ሴካፋ ከ15 ዓመት በታች| ዩጋንዳ ተከታታይ ድል ስታመዘግብ ኢትዮጵያ ነጥብ ተጋርታለች

አራተኛ ቀኑ የያዘው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ዋንጫ ዛሬም ቀጥሎ ዩጋንዳ ተከታታይ ድል ስታስመዘግብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ነጥብ ተጋርተዋል።

በስምንት ሰዓት በተካሄደው የታንዛንያ እና የዩጋንዳ ጨዋታ ዩጋንዳ 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች። ተከታታይ ሁለተኛ ድሏን ላስመዘገበችው ዩጋንዳ ግቦቹን ያስቆጠረው ደግሞ አስር ቁጥር ለባሹ እና የዕለቱ ኮከብ የነበረው ሙጣያባ ትራቪስ ነው።

በ10:30 በተካሄደው ጨዋታ በመጀመርያ ጨዋታቸው በተመሳሳይ የሦስት ለባዶ ሽንፈት ያስተናገዱት ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ተገናኝተው ነጥብ ተጋርተዋል። ደቡብ ሱዳን ከዕረፍት በፊት ግብ አስቆጥራ እየመራች ወደ ዕረፍት ብታመራም ኢትዮጵያ ከዕረፍት በኃላ አቻ የሚያደርጋትን ግብ በማስቆጠር ነጥብ ተጋርታለች። ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ስድስት ነጥብ ካላት ዩጋንዳ እና ሦስት ነጥብ ካስመዘገበችው ሩዋንዳ በመቀጠል ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡