ኢትዮጵያ መድን ለቀረበበት ቅሬታ ምላሽ ሰጥቷል

የከፍተኛ ሊግ ተካፋይ የሆነው ኢትዮጵያ መድን 8 የቀድሞ ተጫዋቾች ከቀናት በፊት የአንድ ቀን ልምምድ አልሰራችሁም በሚል በክለቡ የተወሰነባቸው የቅጣት ውሳኔ ተገቢ አይደለም በሚል ለፌደሬሽኑ ስለማቅረባቸው ዘግበን ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይም ክለቡ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ክለቡ ባደረሰን ምላሽ መሠረት ከቀናት በፊት ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት ለፌዴሬሽኑ ቅሬታ ያሰሙት ተጫዋቾች በሙሉ በክለቡ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ በፈፀሟቸው የሕግ ጥሰቶች የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ስለመሆኑ ገልፀው፤ ክለባቸው ላይ የቀረበው አቤቱታ መሠረተ ቢስና የሕግ አግባብ የሌለው ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡

ስለጉዳዩ ሲያስረዱም ቅሬታቸውን ካሰሙት ተጫዋቾቹ መካከል አብዛኛዎቹ በክለቡ በነበራቸው ቆይታ የተለያዩ የዲሲፕሊን ግድፈት የነበረባቸው ስለመሆኑም አስረድተዋል። ለማሳያነትም ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል በጨዋታ ወቅት የእለቱ አልቢትርን ፀያፍ ስድብ በመሳደብ በቀይ ካርድ የተሰናበተ በዚህም ክለቡም በፌዴሬሽኑ ከተላለፈበት ቅጣት በተጨማሪ የራሱን ቅጣት ያሳለፈበት ፤ በተጫዋቾች መኖሪያ ካምፕ ውስጥ የሚገኝ ቁሶች ላይ ውድመት የፈፀመ እንዲሁም ቡድኑ ከመጀመሪያው ዙር መጠናቀቅ በኃላ በነበረው የእረፍት ወቅት መጠናቀቅ መልስ ሪፓርት ከማድረጊያ ወቅት ለ15 ያክል ቀናት ዘግይቶ መምጣትን የመሳሰሉ ከፍተኛ የህግ ጥሰቶችን የፈፀሙ ተጫዋቾች እንደሚገኙበት አስረድተዋል። በዚህም የተነሳ ክለቡ ለተጫዋቾቹ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ወቅቶች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ስለመስጠቱም ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ እነዚሁ በቅሬታ ደብዳቤው ላይ ስማቸው የሰፈሩት ተጫዋቾች በሰኔ 5 ቀን 2011 የክለቡ አመራር ቦርድ በወቅቱ የነበሩትን የክለቡ ዋና አሰልጣኝን ማሰናበቱን ተከትሎ በማግስቱ በክለቡ የልምምድ ስፍራ በነበረው መደበኛ የልምምድ መርሃግብር ላይ ከክለቡ እውቅና ውጭ አድማ በመምታት ሳይገኙ ቀርተዋል ፤ ክለቡም ባደረገው ማጣራት ይህንን ድርጊት ከጀርባ በመሆን አስተባበረዋል እንዲሁም በቀጥታ ተሳታፊ ናቸው ብሎ ባመነባቸው እነዚሁ ተጫዋቾች ላይ የክለብ ቦርድ አመራር ከክለቡ በይፋ እንዲሰናበቱ መወሰኑን ገልፀው ከዚህም ውሳኔ ማግስት በ7/2/12 ለፌዴሬሽኑ ቅሬታቸውን ካሰሙት ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ በይፋ የመልቀቂያ ደብዳቤ የወሰደ ሲሆን የተቀሩት ተጫዋቾች ደግሞ በፈፀሙት ጥፋት በክለቡ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡

ተጫዋቾቹ ይህን ጥያቄ ለፊዴሬሽኑ ከማቅረባቸው በፊት ክለቡ በራሱ ሕገ ደምብ መሠረት ያስተላለፈውን ውሳኔ ለፌዴሬሽኑ ያሳወቀ ሲሆን በጉዳዩ ዙርያም አስፈላጊ የሰነድ ማስረጃዎቹን ከቅጣትና ማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች ጭምር ለፌደሪሽኑ ማስገባታቸውን ገልፀዋል፡፡

በክለቡ ምላሽ ላይ ሌላው ክለቡን እጅግ ያሳዘነው ክስተት ደግሞ ቅሬታቸውን ካሰሙት ተጫዋቾች መካከል የተወሰኑት ተጫዋቾች በክለቡ በነበራቸው ቆይታ በውስጥ ሰነዶች ላይ የሚገኙት የተጫዋቾቹ ፊርማና ለፌዴሬሽኑ ገቢ በተደረገው የቅሬታ ደብዳቤ ላይ የሰፈረው ፊርማ የተለያዩ ስለመሆናቸው ክለቡ በእጁ የሚገኙ ሰነዶችን ለማስረጃነት በማቅረብ ይህንን የማጭበርበር ድርጊት ከፌዴሬሽኑና ከሌሎች የፍትህ አካላት ጋር በመሆን የማጣራት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አያይዘው ገለፀዋል፡፡

በመጨረሻም የእግርኳሱ መርህ በሚፈቅደው መሠረት የትኛውም ክለብ በውድድር ወቅት በአሰልጣኙ ደስተኛ ባልሆነበት ቅፅበት አሰልጣኙን የማሰናበት መብት እንዳለው የሚታወቅ መሆኑና ተጫዋቾች በውሳኔው ላይ ተቃውሞ ቢኖራቸውም እንኳን ቅሬታቸው ህግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ ማቅረብ እንጂ ወደ አድማ ማምራታቸው አግባብ ነው ብለው እንደማያምኑ ገልፀው ክለቡ ለስፖርት መርህ በፅኑ መከበር እንደሚቆምና ከመርህ ውጭ ለሚደረጉ ማናቸውም ድርጊት ክለቡ እንደማይደራደር አስታውቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ