የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በመጪው እሁድ ከካሜሩን ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከአዳማ የሴቶች ቡድን ጋር ለመጫወት ወደ ስፍራው ያቀናው ብሄራዊ ቡድናችን ትላንት ተጫውቶ የተመለሰ ሲሆን ከአዳማ መልስም ዛሬ ረፋድ ላይ ልምምዳቸውን ሰርተዋል፡፡
ካሜሩንን ለመግጠም ከተዘጋጀው ቡድን ውስጥ የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚዋ አጥቂ ሴናፍ ዋኩማ ለአካዳሚዎች የልምድ ልውውጥ ተመርጣ ለ9 ቀናት ስልጠና ባለፈው አርብ ወደ ደቡብ ኮርያ ያመራች በመሆኑ ለጨዋታው እንደማትደርስ ተረጋግጧል፡፡ ሌላዋ የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ አጥቂ ትደግ ፍስሃ በዛሬው ልምምድ በቁርጭምጭሚቷ ላይ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን የመከላከያዋ ተከላካይ ሳምራዊት ኃይሉ ደግሞ በጉንፋን ምክንያት ዛሬ ልምምድ አልሰራችም፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ለእሁዱ ጨዋታ አገግመው ይደርሳሉ ተብሏል፡፡

ከ8 ቀናት በፊት ወደ ዱዋላ አቅንቶ በካሜሩን 2-1 በሆነ ጠባብ ውጤት ተሸንፎ የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በመጪው እሁድ የመልስ ጨዋታውን የሚያደርግ ሲሆን ይህን ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት ካሸነፈ አልያም በሁለት ግብ ልዩነት ካሸነፈ በተከታዩ የማጣርያ ዙር የግብጽ እና ጅቡቲን አሸናፊ የሚገጥም ይሆናል፡፡
አሰልጣኝ አስራት አባተ ከቀናት በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ካሜሩንን በሜዳቸው አሸንፈው በሴፕቴምበር 2016 ወደሚደረገው የአለም ከ17 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ አንድ እግራቸውን እንደሚያስገቡ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
