ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል

ሀላባ ከተማ ሦስት የቀድሞ ተጫዋቾቹን እና አንድ የውጪ ዜጋ ጨምሮ ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ተክሉ ታፈሰ ቡድኑን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው። ከዚህ ቀደም ለሀላባ ከተማ ተጫወተው ተክሉ በኢትዮጵያ ቡና፤ ያለፉትን ስድስት ዓመታት ደግሞ በወላይታ ድቻ ሲጫወት የቆየ ሲሆን በክረምቱ ወደ ደቡብ ፖሊስ ለማምራት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ወደ ቀድሞ ክለቡ የሚመልሰውን ዝውውር አድርጓል።

በአማካይ ስፍራ ላይ ወደ በርበሬዎቹ ካመሩት መካከል ስንታየሁ አሸብር አንዱ ነው። በ2011 የውድድር ዓመት ሆሳዕና ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ትልቅ አስታዎፅኦ ያበረከተው ስንታየሁ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ሀላባ ተመልሷል። እንደ ስንታየው ሁሉ ጌታሁን ይልማም ከሆሳዕና ወደ ቀድሞ ቡድኑ ሀላባ ተመልሷል።

ከዚህ ቀደም በወላይታ ድቻ፣ ኤሌክትሪክ ጅማ አባ ጅፋር እና ኒያላ የተጫወተው አሸናፊ ሽብሩ ሌላው የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ሲሆን የመስመር አጥቂው ሄኖክ አዱኛ ከአንደኛ ሊጉ አማራ ፖሊስ ወደ ቡድኑ ተቀላቅሏል።

ስድስተኛው የቡድኑ ፈራሚ ጆን ማሉማ ነው። ካሜሩናዊው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ከሀገሩ ክለብ ዮንግ ስፖርት አካዳሚ ነው ክለቡን የተቀላቀለው።

ሀላባ ከተማ ለ2012 የውድድር ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ብቅ ለማለት እንዲሁም በሜዳቸው በስፖርታዊ ጨዋነት ቡድኖችን ለማስተናገድ ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ምክክር እንዳደረጉ የቡድኑ ስራ አስኪያጅ ፈይዱ ፍቃደ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ