የቀድሞው የኢንተር ሚላን ወጣት ቡድን ተጫዋች ለፋሲል ከነማ ፈረመ

ፋሲል ከነማ የሙከራ ዕድል ሰጥቶት የነበረው መልካሙ ታውፈርን በአንድ ዓመት ውል አስፈርሟል።

በአንድ ወቅት ከጣልያን ተስፈኛ ታዳጊዎች መካከል ስሙ ሲጠቀስ የነበረው መልካሙ ከኢንተር ታዳጊ ቡድን ከለቀቀ በኋላ አርዛኬና ለተባለ ቡድን ሲጫወት ቆይቷል። ከዚህ ቀደም በሌስተር ሲቲ ሙከራ ያረገውና ከግብፅ ኤል ጋይሽ እና ከእስራኤል ክለቦች የመጫወት ዕድሎች አግኝቶ እንደነበር የሚናገረው የአጥቂ አማካዩ ወደ ትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ ተመልሶ መጫወትን እንደመረጠ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል። “ለፋሲል ከነማ መፈረሜ ጣሊያን ከነበርኩባቸው 19 ዓመታት የበለጠ ደስታ ሰጥቶኛል። አላማዬ ፋሲል ከነማን ማገልገል እና በብሄራዊ ቡድንም ኢትዮጵያን መጥቀም ነው።” ብሏል።

በጎንደር ደብረታቦር ከተማ ተወልዶ ገና በሦስት ዓመቱ በማደጎ ወደ ጣሊያን ያመራው መልካሙ የጣሊያን ዜግነት ያለው ሲሆን ለጣሊያን ከ16 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል። የኢንተር ሚላን ከ17 ዓመት በታች ታዳጊዎች ቡድን አምበልም ነበር።

ተጫዋቹ እና ፋሲል በአንድ ዓመት ውል ከስምምነት ላይ የደረሱት ከሳምንታት በፊት ቢሆንም ከዜግነት ጋር በተያያዘ ያለለቁ ጉዳዮች በመኖራቸው የፊርማ ጊዜው መዘግየቱን ወኪሉ ጢሞቲዮስ ባዬ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል።


© ሶከር ኢትዮጵያ