ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ባህር ዳር ከተማ

መከላከያ እና ባህር ዳር ከተማ ከሁለት ሳምንት በፊት በድምሩ ዘጠኝ ጎሎች ባስተናገዱበት ስታድየም በ23ኛ ሳምንት መርሐ ግብር እርስ በርስ ይግናኛሉ።

ሶዶ ላይ ተስፋን ሰንቆ የተመለሰው መከላከያ ዛሬ 10፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ከሁለት ሳምንት በፊት ከመዲናዋ በመጥፎ ትዛታ የተመለሰው ባህር ዳር ከተማን ያስተናግዳል። ወላይታ ድቻን በረታበት ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው የወጣው መከላከያ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ነበር ወደ ድል የተመለሰው ሆኖም ራሱን ነፃ ለማድረግ ተጨማሪ ነጥቦች ማግኘት ግድ ይለዋል። በሜዳው ከመምራት ተነስቶ ነጥብ ለመጋራት የተገደደው ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ በዋንጫ ፉክክሩ ቢርቅም የመውረድ ስጋት የለበትም። ሆኖም ላለፉት ሁለት ጨዋታዎች ማሳካት ያልቻለውን ድል መልሶ ለማግኘት ከጦሩ ሦስት ነጥብ ይፈልጋል።

መከላከያ ሳይታሰብ ከወላይታ ድቻ ሦስት ነጥብ ማግኘቱ ጠፍቶበት የነበረውን የአሸናፊነት መንፈስ ለመመለስ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል። ነገር ግን በጨዋታው ላይ ሁለት ግቦችን ማስተናገዱ ሲታሰብ አሁንም በተከላካይ መስመሩ ላይ ያለው ችግር እንዳልተቀረፈ ያሳያል። ቅጣት ላይ ከሚገኘው አበበ ጥላሁን በተጨማሪ ሌላኛው የመሀል ተከላካይ አዲሱ ተስፋዬ ያለበት መጠነኛ ጉዳት ጨዋታውን እንደሚጀምር አጠራጣሪ ማድረጉ ደግሞ ከኋላ ተጨማሪ ስጋት ሊፈጥርበት ይችላል። ለመልሶ ማጥቃት ቅድሚያ ከሚሰጡ ተጋጣሚዎች ጋር ሲገናኝ መሀል ላይ በተደጋጋሚ ከሚነጠቃቸው ኳሶች አደገኛ ጥቃቶች ሲፈፀሙበት እና በርካታ ግቦች ሲቆጠሩበት የሚታየው ጦሩ ዛሬም መሀል ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል። ሙሉ በሙሉ በዳዊት እስጢፋኖስ እንቅቃሴ ላይ ተመስርቶ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለማግኘት ሲጥር የሚታየው መከላከያ ዛሬ ምናልባት ባህር ዳሮች ኢትዮጵያ ቡናን በገጠሙበት አኳኋን ዳግም ከቀረቡ በፍጥነት ኳሶችን ወደ ፊት በማድረስ ከተከላካዮች ጀርባ መድረስን ሌላኛው አማራጩ ሊያደርግም ይችላል።

ከደቡብ ፖሉሱ ጨዋታ በኋላ ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር ለመለያየት ከጫፍ ደርሰው የነበሩት ባህር ዳሮች ሁኔታው በቡድን መንፈሳቸው ላይ ሊፈጥር ከሚችለው መቀዘቀዝ በተጨማሪ ስድስት ተጫዋቾቻቸውን ሳይዙ ነው መከላከያን የሚገጥሙት። በዚህም በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው ሣለአምላክ ተገኝ በቅጣት ፤ በደቡብ ፖሊስ ጨዋታ ሳይጠበቅ በቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው አቤል ውዱ ደግሞ ጉዳት በማስተናገዱ ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ ዳንኤል ኃይሉ ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ፣ ቴዎድሮስ ሙላት እና ተስፋሁን ሸጋውም በተመሳሳይ በጉዳት ቡድናቸውን አያገለግሉም። በመሆኑም የጣና ሞገዶቹ በተለይም በተከላካይ እና በአማካይ ክፍላቸው ላይ ብዙ ለውጦችን ማድረግ የሚጠበቅባቸው መሆኑ በጨዋታው የሚኖረውን የማጥቃት ድፍረት ሊቀንሰው ይችላል። በቡናው ጨዋታ ከራሱ የግብ ክልል ርቆ መከላከሉ ያስከፈለው ዋጋ ሲታሰብ ደግሞ ባህር ዳር ዛሬ ለጥንቃቄ ቅድሚያ በመስጠት የመስመር አጥቂዎቸን መሰረት ያደረገ  የመልሶ ማጥቃት ዕቅድ ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል። 

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በሊጉ የመጀመሪያ ግንኙነታቸው የነበረው የስምንተኛ ሳምንቱ ጨዋታ ባህር ዳር ላይ ተከናውኖ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቆ ነበር።

– አዲስ አበባ ላይ አስር ጊዜ የክልል ቡድኖችን የገጠመው መከላከያ አንድ ጊዜ ብቻ ድል ሲቀናው ሦስቴ ነጥብ ተጋርቶ በስድስት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

– ባህር ዳር ከተማ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው 11 ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን ሲያሸንፍ በአራቱ ነጥብ ተጋርቶ በአምስቱ ደግሞ ተሸንፎ ተመልሷል።

ዳኛ
– ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የዓመቱ 13ኛ ጨዋታውን ይዳኛል። መከላከያን ከጅማ ባህርዳርን ደግሞ ቡና እና ጊዮርጊስ ጋር ያጫወተው አርቢትሩ እስካሁን በዳኘባቸው ጨዋታዎች 41 የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ሲመዝ 2 የቀይ ካርድ እና 3 የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎችንም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-2-3-1)

አቤል ማሞ

ሽመልስ ተገኝ  – ምንተስኖት ከበደ – አዲሱ ተስፋዬ – ታፈሰ ሰረካ

አማኑኤል ተሾመ – ቴዎድሮስ ታፈሰ 

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ፍሬው ሰለሞን

ፍቃዱ ዓለሙ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት አሎ

ማራኪ ወርቁ – ወንድሜነህ ደረጄ – አሌክስ አሙዙ – አስናቀ ሞገስ

ዳግማዊ አባይ – ደረጄ መንግስቱ – ኤልያስ አህመድ

ግርማ ዲሳሳ – ፍቃዱ ደነቀ – ወሰኑ ዓሊ