የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ሀ ውሎ

በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ሀ 12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ተካሂደው ሀዋሳ እና ድቻ ድል አስመዝግበዋል።

ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ድሬዳዋን ገጥሞ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማ ከሀዋሳ ተሽሎ የታየበት ነበር። በተለይ በቀኝ የሀዋሳ የግብ ክልል መስመር ድሬዳዋዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መሰንዘር ችለዋል፡፡ ለዚህም ማሳያ ሚካኤል ገብረመድህን ከግራ አቅጣጫ በሚገባ የደረሰችሁን ኳስ ሞክሮ ሳይጠቀምባት የቀረችው ተጠቃሽ ሙከራ ናት፡፡ በሂደት በእንቅስቃሴ ቢበለጡም በግብ ሙከራ ተሽለው የታዩት ሀዋሳዎች በአጥቂው ተባረክ ኢፋሞ አማካኝነት በርካታ ግብ ሊሆኑ ሚችሉ ዕድሎችን ቢያገኝም በተደጋጋሚ ሊጠቀም አልቻለም፡፡ 20ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ገዛኸኝ በግል ጥረቱ የፈጠረለትን ዕድል ከግብ ጠባቂው ጋር ያገናኘችሁ ብትሆን በተመሳሳይ ተባረክ ወደ ውጪ ሰዷታል፡፡ አምበሉ ሐብታሙ በሀዋሳ በኩል ወደ ሳጥኝ ውስጥ ሰብሮ በመግባት የተጋጣሚን መረብ ለመድፈር መንገዶችን ቢያገኝም ብቻውን ሆኖ የሚረዳው ሌላ ተጫዋች ባለመኖሩ ግብ ማስቆጠር ሳይችል ቀርቷል፡፡ ድሬዎች በቀኝ በኩል ሲያደርጉ የነበረው ጥረት 30ኛው ደቂቃ ላይ ሚካኤል ያሻማትን ኳስ ሮባ አሚን በቀጥታ መቶ  የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ንብረት ዘንባባ አድኖበታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ እና ሀዋሳ ከተማዎች በአንፃሩ ከረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶች ግብ ማስቆጠር የቻሉበት ነበር። 48ኛው ደቂቃ ድሬዳዋዎች ከሚገኙ የኮሪደር ኳሶች በመጠቀም በሰይፈ ታከለ ግሩም ሙከራን ቢያደርጉም በዕለቱ ድንቅ የነበረው የሀዋሳ ግብ ጠባቂ ንብረት ተመልሶበታል፡፡ 62ኛው ደቂቃ ተባረክ ኢፋሞ በረጅሙ ያቀበለውን ኳስ በመቆጣጠር ሐብታሙ ገዛኸኝ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡ ብዙም የግብ አጋጣሚዎችን መመልከት ባልቻልንበት ሁለተኛው አጋማሽ 73ኛው ደቂቃ በዛብህ ካቲቦ በድጋሚ የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ ሁለት አሳድጓል። በቀሪዎቱ ደቂቃዎች ድሬዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥቃቶችን ቢፈፅሙም ኳስን ከመረብ ጋር ማዋሀድ ሳይችሉ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ በተመሳሳይ ቅዳሜ ወላይታ ድቻ በሜዳው መከላከያን 2-0 አሸንፏል።

እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች አምቦ ጎል በሜዳው ከ ሲዳማ ቡና ጋር 2-2 አቻ ሲለያይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ አካዳሚ ባለመገኘቱ ለጥሩነሽ ፎርፌ ተሰጥቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡