ወልዋሎ የአራት ተጫዋቾች ዝውውር አጠናቀቀ

በዝውውሩ በስፋት እየተሳተፉ የሚገኙት ወልዋሎዎች ከወር በፊት ቀድመው የተስማሙት ኢታሙና ኬይሙኔ ፣ ዓይናለም ኃይሉ ፣ ኬኔዲ አሺያ እና ጆናስ ሎሎን አስፈርመዋል።

የእግር ኳስ ህይቱ በተወለደበት ከተማ ዓዲግራት ጀምሮ ሃገሩን ለማገልገል ወደ መከላከያ ሰራዊት ባቀናበት ወቅት ባሳየው ጥሩ አቋም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎም መከላከያን የተቀላቀለው ተከላካዩ ዓይናለም ኃይለ ከዚህ ቀደም ለደደቢት፣ ዳሽን ቢራ፣ ፋሲል ከነማ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መጫወቱ ይታወሳል።

ሌሎች ወልዋሎ የተቀላቀሉት ናሚቢያዊያኑ ኢታሙና ኬይሙኔ እና ጆናስ ሎሎ ናቸው። ኢታሙና ባለፈው ዓመት ከብርቱካናማዎቹ ጋር የተሳካ ቆይታ የነበረው ተጫዋች ሲሆን በግብፁ የአፍሪካ ዋንጫም ተሳታፊ እንደነበር ይታወሳል። ሌላው አዲስ የቢጫ ለባሾቹ ፈራሚ ጆናስ ሎሎ ሲሆን ከኢታሙና ቀጥሎ በፕሪምየር ሊጉ የተጫወተ ሁለተኛው ናሚቢያዊ እንደሚሆን ይጠበቃል።

አራተኛው የወልዋሎ ፈራሚ ከዚ በፊት በሲዳማ ቡና ቆይታ የነበረው ኬኔዲ አሺያ ነው። ተጫዋቹ በወቅቱ ከፍተኛ ክፍያ በ2009 ክረምት ክለቡን ቢቀላቀልም ብዙም ሳይቆይ መለያየቱ ይታወሳል።

ቡድኑን በአዲስ መልክ እያዋቀረ የሚገኘው ወልዋሎ እስካሁን 13 ተጫዋቾች አስፈርሟል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡