ወላይታ ድቻ የሁለት ወጣት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቀቀ

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን የቀጠረው ወላይታ ድቻ ሁለት የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል።

አስቀድሞ አማካዩን ዘላለም ኢሳያስን የመጀመሪያ ፈራሚ ያደረጉ ሲሆን አሁን ደግሞ ሰለሞን ወዴሳ እና ነጋሽ ታደሰን በሁለት ዓመት ስምምነት ወደ ክለቡ አምጥቷል።

የተከላካይ አማካዩ ሰለሞን ወዴሳ በሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን ከ17 እና 20 አመት ቡድን የተገኘ ተጫዋች ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሀዋሳን ከለቀቀ በኃላ ወደ ኢትዮጵያ መድን አምርቶ በክለቡ ጥሩ የውድድር ጊዜን አሳልፏል።

ሌላው የክለቡ አዲስ ፈራሚ ነጋሽ ታደሰ እንደ ሰለሞን ሁሉ በሀዋሳ ወጣት ቡድን የእግር ኳስ ህይወቱን ጅማሮ ያደረገ ሲሆን በሀዋሳ ዋናው ቡድን ውስጥም በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ካደገ በኃላ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ያደረገ ተጫዋች ነው።

እስከ አሁን ሦስት አዳዲስ ተጫዋችን ያስፈረሙት የጦና ንቦቹ የነባር ተጫዋቾችን ውል ለማራዘምም በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ሲሆን በአዳማ እየተደረገ ያለውን ከ20 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ እየመለከቱ የሚገኙት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በርከት ያሉ ወጣቶችን ለማሳደግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡