ኢትዮጵያን ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን የደሞዝ ጣርያውን ውሳኔ በይፋ ተቃወመ

አሶሴሽኑ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፃፈው እና ለባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ፣ ለወጣቶች እና ስፖርት ኮምሽን ፣ ለማህበራት ኤጀንሲ ፣ ለሰራተኛ እና አሰሪ ኤጀንሲ እንዲሁም ለሚዲያዎች ግልባጭ ባደረገው ደብዳቤ የደመወዝ ጣሪያ ውሳኔውን ተቃውሟል።

በቅርቡ ህጋዊነቱን በማረጋገጥ የተቋቋመባቸውን ዓላማዎች ወደ ማስፈፀም ስራ የገባው የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጨዋቾችን ደመ ወዝ ጣሪያ ሀምሳ ሺህ ብር እንዲሆን ያሳለፈውን ውሳኔ በፕሬዘዳንቱ ዮሃንስ ሳህሌ ፊርማ በወጣ ደብዳቤ በመቃውም እንደማህበር የመጀመሪያ ፈተናውን ጀምሯል። ደብዳቤው የፌዴሬሽኑን የመጨረሻ ውሳኔ ከመቃወም ባለፈ ለውሳኔው የተጠራው ስብሰባ የነበረበትን የአካሄድ ግድፈትም አንቀፆችን በመጥቀስ ተቃውሟል።

በዚህም ደብዳቤው እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እየተጠቀመበት ባለው ደንብ መሰረት አሶሴሽኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሙያተኞች ማህበር አባል መሆኑን በመጥቀስ በውሳኔው ወቅት ፌዴሬሽኑ ስላቀረበው ጥናት እንደ ሙያተኞች አባል ስለጉዳዩ ቅድመ ዝግጅት እንዳያደርግ ምንም አይነት ማስረጃ እንዳልተሰጠው ያትታል። በተጨማሪም ማህበሩ በስሩ ያሉትን ሙያተኞች ወክሎ ስምምነቶችን ለማድረግ ምንም አይነት አማራጭ ያልተሰጠው መሆኑን በመግለፅ የቢሾፍቱው ስብስባ ላይ በተሳተፉ እና ውሳኔው በደረሷቸው ክለቦች አግባብነት ላይም ጥያቄ ያነሳል። በመጨረሻው የደብዳቤው ክፍልም ፌዴሬሽኑ የሄደበት መንገድ የፊፋን የስፖርት ችሎት ደንብ የጣሰ በመሆኑ ማህበሩ ህጋዊ መስመሮችን በመከተል በጉዳዩ እንደሚገፋበት አስታውቋል።

የደብዳቤውን ሙሉ ክፍል ከታች ማግኘት ይችላሉ፡-


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡