ሴካፋ እስከ ፍፃሜው ድረስ በሃዋሳ ሊካሄድ ይችላል

 

-ብሄራዊ ቡድናችን ጠዋት ልምምዱን ሰርቷል

 

የ2015 ሴካፋ በ3 ከተሞች መካሄዱን ቀጥሏል፡፡ ዛሬ እና ነገ በሚደረጉ የየምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች ሀላፊዎቹ 8 ቡድኖች ሙሉ በሙሉ የሚለዩ ሲሆን የሴካፋ አወዳዳሪ ኮሚቴ ባወጣው ፕሮግራም መሰረት ከሩብ ፍፃሜ ጀምሮ የሚደረጉትን ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታድየም እንደሚደረጉ መግለፁ የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን ከሩብ ፍፃሜው እስከ ፍፃሜው የሚደረጉት ጨዋታዎች በሙሉ በሃዋሳ መካሄዳቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ከወደ ሀዋሳ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሴካፋ አወዳዳሪ አካላት ፣ የውድድሩ ስፖንሰር እና አብይ የቴሌቪዥን አስተላላፊው ዲኤስቲቪ እንዲሁም በሀዋሳ የሚገኙት ቡድኖች በከተማው እና መስተንግዶው መደሰታቸውና ውድድሩ እዚሁ እንዲጠናቀቅ ፍላጎት ማሳየታቸው ታውቋል፡፡

የውድድሩ በሀዋሳ መቅረት በይፋ ማረጋገጫ ባይሰጥበትም አዘጋጅ አካሉ ተወያይቶ ከውሳኔ ላይ ይደርሳልም ተብሏል፡፡

 

last training

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለነገው ወሳኝ ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ጠዋት ላይ አድርጓል፡፡ በዛሬው ልምምድ ጉዳት ላይ ከሚገኘው ሳላዲን በርጊቾ እና ራምኬል ሎክ በስተቀር 18 ተጫዋቾች ልምምዳቸውን ሰርተዋል፡፡

አጥቂው ራምኬል ሎክ ትላንት አመሻሹ ላይ ከልምምድ በኋላ መጠነኛ የውስጥ ህመም ያጋጠመው ሲሆን እረፍት እንዲያደርግ በሀኪሞች በመወሰኑ የዛሬውን ልምድ ማድረግ አልቻለም፡፡ ነገር ግን ህመሙ ቀለል ያለ በመሆኑ ነገ ታንዛንያን በምንገጥምበት ጨዋታ ይሰለፋል ተብሏል፡፡

ብሄራዊ ቡድናችን ነገ ወሳኝ የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታውን ከታንዛንያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል፡፡ ካሸነፈ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፉን ሲያረጋግጥ አቻ እና ሽንፈት ግን ከምድቡ ለማለፍ የሌሎች ምድቦችን ውጤት ለመጠበቅ ያስገድደዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *