዝል እጅጉን ሲጓጓ የኖረው መሻቱ በግንቦት 1936 በርዕሰ መዲናዋ ቪየና በተደረገው ጨዋታ ተሳካለት፡፡ ሜይዝል ስለዉንደርቲም ለሆጋን ማብራሪያ ሲያቀርብ እንግሊዛዊው አሰልጣኝ ከቡድኑ የመሃል አጥቂ ግራና ቀኝ ያሉትን አጥቂዎች (Inside Forwards) አካላዊ ጥንካሬ ደረጃ ጠየቀው፡፡ ሜይዝልም ተጫዋቾቹ በጨዋታው የመጀመሪያ ሃያ ደቂቃዎች ውስጥ በማጥቃቱ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው እና በቀጣዮቹ ሰባ ደቂቃዎች ግን በመከላከል ላይ ሊያተኩሩ እንደሚችሉ አስረዳው፡፡ ሜይዝል ትክክል ነበር፡፡ ሲንድለር በተደጋጋሚ የእንግሊዙን የመሃል-ተከላካይ አማካይ ጆን ባርከር ወደኋላ እንዲያፈገፍግ ሲያስገድደው ታየ፡፡ ድርጊቱ ከአስራ ሰባት ዓመታት በኋላ በሃንጋሪው አጥቂ ናንዶር ኼጁኩቲ አማካኝነት ሃሪ ጆንስተን የደረሰበትን መከራ ቀድሞ የተነበየ መሰለ፡፡ እንግሊዞቹ ጨዋታው እንደተጀመረ 2-0 የመመራት ሁኔታ ገጠማቸው፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ ጆርጅ ካምሴል ለእንግሊዞች አንድ ግብ አስቆጠረ፡፡ ክብ ጠፍጣፋ ኮፍያ አድርጉ በቴክኒካል ክልሉ ላይ በጭንቀት በሚንጎራደደው ሜይዝል የምትመራው ኦስትሪያ የበላይነት ማሳየቷ ግልጽ ነበር፡፡
” እኛ በሜዳው ላይ በመመላለስ ዑደት ውስጥ እንደነበርን አልተገነዘብነውም፤ በዚያ ላይ የአየር ሁኔታው በአስቀያሚ ሁኔታ ሞቃት ነበር፡፡” ሲል ጃክ ክራይሰን ከጨዋታው በኋላ አስተያየቱን ሰጠ፡፡ እንግዲህ የሙቀቱ መጠንና ሁኔታ አካላዊ ፍትጊያ የሚያመዝንበትን ጨዋታ ለማድረግ የማያዛልቅ እና የኳስ ቁጥጥርን ብቻ የሚፈቅድ ሲሆን የብሪታኒያ ቡድኖች ከተጋጣሚዎቻቸው አንጻር ልቀው ሳይገኙ ዘለቁ፡፡ 

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *