የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 6-1 ጅማ አባጅፋር

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የተደረገው የፋሲል ከነማ እና የጅማ አባጅፋር ጨዋታ በፋሲል ከነማ የበላይነት 6-1 ተጠናቋል። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“በርካታ ግቦች ማስቆጠራችን በራስ መተማመናችን እንዲጨምር ያደርጋል” ውበቱ አባተ (ፋሲል ከነማ)

ሰለ ጨዋታው

ለኛ በጣም ትልቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ውጥረት ያለው ጨዋታ ነው። ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የምትመጣበት ስለሆነ በግማሽ ግብ እንኳን ማሸነፍ ካለ ፍላጎታችን ያ ነው። በርካታ ግቦች ማስቆጠራችን ደግሞ የበለጠ በራስ መተማመናችን እንዲጨምር ነው የሚያደርገው። እንዳየሁት በርካታ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለናል፤ ሰባተኛ ጨዋታችን ነው። ወጥ የሆነ አቋም እያሳየን ስለሆነ በጣም ጥሩ ነው ።

ስለ ቀሪ ጨዋታዎች

የኛ ስራ ከዚህ ከደረስን በኋላ ወደፊት እንደምንሄድ የሚያሳየን የቡድኑ አቅም ነው። ቡድኑ አቅም እንዳለው እያየን ነው። በሁሉም ነገር መከላከልም ማጥቃትም ላይ ጥሩ ነገር ነው ያለው። እስከ መጨረሻው ለዋንጫ እንጫወታለን ብዬ ነው የማስበው። እንዳያችሁት ሁሉም ተጫዋቾች ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ ስለሆነ ማይሳካበት ምንም ምክንያት የለም። ጥንቃቄ ግን ያስፈልጋል፤ ስታሸንፍ ሁሉን ነገር ትክክል ነህ ማለት አይቻልም። ስህተቶች አሉ እነሱን እያረምን መሆን አለበት እና ደጋፊውን ለማስደሰት ጥረት እናደርጋለን ።

ስለ ደጋፊው

ስለ ደጋፊው ምን ማለት እችላላሁ። በጣም ትልቅ ሀይል ነው። ለኔ ደጋፊው እንደምታውቁት ነው ከሜዳም ውጭ ብዙ ደጋፊ አለን። አሁን ደግሞ በጣም የተሻሻለው ሁኔታ በመመልከት ወደመደገፍ የመጡበት ሁኔታ ያ የበለጠ ሞራል ይሆናል። ባለፉት ጊዜያቶች ላይ በጨዋታ የመመሰጥ፤ ድርሻቸውን የመርሳት ነገር ነበር። አሁን ግን ትክክልኛ ደጋፊ ነው እያየን ያለነው። ማመስገን እፈልጋለሁ።

“ተጫዋቾች ተነሳሽነት አልነበራቸውም” የሱፍ ዓሊ (ጅማ አባጅፋር )

ሰለ ጨዋታው

ያው አንደ ችግርም የሚነሳ ሳይሆን ተጫዋቾች ተናሳሽነት አልነበራቸውም። ሜዳም ከገቡ በኋላ ከዚህ በፊት ያየንባቸውን ነገር አላየንባቸውም። ከእረፍት በኋላም ምንም መነቃቃት አልነበረም። ከበፊቱ ወጣ ያለ ጨዋታ ነው የተጫወትነው። እኔንም አስገርሞኛል ተጫዋቾች በየግልም ጥሩ አልነበሩም። ከዚህ በፊት ስንጠቀም ከነበረው 4-4-2 አሰላለፍ ላይ 4 ተጫዋቾች የሉም። እሱን እንደ አዲስ ነው የሰራነው። እሱም ትልቅ ተፅዕኖ ነበረው።

ስለ ተጋጣሚ

ተጋጣሚዎቻችን በጣም ጥሩ ናቸው። ኳስ መሰረት አድርገው ነው የሚጫወቱት። ወደ ግብ በመድረስም ከኛ የተሻለ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ነበር። ያ የሆነው ደግሞ የኛ ተጫዋቾች ጥሩ ስላልነበሩ ነው። ከኛ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የተሻለ ነገር አይተንባቸዋል። ይሄን ነገር ከደጋገሙት ለዋንጫ የተሻለ እድል አላቸው ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡