ሦስት ኢትዮጵያውያን የሚገኙበት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ከዕረፍት ይመለሳል

በአፍሪካ ዋንጫ መጀመር ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ወደ ውድድር መመለሱ ተከትሎ ጋቶች ፓኖም ዛሬ ወደ ጨዋታ ይመለሳል።

በግሉ ከኤል ጎና ጋር ጥሩ ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው አማካይ ጋቶች ፓኖም ዛሬ ምሽት 2:00 ዛማሌክን በመግጠም ከዕረፍት ወደ ጨዋታ ይመለሳል። በመጀመርያው የውድድር ዓመት ጥሩ ጊዜ አሳልፈው በሊጉ ወገብ ላይ መቀመጥ ችለው የነበሩት አዲስ አዳጊዎቹ ኤል ጎናዎች ቀስ በቀስ ውጤታቸው አሽቆልቁሎ በመጨረሻ ሳምንታት ላለመውረድ መጫወታቸው ይታወሳል።

በግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሌላው ኢትዮጵያዊ ኡመድ ኡክሪ የሚገኝበት ስሞሃም ከኤል ጎና በአንድ ነጥብ በልጦ ሊጉ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ሌላው ኢትዮጵያዊ ሽመልስ በቀለ የሚገኝበት ምስር አል ማቃሳም የሊግ ጨዋታዎቹ አጠናቆ በአርባ ስድስት ነጥብ በሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሊጠናቀቅ ጥቂት ተስተካካይ ጨዋታዎች የቀሩትን ይህን ሊግ አል አህሊ በ74 ነጥቦች ሲመራው ቀሪ ጨዋታ የሌለው ፒራሚድ በሰባ ነጥብ ይከተላል ፤ ከሊጉ መሪ ቀጥሎ የተሻለ የዋንጫ ዕድል ያላቸው ዛማሌኮችም አንድ ቀሪ ጨዋታ በእጃቸው ይዘው በ68 ነጥቦች በሦስተኛ ደረጃ ይገኛሉ።

ሽመልስ በቀለ ለበርካታ ዓመታት የተጫወተበት ፔትሮጀት ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ከሊጉ መውረዱ ሲያረጋግጥ ዳክልይ እና ነጎም ሌሎች ከሊጉ የወረዱት ቡድኖች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡