ሎዛ አበራ ለማልታው ክለብ ፊርማዋን ለማኖር ነገ ታመራለች

ሎዛ አበራ ለማልታው ክለብ ቢርኪርካራ ፊርማዋን ለማኖር ነገ 7 ሰዓት ትበራለች።

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት አጋማሽ ከሲዊድኑ ከንግስባካ ክለብ ጋር ረዘም ያለ የሙከራ ጊዜ አሳልፋ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰችው ሎዛ አበራ ፊርማዋን ለአዳማ ከተማ በማኖር መጫወቷ ይታወሳል። ዳግም ከኢትዮጵያ ውጪ የመጫወት እድል ያገኘችው ተጨዋቿ ነገ ምሳ ሰዓት ወደ ማልታ በማቅናት ለቢርኪርካራ የሁለት አመት ኮንትራት እንደምትፈርም ወኪሏ ሳምሶን ናስሮ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። 

ተጨዋቿ ወደ ማልታ ስታመራ ያለምንም የሙከራ ጊዜ እንደሆነ የገለፀው ሳምሶን ተጨዋቿ ብቃቷን እንድትጠብቅ ለተከታታይ ቀናት በትንሿ የአዲስ አበባ ስታዲየም ከባለሙያ ጋር ልምምድ ስትሰራ እንደቆየች አስረድቷል። የተጨዋቿ የጉዞ እና ሆቴል ወጪ በክለቡ እንደሚሸፈንም ገልጿል።

በ1999 የተመሰረተው ቢርኪርካራ የሀገሪቱን የሴቶች ሊግ ላለፉት ተከታታይ ሦስት ዓመታት ማንሳቱ ይታወቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡