አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በፋሲል ተካልኝ ምትክ ማንን ረዳታቸው ያደርጉ ይሆን?

ያለፈውን አንድ ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የባህር ዳር ከተማ ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ማንን ቀጣይ ረዳታቸው እንደሚያደርጉ አነጋጋሪ ሆኗል።

የብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የፋሲል ተካልኝን ምትክ ለመተካት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሁለት ምክረ ሀሳቦች እንደቀረበላቸው ሰምተናል።

የመጀመርያው ረጅም ዓመት በአሰልጣኝነት የቆዩ ቢሆኑ ካላቸው ልምድ በመነሳት ብሔራዊ ቡድኑን ሊጠቅሙ ይችላሉ በማለት እንደ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም፣ ወርቁ ደርገባ፣ ዻውሎስ ጌታቸው፣ አጥናፉ ዓለሙ እና ግርማ ሐብተዮሐንስን ምክትል አሰልጣኝ ቢያደርጉ መልካም ነው የሚለው ምክረ ሀሳብ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ የቀረበው ደግሞ ወደ ፊት ረጅም ዓመት ብሔራዊ ቡድኑን ሊያገለግሉ የሚችሉ ፣ አቅማቸውን የሚያሳድጉ እና ልምድ እያገኙ ሲሄዱ ብሔራዊ ቡድኑን ማጠናከር የሚችሉ ወጣት አሰልጣኞችን ማድረጉ የተሻለ ነው በሚል እንደ አንዋር ያሲን፣ ዕድሉ ደረጄ፣ እስማኤል አቡበከር እና ካሊድ መሐመድን ቢመለከቱ የሚል ሀሳብ ቀርቦላቸዋል።

እስካሁን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ለመለያየት የመልቀቂያ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ያላስገቡ በመሆናቸው ከአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጋር አብረው በቀጣይ ጨዋታዎች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ሲገመት የመልቀቂያ ደብዳቤ ካስገቡ በኋላ በሂደት ተተኪ ም/አሰልጣኝ ሊያሳውቁ እንደሚችሉ እየተነገረ ይገኛል። ይህም ቢሆን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ በምክትል አሰልጣኝ አድርጎ ለመሾም ቀዳሚ ምርጫቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዕውቁ ተጫዋች በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ዋና አሰልጣኝ በመሆን እያገለገለ የሚገኘውን አንዋር ያሲን እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው ሰምተናል።

* በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮች ካሉ እየተከታትለን የምናሳውቅ መሆናችን ከወዲሁ እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡