ጅማ አባጅፋር የተጫዋቾች ደሞዝ መዘግየት ችግር በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደሚቀረፍ ገለፀ

የጅማ አባጅፋር ተጫዋቾች ደሞዝ አለመከፈሉን በማስመልከት ለፌዴሬሽኑ በድጋሚ የአቤቱታ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙርያ የክለቡን አመራሮች አናግራ ችግሩ በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚቀረፍ አስታውቀዋል።

የበጀት እጥረቱ በጅማ አባጅፋር ላይ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን አብዛኛዎቹ የሀገራችን ክለቦች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የጠቆሙት የክለቡ አመራሮች የተጫዋቾቹ ደሞዝ እስካሁን የዘገየበት ምክንያት ዘለቄታዊ የገቢ ምንጭ የሚሆኑ ሥራዎች ላይ ትኩረት በመደረጉ እንደሆነና በዚህም ዙርያ ክለቡ በቅርቡ ለሚዲያ ይፋ እደሚያደርግ ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለት የአንድ ወር ደሞዝ እንደገባላቸው የገለፀው ክለቡ በቀጣይ ቀናት ውስጥ ቀሪውን ክፍያ ሙሉ ለሙሉ እንደሚያጠናቅቁ፤ የክለቡን ስምና ዝና ለመጠበቅ እስከ ዛሬ ድረስ በትዕግስት ለጠበቁን የክለቡ ታማኝ ተጫዋቾችም ምስጋናቸውን እንደሚያቀርቡ ገልፀውልናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ