ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደጉ አራት ቡድኖች ታውቀዋል

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ሶሎዳ ዓድዋ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ጋሞ ጨንቻ እና ባቱ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጋቸውን አረጋግጠዋል። ቀሪ ሁለት አዳጊ ቡድኖች ደግሞ ቅዳሜ ይታወቃሉ።

03:00 የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ሶሎዳ ዓድዋን ከ አዲስ አበባ ፖሊስ አገናኝቶ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ 2-2 አቻ በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው ሶሎዳ ዓድዋ 5-3 በማሸነፍ ወደ ከፍተኛ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ማደግ ችሏል። ሶሎዳ ዓድዋዎች የቢጫ ካርድ ክስ በአአ ፖሊስ ላይ አስመዝግበው በተጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ኳሱን ይዘው በመጫወት ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩ ቢሆንም ወደ ፊት የማይሄድ መሐል ሜዳ ላይ ብቻ የተገደበ እንቅስቃሴ በማብዛታቸው ለጎል የቀረበ ጠንካራ ሙከራ ለተወሰኑ ደቂቃ ለማየት አልተቻለም። ከሶሎዳ ዓድዋ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት አአ ፖሊሶች 37ኛው ደቂቃ ላይ በወላይታ ድቻ ያልተሳካ ቆይታ ያደረገው ዳዊት መኮንን በቀጥታ የማዕዘን ምት ወደ ጎልነት ቀይሮ ቀዳሚ ሆነዋል። በግራ መስመር የፖሊሶችን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በጥሩ ብቃት እየተወጣ ያለው እዮብ ገ/ማርያም 42ኛ ደቂቃ ከግራ መስመር ተጫዋቾችን በፍጥነት ለጓደኞቹ ለማቀበል ወደ ጎል መሬት ለመሬት ያሻገረውን የሶሎዳ ዓደዋ ተከላካይ ቃላአብ ኪዱ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል ፖሊሶች ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተዋል።

ከእረፍት መልስ 51ኛው ደቂቃ እዮብ ገ/ማርያም በሚታወቅበት ፍጥነቱ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ቺፕ በማድረግ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶታል። ይህች ሙከራ ምናልባትም ሶሎዳን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የነበራቸውን ጥረት የሚያበላሽ ይሆን ነበር። ከዚህ በኃላ በቀሩት ደቂቃዎች ሁሉ ተጭነው የተጫወቱት ሶሎዳዎች ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ልምዱን ተጠቅሞ እየተጫወተ የሚገኘው የቀድሞ የወልዋሎ ተጫዋች አማኑኤል ዘርኡ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል አስቆጥሯል።

ወደ ኃላ አፈግፍገው መጫወታቸው እና የተጫዋች ቅያሪ ዋጋ ያስከፈላቸው ፖሊሶች አልፎ አልፎም ቢሆን ወደ ጎል በመድረስ እና ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት በጎል ያልታጀበ በመሆኑ ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ተቸግረዋል። ጥሩ እግርኳስ በተመለከትንበት በዚህ ሶሎዳ ዓድዋዎች አቻ መሆን የሚችሉበትን ዕድል ክብሮም አፅብሐ አግኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረው ኳስ የሚያስቆጭ ቢሆንም 84ኛው ደቂቃ ራሱ ክብሮም የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የአቻነት ጎል አስቆጥሯል። ጨዋታውም በመደበኛ የጨዋታ ክፍለጊዜ 2-2 አቻ በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው ሶሎዳ ዓደዋ 5-3 በማሸነፍ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጉን አረጋግጧል።

05:00 ኮልፌ ቀራንዮ ከ ሰ/ሸ/ደ/ብርሃን ያደረጉት የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በአሰልቺ ሁኔታ ያለጎል ተጠናቆ በመለያ ምት ኮልፌ ቀራንዮ 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በዘጠና ደቂቃ ውስጥ የረባ የጎል ሙከራም ሆነ ሳቢ እንቅስቃሴ ሳንመለከትበት ጥንቃቄ የበዛበት ጨዋታ ሆኖ ባለፈው በዚህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግልፅ የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ ያለ ጎል በአቻ ውጤት በመጠናቀቁ በመለያ ምት ኮልፌ ቀራንዮ 3-1 በማሸነፍ ወደ ከፍተኛ ሊግ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ መቀላቀል ችሏል። ቡድኑ ዓምና ከክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ አንደኛ ሊግ ማደጉ የሚታወስ ሲሆን በከፍተኛ ሊግ የሚወዳደር 3ኛው የክፍለ ከተማ ቡድን ይሆናል።

ቀትር 07:00 ጋሞ ጨንቻን ከ ሱሉልታ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ የውድድሩ ክስተት ቡድን በሆነው ጋሞ ጨንቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በቀድሞ የአርባምንጭ ጨጨ አሰልጣኝ መለሰ ሸመና አማካሪነት የሚመራው እና በወጣት ተጫዋቾች የተዋቀረው የጋሞ ጨንቻ ቡድን እንዲሁም ከጨዋታ ጨዋታ የቡድን አጨዋወታቸው እየተቀናጀ መምጣቱን እየተመለከትን የምንገኘው ሱሉልታ ከተማ መካከል ብርቱ ፉክክር አድርገዋል። በየጨዋታዎቹ ምርጥ አጥቂ እንደሆነ እያስመሰከረ የሚገኘው እና ወደ ፊት ጥሩ አጥቂ እንደሚሆን እየተነገረለት የሚገኘው የጋሞ ጨንቻ የፊት አጥቂ በድሉ ሰለሞን ባስቆጠረው ጎል 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ከፍተኛ ሊግኑ መቀላቀል ችሏል። በርከት ያሉ የጋሞ ጨንቻ ደጋፊዎችም በስቴዲየም ውስጥ የሚያደርጉት ድጋፍ ለተመልካቹ አዝናኝ ነበር።

09:00 ባቱ ከተማን ከቂርቆስ ያገናኘው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ባቱ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል። ዋና አሰልጣኛቸው ከማንኛውም ውድድር ስድስት ወር የተቀጣባቸው ቂርቆሶች በጨዋታው 15 ደቂቃዎች የተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም በኋላ ላይ እንቅስቃሴያቸው እየወረደ መጥቶ በባቱዎች ብልጫ ተወስዶባቸዋል። 26ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን የምናቀው በላይ ገዛኸኝ ወደ ጎል አጠንክሮ የመታውን ግብጠባቂው ዮናስ ጉደታ ሲተፋው አብርሃም ጎይቶም በቀላሉ የባቱን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።

ከእረፍት መልስ ቂርቆሶች ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም ጎል የማስቆጠር አቅማቸው ጠንካራ ባመሆኑ ተቸግረዋል። በመልሶ ማጥቃት እና በጥንቃቄ የተጫወቱት ባቱዎች ተጨማሪ የጎል ዕድል ቢፈጥሩም ሳይጠቀሙበት ቀርተው ጨዋታው ባቱ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት በማሸነፍ ከ2 ዓመታት በኋላ ከፍተኛ ሊጉን መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።

የአንደኛ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ እና የመለያ ጨዋታዎች ቅዳሜ ሐምሌ 20 ይደረጋሉ።

ወደ ከፍተኛ ሊግ ለማደግ መለያ ጨዋታዎች

3:00 አአ ፖሊስ ከ ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን

5:00
ቂርቆስ ክ/ከተማ ከ ሱሉልታ ከተማ

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች
7:00
ሶሎዳ ዓድዋ ከ ኮልፌ ቀራኒዮ

9:00
ጋሞ ጨንቻ ባቱ ከተማ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡