የኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ የወዳጅነት ጨዋታ ነገ ይደረጋል

ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ለ2020 ቻን ውድድር ማጣርያ ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ ነገ 10:00 በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የወዳጅነት ጨዋታ ያከናውናሉ።

በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ዋሊያዎቹ ማክሰኞ አመሻሽ ባህር ዳር በመግባት ልምምዳቸውን አከናውነዋል። ረቡዕ በቀን ሁለት ጊዜ ከሃሙስ ጀምሮ ደግሞ በቀን አንድ ጊዜ የተግባር ላይ ስራቸውን ያከናወኑት ዋሊያዎቹ በጉዳት ምክንያት ያሬድ ባዬን ማያሰልፉ ሲሆን በተጨማሪም ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው መጠነኛ ጉዳት ላይ በመገኘቱ ልምምድ በአግባቡ እንዳልሰራ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ከስብስቡ ውጪ ይሁን አይሁን እንዳልታወቀ ተገልጿል። በዩኒሰን ሆቴል ማረፊያውን ያደረገው ቡድኑ ዛሬ ረፋድ 4 ሰዓት ላይም የመጨረሻ ልምምዱን በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም አከናውኗል።

ተጋጣሚያቸው ዩጋንዳዎች ከትላንት በስትያ ጨዋታው ወደሚደረግበት ባህር ዳር በመግባት ልምምዳቸውን አድርገዋል። በጆናታን ሚክንስትሪ የሚሰለጥኑት ዩጋንዳዎች ዛሬ ጨዋታቸውን በሚያደርጉበት ሰዓት (10:00) ቀለል ያለ ልምምድ አድርገዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ