ለሚ ንጉሴ የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ውድድር ላይ ለመዳኘት ወደ አስመራ ያመራል

በኤርትራ አስተናጋጅነት የሚከናወነው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ውድድር ላይ እንዲመሩ ከተመረጡ ዳኞች መካከል ለሚ ንጉሴ ተካቷል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለበርካታ ዓመታት ሲመራ እና በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ጨዋታዎች ሲመራ የቆየው ለሚ ንጉሴ ነገ ስምንት ሰዓት ላይ በሚጀመረው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ዋንጫ ለመሳተፍ ወደ አስመራ ያቀናል። ባለፈው ሳምንት በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የጅቡቲው አርታ ሶላር ሰቨን እና ሱዳኑን አል ካርቱም አልዋጣኒ ያደረጉትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የመራው ዳኛው ከኢትዮጵያ ወደ ውድድሩ የሚያመራ ብቸኛው ዳኛ ነው።

በውድድሩ የሚዳኙት ዳኞች ራሷን ካገለለችው ጅቡቲ እና ሌሎች ስምንት የሴካፋ አባል ሃገራት የተውጣጡ ሲሆን አዘጋጅዋ ኤርትራ ሥስት ዳኞችን ታሳትፋለች።

ውድድሩ ነገ ስምንት ሰዓት ላይ የሚጀመር ሲሆን በመክፈቻው ኬኒያ እና ሶማሊያ ሲጫወቱ ከመክፈቻው ቀጥሎ አዘጋጇ ኤርትራ ብሩንዲን ትገጥማለች። ሁሉም የውድድሩ ጨዋታዎችም በቺቾሮ ስታዲየም የሚከናወኑ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡