ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ሰባት – ክፍል አራት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም በመሳጭ ትረካ ሀያ ስምተኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። የገናናዋ የእግርኳስ ሀገር ብራዚልን ታሪክ በሚያወሳው 7ኛ ምዕራፍ የሀገሬው ሰዎች “ማራካናዞ” ብለው የሚጠሩት የ1950 ዓለም ዋንጫ መቅሰፍት ተንተርሶ የተሰናዳውን ፅሁፍ አቅርበንላችኋል።


ብራዚሎች በ1950 ባዘጋጁት የዓለም ዋንጫ ውድድር ምርጥ ቡድን በማቅረብ በሁሉም ዘንድ ታዋቂነትን ያትርፉ እንጂ በፍጻሜው ጨዋታ ድል ሊጎናጸፉ አልቻሉም፡፡ መላ የሃገሪቱ ህዝብ ከጠበቀው በተጻራሪ መራር ሽንፈት ገጠማቸው፡፡ በሃገሪቱ አስከፊ ውጤት እጅጉን የደነገጠው ኔልሰን ሮድሪጌዝም ታሪካዊውን ውድቀት “የእኛ መቅሰፍት!፥ የእኛ ሄሮሺማ!” ሲል ገለጸው፡፡

በፍላቪዮ ኮስታ አማካኝነት የተሰናዳው ዲያጎናል ፎርሜሽን መጠነኛ ማስተካከያዎች ተደርጎለት በብሄራዊ ቡድኑ እንዲተገበር ታቀደ፡፡ ቀደም ሲል በቡድኑ ከመሐል አጥቂው ጎን በመጫወት ሁነኛ የፊት መስመር ተሰላፊነት (Inside-Forward) ሚና የነበረው አደሚር የመሐል አጥቂ (Centre-Forward) ኃላፊነትን የሚወጣ ተጫዋች እንዲሆን ተደረገ፡፡ በሜዳው ቁመት በግራው መስመር ወደ መሃል ተጠግቶ በመጫወት የሚታወቀው (Inside-Left) ጃየር የአጥቂ አማካይ (Ponta da lanca) ሆኖ ቀረበ፤ ዚዚንሆ ደግሞ በጥልቀት ወደኋላ ካፈገፈገ ቦታ የሚነሳ የፊት መስመር ተሰላፊነት (Deeper-Lying Inside-Forward) ተሰጠው፡፡ ፍሰቱን የጠበቀ ማራኪ ጨዋታ እና በጎነ-ሦስት ምስል በሚወከሉ ቦታዎች ላይ በሚንቀሳቀሱ ተጫዋቾች መካከል የሚደረጉ የተመጠኑ ቅብብሎች (Triangle of Passes) በፎርሜሽኑ እድገት የተገኙ ፍሬዎች ሆኑ፡፡ በ1949ኙ የኮፓ አሜሪካ ውድድር ብራዚል ከጥሎ ማለፉ በፊት ባካሄደቻቸው ሰባት ጨዋታዎች ሠላሳ ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር ወደ ፍጻሜው አመራች፡፡ በዋንጫ ጨዋታውም በፍሌይታስ ሶሊች የምትሰለጥነው ፓራጓይን 7-0 ረመረመች፡፡

የዓለም ዋንጫው ሲጀመር ዚዚንሆ ጉዳት አጋጠመው፤ ነገርግን ያለ ወሳኝ ተጫዋቿም ቢሆን ብራዚል የብዙዎችን ቀዳሚ ግምት አገኘች፡፡ በመክፈቻው ጨዋታም የሃገሪቱ ኮከቦች የሚጠበቅባቸውን ለማሳየት ግዜ አልወሰደባቸውም፤ ሜክሲኮን 4-0 ባሸነፉበት የማራከኛው ጨዋታ ለአምስት ጊዜያት ያህል የግቡ ቋሚዎች የጎል ሙከራዎቻቸውን አክሽፈውባቸዋል፡፡ እርግጥ በብሄራዊ ቡድኑ ችግሮች መስተዋል የጀመሩት ገና ስብስቡ ለሁለተኛው ጨዋታ ሪዮን ለቆ ከሲውዘርላንድ ጋር ለመጋጠም ወደ ሳኦፖሎ ባቀናበት ወቅት ነበር፡፡ በጊዜው እንደተለመደው ፍላቪዮ ኮስታ በርካታ የተጫዋቾች ቅያሪ አደረገ፤ የከተማዋን (ሳኦፖሎ) ደጋፊዎች ቀልብ ለመሳብ ሲል ሶስት የፓውሊስታ አማካዮችን ወደ ቋሚ ተሰላፊነት አመጣ፤ ምናልባት ይህ የአሰልጣኙ ውሳኔ የቡድኑን መንፈስ ረብሿል፤ ምናልባትም 1-3-3-3 ፎርሜሽንን የሚተገብረው የሲውዘርላንዶች ቬሩ የተባለው ጥብቅ የመከላከል ሥርዓት (Verrou System) ለአዘጋጇ ሃገር ተጫዋቾች እንግዳ ሆኖባቸው ይሆናል፤ የሆነው ሆኖ ብራዚሎች የዚያን ዕለት በተለመደ ብቃታቸውና በሚስብ አቀራረባቸው ሊገኙ አልቻሉም፡፡ ለሁለት ጊዜያት ያህል ጨዋታውን የመምራት ዕድል ቢያገኙም 2-2 አቻ ከመሆን የዘለለ ነጥብ አላስመዘገቡም፡፡ ይህ ውጤታቸው በቀጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ዩጎዝላቪያን የመርታት ግዴታ ደቀነባቸው፡፡

ጤንነቱ የተመለሰለት ዚዚንሆ በጡንቸኛው የመሃል አጥቂ ባልታዛር ምትክ ወደ ሜዳ ገባ፤ የእርሱ መመለስ አደሚርን በቀድሞው ነጻ-የዘጠኝ ቁጥር ሚናው (Mobile No.9) እንዲጫወት አገዘው፡፡ ይህ አሰላለፍ ከአንድ ዓመት በፊት የደቡብ አሜሪካ ሃገራት ዋንጫ ውድድር ላይ በአስደናቂ አቋም ባለ ድል የሆነውን የብራዚል ቡድን እንደገና ይመልስ ነበር፡፡ ሆኖም ከሲውዘርላንድ ጋር አቻ ሲለያይ በዲያጎናል ፎርሜሽን ጠቀሜታ ላይ ጥርጣሬ የገባው ፍላቪዮ ኮስታ ይበልጥ ቀጥተኛ የሆነው W-M ፎርሜሽንን ተቀዳሚ ምርጫው አደረገ፡፡ አሰልጣኙ የተጋጣሚ ቡድን የተከላካይ ክፍልን የሚገዳደር፣ አደጋ ተጋፋጭ፣ በሦስት የፊት መስመር ተሰላፊዎች የተዋቀረና በሜዳው ቁመት መሃለኛው ወረዳ ላይ የሚዋልል የአጥቂ ክፍል አዘጋጀ፤ ዳኒሎና ካርሎስ ባወርን የመሳሰሉ በጥልቀት ወደኋላ ተስበው የመከላከል ሒደቱ ላይ ተጨማሪ ጥንካሬ የሚሰጡ ወደ መስመር የተጠጉ የመሃል-አማካዮችንም (Half-Backs) ያዘ፤ ይህን የተሟላ የአጥቂና የተከላካይ ክፍል ያዋቀረው ኮስታ W-Mን ለመተገበር ዝግጁ ሆነ።

ማሻሻያዎች የተደረጉ ሰሞን ለውጡ ፍሬ አፈራ፤ ለፍጻሜው የሚያደርሰው ጨዋታ ከመጀመሩ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ከመልበሻ ክፍሉ መውጫ በር አናት ላይ እንደነገሩ ከተቀመጠ ወጋግራ ጋር ተጋጭቶ የመፈንከት አደጋ የደሰሰበት ራጅኮ ሚቲች የህክምና እርዳታ እየተደረገለት ስለነበር ዩጎዝላቪያ ጨዋታውን በአስር ተጫዋቾች ጀመረች፡፡ እናም ሚቲች ወደ ሜዳ ሲገባ አደሚር ብራዚልን መሪ ያደረገች ጎል አግብቶ ጠበቀው፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ዚዚንሆ የከባዱን ግጥሚያ ማሸነፊያ ግብ አስቆጥሮ የሀገሪቱን አሸናፊነት አረጋገጠ፡፡

በተክለሰውነት የገዘፉና በቴክኒክ የተካኑ ተጫዋቾችን የያዙት ዩጎዝላቮች ለአዘጋጇ ሃገር ጠንካራ ተጋጣሚ የነበሩ፡ በመሆኑ ብራዚሎች ይህን ከባድ ፍልሚያ በድል መወጣታቸው በሲውዘርላንዱ ጨዋታ ከድቷቸው የነበረውን የራስ መተማመን ድጋሚ እንዲያገኙ አስቻላቸው፡፡ በመጨረሻው ምድብ በተካሄዱ ሁለት የመክፈቻ ጨዋታዎች ብራዚሎች የተዋጣላቸው ሆነው ታዩ፡፡ ሲውዲንን 7-1፣ ስፔንን ደግሞ 6-1 ከረቱ በኋላ ብሪያን ግላንቪል “የወደፊቱን እግርኳስ የሚጫወቱ! በታክቲክ እምብዛም የሆኑ ነገርግን በቴክኒካዊ ክህሎት አስገራሚ ብቃት የሚያሳዩ!” ሲል ጻፈ፡፡

እውነትም በወቅቱ በታክቲካዊ የእግርኳስ ዳራ ብራዚሎች ብዙም አስገራሚ ነገር አላሳዩም፤ ነገርግን ኳስ ይዞ የሚጫወተው የመሐል-ተከላካይ አማካያቸው (Ball-Playing Centre-Half) ኦብዱሊዮ ቫሬላን በመጠቀም የቪቶሪዮ ፖዞን <ሜቶዶ> የአጨዋወት ሥርዓት የሙጥኝ ካሉት ኡሯጓዮች በተሻለ ደረጃ ይገኙ ነበር፡፡ ኡሯጓይ በመጨረሻው ዙር የመክፈቻ ጨዋታ ከስፔን ጋር 2-2 አቻ ተለያይታ ከሲውዲን ጋር ባከናወነችው ሁለተኛ ጨዋታዋ በመጨረሻዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ውስጥ 3-2 ለማሸነፍ ሁለት ግቦች ማስቆጠር ተጠብቆባታል፡፡

ብራዚል የውድድሩ አሸናፊ ለመሆን ከኡሯጓይ አንድ ነጥብ መጋራት በቂዋ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም የሪዮ ነዋሪ በፍጻሜው ከድል ውጪ ሌላ ውጤት ፍጹም አልጠበቀም፤ የዓለም ዋንጫው ጨዋታ በሚደረግበት ዕለት የወጣው የኦ-ሙንዶ ጋዜጣ የማለዳ ዕትም የብራዚል ቡድን ምስል ሥር ” እነዚህ የዓለም ዋንጫው አሸናፊዎች ናቸው፡!” የሚል አርዕስት ያለው ጽሁፍ ይዞ ወጣ፡፡ ቴክሴይራ ኼርዘር <ዘ-ታፍ ጌም ኦፍ ዘ-ወርልድ ካፕስ> ላይ ቫሬላ በጠዋት በሆቴሉ ውስጥ በሚገኘው የህትመት ውጤቶች መሸጫ የጋዜጣውን ርዕስ ማሳያው ላይ ተመለከተ፤ ወደ ውስጠኛው ክፍል በከፍተኛ ንዴት ዘው ብሎ ገባ፤ በመደብሩ የነበሩትን የጋዜጣውን ሁሉንም ቅጂዎች ገዝቶ ወደ ራሱ ክፍል ወሰዳቸው፤ እያንዳንዱን ገጽ በሽንት ቤቱ ወለል ላይ አነጠፈ፤ የቡድን አጋሮቹን ሰበሰበና ጋዜጦቹ ላይ ሽንታቸውን እንዲሸኑ አደረገ፡፡

ጨዋታው ከሚካሄድበት ቀን አስቀድሞ የሪዮ ሃገረ-ገዢ አንጄሎ ሜንዴዝ ደ ሞራይዝ መላ የቡድኑ አባላትን የሚያነሳሳና ከፍ ከፍ የሚያደርግ የውዳሴ መዓት አዥጎደጎደላቸው፡፡ ” እናንት ብራዚላውያን- የውድድሩ ባለድሎች እንደምትሆኑ አውቃለሁ!፤ የቡድናችን ተጫዋቾችም በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በሚሊዮን በሚቆጠሩ የሃገራችሁ ልጆች ፊት አሸናፊነታችሁን ታውጃላችሁ! በምድር ላይ አንዳችም ተወዳዳሪ የላችሁም! ዘወትር የተቀናቃኞቻችሁ የበላይ ናችሁ! ለድል አድራጊነታችሁ ከወዲሁ ምስጋናዬን አቀርብላችኋለሁ!” አላቸው ስለሚያስመዘግቡት ስኬት እርግጠኝነት በተሞላበት መንፈስ፡፡

ያኔ ጥቂትም ቢሆን ስለ ሽንፈት ሃሳብ የገባው ምናልባት ፍላቪዮ ኮስታ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ “የኡሯጓውያን ቡድን ሁሌም የተረጋጉትን ብራዚላውያን እግርኳሰኞች ይረብሻሉ፡፡ ተጫዋቾቼ እሁድ ወደ ሜዳ ሲጓዙ ቀድመው በመለያዎቻቸው ላይ የአሸናፊነታቸውን ምልክት አሰፍተው እንዳይሄዱ ሰግቻለሁ፡፡ የግል ክህሎትን ለማሳየት የሚደረግ የትርዒት ግጥሚያ’ኮ አይደለም፤ ይልቁንም ይሄም ልክ እንደ ሌሎቹ ጨዋታዎች ሊሆን ይችላል- ነገርግን ከሁሉ ፍልሚያዎች የከበደ ነው፡፡” ሲል አስጠነቀቀ፡፡

ከሁሉ ለየት ባለ መልኩ ይህን ጨዋታ ለብራዚሎች ከባድ የሚያደርግባቸው የኡሯጓውያኑ አሰልጣኝ ሁዋን ሎፔዝ ብልሃተኝነት እና ስልጡንነት ነበር፡፡ በአውሮፓ የተቀሰቀሰው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሃገራት ብሄራዊ ቡድኖቻቸውን ይዘው የልምድ ልውውጥ የሚያስገኝላቸውን የጉብኝት ጉዞዎች አገደ፤ ይህም በሌሎች ቦታዎች የተፈጠሩ የታክቲክ ዕድገቶችን የመቃረም አጋጣሚን ቀነሰ፤ ስለዚህም በደቡብ አሜሪካ በሚገኙ የእግርኳስ ተቃናቃኞች መካከል የራዮፕላተንሴን አጨዋወት ዘይቤ (Rioplatense-School) ለመከተል ተገደዱ፡፡ ሁዋን ሎፔዝ ሲውዘርላንድ ብራዚልን ያስቸገረችበትን መንገድ አጢኗል፤ እናም የእነርሱን (ሲውዘርላንድ) ሥልት ለመጠቀም ተነሳሽነት ወሰደ፡፡ አሰልጣኙ የመስመር ተከላካዩ (Full-Back) ማቲያስ ጎንዛሌዝን ወደኋላ በጥልቀት ተስቦ እንደ ጠራጊ (Sweeper) እንዲጫወት አዘዘው፤ ሌላኛውን የመስመር ተከላካይ ዩዞቢዮ ቴኼራን ደግሞ የመሃል ተከላካይነት (Centre-Back) ሚና ሰጠው፡፡ በሜዳው ስፋት የመሃሉ ክፍል በግራና ቀኝ ወደ መስመር ተጠግተው የሚጫወቱት ሁለቱ አማካዮች (Wing-Halves) ሹበር ጋምቤታ እና ቪክቶር አንድራዴ የብራዚሎቹን የመስመር አማካዮች (Wingers) ቺኮ እና አልቤርቶ ፍሬይካ ላይ ተጫዋችን-በ-ተጫዋች የመቆጣጠር ጥብቅ ክትትል (Man-Marking) እንዲያደርጉ ተነገራቸው፤ የመሃል አጥቂው (Center-Forward) ቫሬላና ከእርሱ ግራና ቀኝ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) ደግሞ ከተለመደው የማጥቃት ተጫዋቾች አመዛኝ ቦታ ወደኋላ አፈግፍገው ለካርል ራፐን <1-3-3-3> ፎርሜሽን (Verrou-System) የቀረበ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ ግትር አደራደር ተገበሩ፡፡

በዕለቱ በማራካኛ ይፋዊ የተመልካቾች ቁጥር 173,850 የደረሰ ቢሆንም በስታዲየሙ የተገኙ ታዳሚዎች ትክክለኛ አሃዝ ከ200,000 እንደሚልቅ ብዙዎች ይከራከራሉ፡፡ በከፍተኛ በጭንቀት ውስጥ ሆኖ የመርበድበድ ስሜቱን መቆጣጠር ያቃተው የኡሯጓዩ የቀኝ መስመር አጥቂ (Inside-Right) በተሻሻለው ፎርሜሽን (1-3-3-3) ደግሞ የቀኝ መስመር አማካይ (Right-Half) የነበረው ሁሊዮ ፔሬዝ የየሃገራቱ ብሄራዊ መዝሙሮች ሲዘመሩ እንኳ ራሱን በውሃ ከማርጠብ አልቦዘነም፡፡ ይሁን እንጂ ቀስበቀስ ጫናው አቅጣጫውን የመቀየር አዝማሚያ አሳየ፤ የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ብራዚል የበላይነቷን አሳየች፤ ነገርግን የመሪነት ግብ ልታስቆጥር አልቻለችም፡፡ የሎፔዝ ታክቲክ የሃገሪቱ ቡድን እንዲፈዝ ሳያደርግ ባይቀርም ሙሉበሙሉ አሉታዊ ተጽዕኖ አላሳደሩባቸውም ነበር፡፡ የብራዚሉ ጃየር በጨዋታው ሒደት የግብ ሙከራው በጎሉ ቋሚ ተመለሰበት፡፡ ሮክዌ ማስኮሊም በግላንቪል አገላለጽ ” ግብ አፋፍ ሲደርስ አካሉን እንዳሻው እያደረገ የአክሮባት ትዕይንት በሚመስል ጀብዱ እጅግ አስገራሚ ችሎታ አሳይቷል!” ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል ሲያቀኑ የውጤት ለውጥ አልታየም፥ 0-0 አቻ፡፡ የብራዚል ደጋፊዎች ጭንቀት እየናረ ሄደ፡፡

የጨዋታውን ሁኔታ ወደኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ ወሳኝ ሽግግር የተደረገው ቫሬላ የውድድሩ አዘጋጅ ሃገር የግራ መስመር ተከላካይ (Left-Back) ሆኖ የተሰለፈው ቢጎዴ ላይ ኃይለኛ ጡጫ ካሰረፈበት የሃያ ስምንተኛው ደቂቃ በኋላ እንደነበረ እንረዳለን፡፡ ሁለቱም ተጫዋቾች አጋጣሚው በጨዋታ ላይ የሚፈጠር ቀላል የአካል ንክኪ ከመሆን ያለፈ እንዳልነበር ይስማማሉ፤ ያም ሆኖ ክስተቱ ከተፈጠረበት ቅጽበት አንስቶ ቢጎዴ በስጋት እስር ተሸብቦ ፈሪ ሆኖ እንደቀረ፤ ህይወቱን ሙሉ ሲከታተለው የኖረ ማንጓጠጫ ስም ሆነበትና የጨዋታው አፈታሪክ አካል ወደመሆን ደረሰ፡፡

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በጀመረ ሁለተኛው ደቂቃ አደሚር ከኡሯጓዮች በመልስ ምት የተለጋ ኳስ ተቆጣጥሮ ለፍሬይካ አቀበለው፤ ፍሬይካ የኡሯጓዩን ተከላካይ አንድራዴ አልፎ ኳሷን ከመረብ ውስጥ ዶላት፤ ብራዚል መሪ ሆነች፡፡ በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቢሆን ኖሮ ለኡሯጓውያኑ አስደንጋጭ ይሆን ነበር፡፡ ነገርግን ብራዚሎቹን ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ስለተገዳደሯቸው ኡሯጓዮች ሙሉበሙሉ ብልጫ እንደማይወሰድባቸውና ተጋጣሚያቸውን መቋቋም እንደሚችሉ ያውቁ ነበር፡፡

ሆን ብለው ያድርጉት-አያድርጉት፥ ለማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ኡሯጓዮች የማጥቃት ሒደታቸውን በሜዳው ቁመት የቀኝ መስመሩን ታከው መተግበር መረጡ፡፡ ይህ መስመር ብራዚላውያኑ ተጫዋቾች የዲያጎናል ፎርሜሽኑን መዘውር የሚያሽከረክሩበት የሜዳ ክፍል ሲሆን ከሁለቱ የመሃል-መስመር ተከላካዮች (Half-Backs) መካከል ወደፊት ተጠግቶ የሚጫወተው ዳኒሎ የሚገኘውም እዚሁ ስፍራ ላይ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ የመከላከል አደረጃጀታቸውን በቀላሉ ሊይዙ የማይችሉበትና ይበልጡን ተጋላጭ የሚሆኑበት ድክመት በተደጋጋሚ ይፈጠር ጀመር፡፡ ብራዚል W-Mን ስትተገብር ዳኒሎ በነጻነት ወደፊት እየሄደ ሲንቀሳቀስ ከጀርባው ተጋጣሚ ቡድን ጥቃት ሊያደርስ የሚያስችለውን ሰፊ ክፍተት ይተዋል፤ በዲያጎናል ፎርሜሽን የዳኒሎ ተጣማሪ የሆነው ቢጎዴ ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክልል ተጠግቶ ከመንቀሳቀስ ይልቅ እንደ ቀጥተኛ የግራ መስመር ተከላካይ (Orthodox Left-Back) ስለሚጫወት ሚናውን በቶሎ ተላምዶታል፡፡ የኡሯጓይ ደካማ ጎን ፣ ከጀርባው ገበጥ ያለ ቁመና የያዘው የሃገሪቱ የቀኝ መስመር አማካይ (Right-Winger) አልሲዴ ጂጊያ በጨዋታው ይህን ያህል በነፃነት የሚቦርቅበት ሰፊ ቦታ እንደሚያገኝ አስቦ አይደለም አልሞም የሚያውቅ አይመስልም፡፡

የኡሯጓዮቹ ያልታሰበ ዱብዕዳ እስሚወርድባት ቅጽበት ድረስ ብራዚል ዋንጫውን ለማንሳት ሃያ አራት ደቂቃዎች ብቻ ይቀራት ነበር፡፡ ከጎሉ በኋላ ተጽዕኖው እየጨመረ የመጣው ቫሬላ ወደፊት እየተጠጋ ቅብብሎችን ለጂጊያ ያሰራጭ ጀመር፡፡ ቫሬላ- እንዳሻው የሚከንፍበት ሰፊ ክፍተት አገኘ፣ ቢጎዴ ወደ እርሱ እየቀረበ መሆኑን አጣራ፤ ጠበቀና ቴክኒካዊ ችሎታውን በመጠቀም አታሎ አለፈው፤ እግሩ ሥር የያዘውን ኳስ ለሁዋን ቺያፊኖ በቀላሉ አሳለፈለት፤ ቺያፊኖ ስል ሆነ፤ ለእርሱ በቀረበው የግቡ ቋሚ (Near-Post) በኩል ኳሷን ሰደዳት፤ ኡሯጓውያኑ የመጀመሪያ ጎላቸውን አገኙ፡፡ ከጨዋታው በኋላ የሽንፈቱ ማማከኛዎች መዘርዘር ሲጀምሩ ገና ተመልካቹ ከስታዲየሙ አልወጣም ነበር፡፡ ፍላቪዮ ኮስታ “በማራካኛ ያረበበው ጸጥታ ተጫዋቾቻችንን ድንጋጤ ላይ ጣላቸው፡፡” አለ፡፡ “ተጫዋቾቹ የማራካኛ ታዳሚን ድጋፍ የሞትና የሽረት ጉዳይ ሲያደርጉትና የተመልካቹን ‘አለሁ!’ ባይነት እጅጉን ሲሹ የማራካኛ ምላሽ ግን ዝምታ ብቻ ሆነባቸው፤ በእግርኳስ ስታዲየም ድባብ የመተማመን ሁኔታ ውስጥ ፈጽሞ ራስህን ማግኘት የለብህም፡፡” ሲል የሙዚቃ ባለሙያው ቺኮ ብዋርኬ የታዘበውን ተናገረ፡፡

በፍጻሜው አቻ መለያየት ለብራዚሎች በቂ ነበር፡፡ ይሁንና የጨዋታው ፍጥነትና የጋለ ስሜት መልሶ ራሳቸውን አስቸገራቸው፡፡ ከአስራ ሶስት ደቂቃዎች በኋላም ጂጊያ በኡሯጓዮች ቀኝ መስመር ኳስ ተቀበለ፤ ይህን ጊዜ ቢጎዴ ከቡድን አጋሮቹ ተነጥሎ ቢሆንም ቅርቡ ስለነበር አጥቂው ኳሷን ለፔሬዝ መልሶ አቀበለው፤ ኡሯጓዮች በጫና ብዛት መርበድበዳቸውን ዘነጉት- ጃየርን ተገዳድሮ ካለፈው በኋላ ኳሳሷን ከቢጎዴ ጀርባ መልሶ ለጂጊያ አደረሰለት፡፡ ጂጊያ የሚችለውን ያህል በፍጥነት ወደ ኳሷ ከነፈ፤ የብራዚሉ ግብ ጠባቂ ሞአክር ባርቦሳ በረጅሙ ተሻጋሪ ኳስ ይልካል ብሎ ሲጠብቅ አጥቂው በቄንጠኛ ምት በድጋሚ በሚቀርበው የጎሉ ቋሚ ሥር ኳሷን ዶላት፡፡ ፍጹም የማይታሰበውም ሆነ፤ እናም ብራዚሎች ሳይሆኑ ኡሯጓዮች የአለም ዋንጫ አሸናፊነትን ክብር ተቀዳጁ፡፡

በ1889 ከቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ተላቃና ነጻነቷን ተጎናጽፋ የሃገርነት ቁመናን መያዝ የጀመረችው ብራዚል በጦርነት አውድማ ተገኝታ አታውቅም፡፡ ሮድሪጌዝ የ1950ውን የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለሃገሩ የሄሮሺማ አምሳያ ስለመሆኑ ሲናገር ሃገሪቱ በታሪክ ያጋጠማት እጅግ ከባዱ መቅሰፍት እንደሆነ ለማስረዳት ሲሻ የተጠቀመው ገለጻ ነው፡፡ <አናቶሚ ኦፍ ዲፊት> በተሰኘው መጽሃፉ ፓውሎ ፔርዲጋኦ በመጠኑም ቢሆን ስሜት በሚነካ አገላለፅ ተመሳሳይ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ ደራሲው የመጽሃፍ ቅዱስ ጥልቅ ማብራሪያ የሚሰጥ ያህል ለጨዋታው ሰፊ ትንታኔ ለማቅረብ ይረዳው ዘንድ ፍጻሜውን በታላቅ ተመስጦ በተደጋጋሚ ተመልክቶታል፤ የፍልሚያውን አጠቃላይ የራዲዮ ቀጥታ ስርጭትም በወረቀት ገልብጦታል፡፡ “በታሪክ ከታዩ ብሄራዊ የቀውስ አብነቶች በሙሉ የ1950ው የዓለም ዋንጫ እጅግ ውቡና በደስታ የተሞላው ነው፡፡ በዓለም ግዙፉ የሃሩር ክልል ውስጥ አልያም በሁለት የሃሳብ መስመሮች መካከል በሚገኙ ሃገራት የተከሰተው ትልቁ የመሸናነፍ (Waterloo of the Tropics!) ውጤት ይመስለኛል፤ ሽንፈቱ የብራዚል ጣዖታት በሰይጣን የተደመሰሱበትን ከፍተኛ የውድመት አፈ-ታሪክ (Gotterdammerung) ይወክላል፡፡ ሽንፈቱ መደበኛ እውነታን ወደር ወደሌለው ትረካ የቀየረ ነበር፡፡ በሰዎች ምናብ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የሚኖር እና ያደገ አስደናቂ ታሪክ ነው፡፡” በማለት ጻፈ፡፡

ቢጎዴ፣ ባርቦሳና ዩቬናል የውድቀቱ ተጠያቂዎች ሆኑ፡፡ እነዚህ ሶስት የብራዚል ተጫዋቾች ምናልባት የአጋጣሚ ጉዳይ ባይሆንም ጥቁር ነበሩ፡፡ በ1963 ባርቦሳ የዚያን ጨዋታ እኩይ መንፈስ ከአዕምሮው ለማስወጣት በሚያደርገው ጥረት ጓደኞቹን የፍም ጥብስ ጋብዞ ያን ገደቢስ የማራካና ግብ ቋሚዎች የማቃጠል ዝግጅት አደረገ፡፡ ይሁን እንጂ ውርደትና በሰዎች ዘንድ ሥር የሰደደውን ጥላቻ ሊያመልጥ አልቻለም፡፡ ከዚያ አስከፊ ሽንፈት ሃያ ዓመታት በኋላ  ባርቦሳን በሱቅ ውስጥ ሲገበያይ ያየች አንዲት ሴት ለልጇ-ጣቷን ወደ ባርቦሳ እያመላከተች “ተመልከተው! ተመልከተው! መላ ብራዚላውያንን ያስለቀሰው ሰው ያውልህ!” አለችው፡፡

በ2000 ህይወቱ ከማለፉ ጥቂት ቀናት በፊት ባርቦሳ እንዲህ አለ፡፡ ” በብራዚል ለከፍተኛው ወንጀል የሚወሰነው የቅጣት ፍርድ የሰላሳ ዓመት እስር ነው፡፡ እኔ ግን ለሃምሳ ዓመታት ተሰቃየሁ፡፡” በእውነቱ የባርቦሳ ድርጊት ስህተት ሊሆን ይችላል፤ ሌሎች አበይት መንስኤዎች ይፈለጉ ከተባለ ግን ዚዚንሆ በጨዋታው ብራዚል W-M ፎርሜሽን መተግበሯ ከስህተቶች ሁሉ የከፋው ስለመሆኑ ይሟገታል፡፡ ” በፍጻሜውና ከሱ በፊት ባደረግናቸው ሦስት ጨዋታዎች በተጫዋችነት ህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በW-M ፎርሜሽን ተጫወትኩ፡፡ ስፔይን በW-M ተጫወተች፤ ሲውዲን በW-M ተጫወተች፤ ዩጎዝላቪያ በW-M ተጫወተች፤ እነዚህ ሶስት W-M የተገበሩ ሃገራትን አሸነፍናቸው፡፡ ኡሯጓይ ግን በW-M አልተጫወተችም፤ ይልቁንም ብሄራዊ ቡድኗ አንድ ለብቻው ተነጥሎ፣ በጥልቀት ወደኋላ ተስቦና ለበረኛው እጅጉን ቀርቦ የሚጫወት ተከላካይ (Deep-Back) እና ከእርሱ ፊት ሌሎች ተከላካይ ተጫዋቾችን አሰለፈች፡፡” ሲል ለቤሎስ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ በሰፊው አብራርቷል፡፡ በእርግጥ ተዘንግቶ ሊሆን ይችል ይሆናል እንጂ በዚዚንሆ የተጠቀሰው የመከላከል አወቃቀር (Defensive-Base) ብራዚል የ1919ኙን የደቡብ አሜሪካ ዋንጫ ስታሸንፍ የተጠቀመችበት ሲስተም ነበር፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም ዘጠኝ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡