ከፍተኛ ሊግ ሀ | ሰበታ ከተማ መሪነቱን ሲያጠናክር ተከታዮቹ ነጥብ ጥለዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከእረፍት በኋላ በ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲጀመር ሰበታ ከተማ መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል አስመዝግቧል። ተከታዮቹ ለገጣፎ፣ ኤሌክትሪክ እና ወልዲያ ነጥብ ሲጥሉ ደሴ ከተማ አሸንፏል።

ወደ ኮምቦልቻ አምርቶ ወሎ ኮምቦልቻን የገጠመው ሰበታ ከተማ 4-0 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሯል። ናትናኤል ጋንቹላ በ15ኛው እና 55ኛው ደቂቃ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነቱ አናት ላይ ሲቀመጥ ወደ ቀድሞ ክለቡ በዚህ ሳምንት የተመለሰው ዐቢይ ቡልቲ በ70ኛው፤ ጫላ ዲሪባ ደግሞ በ83ኛው ደቂቃ ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል። ድሉን ተከትሎ ሰበታ በሁለት ነጥቦች ልዩነት ምድቡን መምራት ጀምሯል።

ለገጣፎ ላይ ያለፉትን ዓመታት በአዳማ እግርኳስ ላይ ስኬታማ ስራ ሲሰሩ የነበሩት ሁለቱ ወጣት አሰልጣኞች ዳዊት ታደለ እና ዳዊት ሐብታሙ ያገናኘው የለገጣፎ እና የገላን ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የረባ እንቅስቃሴ ሆነ የግብ ሙከራዎች ሳንመለከትበት በተጠናቀቀው የመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንግዶቹ ገላኖች በመልሶ ማጥቃት እና በፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግ በጨዋታው የመጀመርያ የጎል እድል መፍጠር ችለዋል። ከገላን ግብ ክልል በረዥሙ የተመታውን የለገጣፎው ተከላካይ አንዋር ኳሱ ነጥሮበት ሲያመልጠው ጅብሪል አህመድ ወደ ፊት ይዞ በመግባት ተረጋግቶ የቁጥር ብልጫቸውን በመጠቀም ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

ባለሜዳዎቹ ለገጣፎዎች ጌትነት ደጀኔ ከማዕዘን ምት ከፈጠረው አጋጣሚ በቀር ኳሱን ከግብ ጠባቂው ጀምሮ አደራጅተው ለመጀመር ቢያስቡም የሜዳው የመሐለኛው የሜዳ ክፍል ሲገቡ አማካዮቹ በሚፈጥሩት ተደጋጋሚ ስህተት በበቂ ሁኔታ አጥቂዎቹ ለጎል የቀረበ እድል ሳያገኙ በመቅረታቸው አንድም የጎል እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። ይልቁንም በሚያደርጉት ያልተሳካ ቅብል በሚፈጥሩ ተደጋጋሚ ስህተቶች መነሻነት ገላኖች በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ለገጣፎ የግብ ክልል ቢደርሱም በተመሳሳይ እነርሱም ምንም ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ የጎል ሙከራዎችን በተመለከትን በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ገላኖች ሁለቱን አጥቂዎቻቸውን አንተነህ ደርቤ እና እሸቱ ጌታሁን ቀይረው ካስገባ በኋላ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። የገላኑ አጥቂው እሸቱ ጌታውን በፍጥነት ከቀኝ መስመር ቆርጦ ወደ ፊት በመግባት ወደ ጎል ያሻገረውን ሚካኤል ደምሴ አግኝቶ ቢመታውም ኳሱ ግብጠባቂውን ጨርፎ በማለፍ ጎል ሆነ ሲባል የለገጣፎ ተከላካይ ነስረዲን ኃይሌ ወደ ውጭ አውጥቶታል።

በዛሬው ጨዋታ እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ባለሜዳዎቹ ለገጣፎዎች በተደጋጋሚ ባልተደራጀ እንቅስቃሴ ገላን የግብ ክልል ቢደርሱም ክፍት የሆነ የግብ ዕድል መፍገር አልቻሉም። ከቆሙ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረትም የገላኑ ግብጠባቂ ውብሸት ጭላሎ በቀላሉ ይቆጣጠራቸው ነበር።

በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃ ተጭነው የተጫወቱት ገላኖች ከቅጣት ምት በቀጥታ ሚኬኤል ደምሴ ወደ ጎል የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን አንተነህ ሀብቴን ቢያልፈውም ተከላካዩ መዝገቡ ቶላ ጎል እንዳይሆን ያወጣው ኳስ ለገላን የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል። ብልጫ ቢወሰድባቸው አልፎ አልፎ ወደ ጎል በረጃጅም ኳሶች ወደ ጎል የሚደርሱት ለገጣፎዎች ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ከገላን ተከላካዮች በግንባር ተጨርፎ የቀረውን ኳስ አምስት ከሃምሳ ውስጥ ብሩክ መርጊያ ሳይጠቀምበት ወደ ሰማይ የሰደዳት ኳስ ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚ ነበር።

የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ መልኩን በመቀየር ወደ ኃይል አጨዋወት አምርቶ የነበረ ቢሆንም ተደጋጋሚ የውሳኔ ችግር ያየንባቸው የዕለቱ ፌዴራል ዳኛ ዮናስ ጨዋታውን ለመቆጣጠር ካርዶችን ለመጠቀም ተገደው ጨዋታው ያለ ጎል በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ አክሱም ተጉዞ ነጥብ ጥሏል። 1-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ገና በመጀመርያው ደቂቃ በሐብታሙ ረጋሳ ጎል ቀዳሚ በመሆን ለረጅም ደቂቃዎች መምራት ቢችልም በ70ኛው ደቂቃ በረከት ግዛው ባለሜዳው አክሱም ከተማን አቻ አድርጓል።

ወልዲያ ላይ አቃቂ ቃሊቲን የገጠመው ወልዲያ 1-1 አቻ ተለያይቷል። ተስሎች ሳይመን በ40ኛው ደቂቃ ወልዲያን መሪ ሲያደርግ በ65ኛው ደቂቃ ዮናስ ባቢና አቃቂ ቃሊቲን አቻ አድርጓል።

ደሴ ከተማ በሜዳው ቡራዩ ከተማን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል። በድሩ ኑርሁሴን የሁለቱም የደሴ ከተማ ጎሎች ባለቤት ነው።

በዚህ ምድብ አውስኮድ ከፌዴራል ፖሊስ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *