የ22ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተባለበት ቀን ይካሄድ ይሆን?

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት የፊታችን ሐሙስ በሚካሄዱ 8 ጨዋታዎች ይቀጥላል ተብሎ መርሐግብር የወጣለት ቢሆንም በታሰበለት ጊዜ ላይካሄድ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

ከአንዳንድ ክለቦች ባገኘነው መረጃ መሰረት ከፌዴሬሽኑ ሊግ ኮሚቴ ስልክ እየተደወለ ወዴትም አካባቢ እንዳትንቀሳቀሱ፤ የመርሐ-ግብር ለውጥ ካለ እናሳውቃችኃለን በመባል እንደተነገራቸው ሰምተናል። በዚህም መሠረት በተለይ የደቡብ ፖሊስ እግርኳስ ክለብ መንገድ ጀምረው ወደ መጡበት እየተለሱ መሆናቸውን ለማወቅ ችለናል።

የሊግ ኮሚቴው ተወዳዳሪ ክለቦችን ቆዩ ያለበት ምክንያት በይፋ የገለፀ ነገር ባይኖርም ” የተቋረጡ ውድድሮች ሳይካሄዱ ሌሎች ውድድሮችን ማስኬድ አዳጋች ሊሆን ይችላል በሚል 22ኛው ሳምንት ውድድርን ላይካሄድ እንደሚችል ሰምተናል። በአሁን ሰአት የሊግ ኮሚቴ አባላት ስለቀጣይ መርሐግብሩ መካሄድ አለመካሄድ ለመወሰን ስብሰባ መቀመጣቸውን ለማረጋገጥ ችለናል::