መቐለ እና ፋሲል የአፍሪካ ውድድር ቅድመ ማጣርያ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል

የ2019/20 የካፍ የክለብ ውድድሮች ድልድል ዛሬ ይፋ ሲሆን የኢትዮጵያዎቹ መቐለ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ የቅድመ ማጣርያ ተጋጣሚዎቻቸውን አውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሆነው መቐለ 70 እንደርታ በቅድመ ማጣርያው የኢኳቶርያል ጊኒው ካኖ ስፖርት አካዳሚን ይገጥማል። በ2014 የተመሰረተው ቡድኑ የሀገሪቱ የሊግ ውድድር አሸናፊ የሆነ ሲሆን እንደ መቐለ ሁሉ በውድድሩ ሲሳተፍ የመጀመርያው ነው።

መቐለ የመጀመርያ ጨዋታውን ወደ ኢኳቶርያል ጊኒ አምርቶ ከነሐሴ 3-5 ባሉት ቀናት ሲያደርግ የመልሱን ጨዋታ በሜዳው ከነሐሴ 17-19 ባሉት ቀናት ያደርጋል። ይህን ዙር ካለፈ ደግሞ በአንደኛው ዙር ማጣርያ መስከረም ወር ላይ ከደቡብ ሱዳኑ አትባራ እና የግብፅ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ከሚሆነው ቡድን ጋር የሚጫወት ይሆናል።

በዛሬው ዕለት ሀዋሳ ከተማን በመለያ ምቶች በማሸነፍ የኢትዮጵያ ዋንጫን ያነሳው ፋሲል ከነማ ከታንዛኒያው አዛም ጋር ተደልድሏል። ከ12 ዓመታት በፊት የተመሰረተው የታንዛኒያው ክለብ በ2018/19 የውድድር ዓመት 3ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቁ ነው በውድድሩ ውስጥ የተካተተው።

ፋሲል የመጀመርያ ጨዋታውን ከነሐሴ 3-5 ባሉት ቀናት በሜዳው ሲያከናውን የመልሱን ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ከነሐሴ 17-19 ባሉት ቀናት የሚያከናውን ይሆናል። ይህን ዙር ካለፈም በመስከረም ወር ከዛምቢያው ትሪያንግልስ እና ከብሩንዲው ቱኪንዞ ጋር ይጫወታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡