“በውድድሩ ላይ ህግ የሚባል ነገር የለም” የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ

የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተደረገ ሲገኝ ኢትዮጵያም ከምድብ ሁለት ባደረገቻቸው ሁሀለቱም ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዳ ወደ ሩብ ፍፃሜ የመግባቷ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል

በምድብ ሁለት ከዛንዚባር ታንዛኒያ እና ኬንያ ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ በታንዛኒያ 4-0 ትላንት ደግሞ በዛንዚባር 2-1 በመሸነፍ ከኬንያ ጋር የምታደርገው የመጨረሻ ጨዋታ እየቀራት ከውድድሩ መሰናበቷን መመረጋገጧን ተከትሎ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ ለሶከር ኢትዮጵያ የዕድሜ ችግር እና በሴካፋ ውስጥ ወገንተኝነት መታየቱ የውድድሩን ይዘት አበላሽቶታል ይላሉ፡፡

አሰልጣኙ የሰጡትን ሀሳብ እንደሚከተለው አቅርበነዋል

“አሳዛኝ ተሸናፊ ሆነናል፤ በውድድሩ ላይ ስንሳተፍ ወጣቶችን በደንብ ለማሳየት እንዲረዳን ነው። በዚህ ውድድር ላይ ሳሩ ለኛ ቢከብደንም ለነሱ ግን አልቸገራቸውም። በእንቅስቃሴ ረገድ በሁለቱም ጨዋታ ብልጫ ነበረን። ከድቻ፣ ከሀዋሳ እና ከሌሎችም ቦታዎች የመጡ ተጫዋቾች የሚያሳዩት ነገር በሙሉ ለእኔ ደስታን ፈጥሮልኛል፤ ተተኪ እንዳለንም ያሳየን ውድድር ነው።

” ውድድሩ ትልቅ አላማ ቢኖረውም ህግ የሚባል ነገር ግን የለውም። አንደኛ ከእድሜ አንፃር ከእኛ ዛንዚባር እና ሶማሊያ ውጪ በትክክለኛ ዕድሜ ለውድድሩ የቀረበ የለም። የMRI ምርመራ ባለመኖሩ ተቸግረናል። የዕድሜ ጉዳዩ ሳይፈታ ደግሞ 10:00 ትጫወታላቹ ተብለን ቀድሞ ሰዓት ይነገረን እና ተቀይሮ 7:00 ያደርጉብናል። ለምን ተቀየረ ስትል መልስ ሳይሰጡህ ተገደህ ትጫወታለህ።

” በሁለቱም ጨዋታችን ጥሩ ነበርን። በተለይ በመጀመሪያው የታንዛኒያ ጨዋታ ሰባት የተጋጣሚያችን ተጫዋቾች ዕድሜያቸው ከፍ ያለ ሲሆን ፓስፖርት ደግሞ የላቸውም። ለምን ብለን ስንጠይቅ ሴካፋ ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ ብሎን ምላሽ ሰጥቶናል። ታዲያ ይሄ ውድድር ለምን ተዘጋጀ? ህጉ ውሸት ነው ማለት ነው። ይህ ሁሉ ግን ሊከሰት የቻለው ሴካፋ ውስጥ የኢትዮጵያ ተወካይ ስለሌለ ነው። ዕርስ በዕርሳቸው ሲግባቡ ኢትዮጵያን የወከለ አለመኖሩ በእጅጉ ከብዶናል።”

ኢትዮጵያ የመጨረሻ የምድቡን ጨዋታ ነገ ከኬንያ ጋር 7:00 ላይ ታደርጋለች፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ