ሳላዲን ሰኢድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፈርሟል መባሉን አስተባበለ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ሳላዲን ሰኢድ ከኤምሲ አልጀርስ ጋር ከተለያየ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ እረፍት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ዋዲ ዴግላ ኮከብ የአካል ብቃት ደረጃውን ለመጠበቅ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ልምምድ እየሰራ ሲሆን ይህም ፈረሰኞቹ ያለፉት 5 አመታት ከሃገር ውጪ ያሳለፈውን አጥቂ ወደ ክለባቸው ለመመለስ ተስማምተዋል የሚሉ ጭምጭምታዎችም እንዲሰሙ በር ከፍቷል፡፡

በጉዳዩ ዙርያ ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት እና ከተጫዋቹ ጋር ባደረገችው ቆይታ ሳላዲን ሰኢድ እስካሁን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት ምንም አይነት ስምምነት ላይ አልደረሰም፡፡

ከክለቡ አካባቢ እንዳገኘነው መረጃ ሳላዲን ያለፉትን 5 ቀናት ከቡድኑ ጋር መደበኛ ልምምድ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን አሰልጣኙ እና ክለቡም ተጫዋቹ ላይ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ነገር ግን የሳላዲን ቀዳሚ ምርጫ ወደ ሌሎች የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ክለቦች በመሆኑ ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን ማስፈረም አልቻለም፡፡

በጉዳዩ ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን የሰጠው ሳላዲን ሰኢድም በክለቡ በኩል ያለውን ሀሳብ በማጠናከር ቅድሚያ የሚሰጠው ለሃገር ውጪ ዝውውር እንደሆነ ተናግሯል፡፡

‹‹ በኤምሲ አልጀርስ በተፈጠረው ነገር በጣም አዝኛለሁ፡፡ ስለዚህ ጉዳይም ደግሜ ማንሳት አልፈልግም፡፡ አሁን አእምሮዬን ለማረጋጋት እና እረፍት ለማድረግ ሀገሬ እገኛለሁ፡፡ የአካል ብቃቴን ለመጠበቅ እንዲረዳኝም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ልምምድ በማድረግ ላይ እገኛለሁ፡፡ ከዚህ በፊትም ለእረፍት ወደ ሃገሬ ስመጣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ልምምድ እሰራ ነበር፡፡

‹‹ በወኪሌ በኩል ከግብፅ እና ከአፍሪካ ውጪ ከሚገኙ ክለቦች ጋር እየተነጋገርኩ ነው፡፡ የግብፅ የዝውውር መስኮት እስኪዘጋ በርካታ ቀናት ይቀራሉ፡፡ በዚህ ሳምንትም አንድ ነገር ይፈጠራል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ነገር ግን ዝውውሮች የማይሳኩ ከሆነ ካለ ጥርጥር የቀድሞ ክለቤን (ቅዱስ ጊዮርጊስ) እቀላቀላለሁ፡፡ ›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የቻምፒዮንስ ሊግ የተጫዋቾች ማስዝገብያ ቀነ ገደብ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተጠናቀቀ ቢሆንም በጉዳት እና ሌሎች ምክንያቶች ከቀነ ገደቡ በኋላ የተጫዋች ለውጥ ለማድግ የሚፈቅድ አሰራር በካፍ ደንብ ላይ መኖሩ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ላይ የሚወዳደረው ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀድሞው አጥቂውን በእጁ ለማስገባት ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጎታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *