የአሰልጣኞች ገጽ | አብርሀም ተክለሃይማኖት፡ (የመጨረሻ ክፍል – ስለ አሰልጣኞች )

የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ በሚዳስሰው “የአሰልጣኞች ገፅ” አሰልጣኝ አብርሀም ተክለሃይማኖትን በተከታታይ እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። ዛሬ በመጨረሻው ክፍል መሰናዷችን ስለአሰልጣኞች አንስተን ቆይታ አድርገናል።


1970ዎቹ አጋማሽ ላይ የነበሩ የአዲስ አበባ አሰልጣኞች ኳስ የሚችለው የአዲስ አበባ፣ የአስመራና የድሬደዋ ልጅ ብቻ ይመስላቸው ነበር፡፡የሚል ቅሬታ እንድትሰጥ የገፋፋህ ምክንያት ያለመመረጥህ የፈጠረብህ ስሜት ይሆን?

★ እኔና ገብረመድህን ኃይሌ ከጎጃም፣ ሙሉጌታ ከበደ ከደሴ፣ አቡሽ ከወሎ ተጠርተን መጣን፡፡ ያኔ ደሴ ውስጥ እጅግ በጣም ምርጥ-ምርጥ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ስዩም ከበደ ከእኛ ቀድሞ ነው የመጣው፡፡ በየቡድኖቹ ካሉ ምርጦች ተለይተን አዲስ አበባ ከመጣን በኋላ ኢትዮጵያ ሆቴል አርፈን ለአንድ ወር ያህል በልምምድ ቆየን፡፡ ከእኛ ቀደም ብሎ ሁለትና ሶስት ወር ሲሰለጥን ከሰነበተው የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን ጋር አጋጠሙን፡፡ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ከቶጎ ጋር በ10:00 ከመጫወቱ በፊት በ8:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ እኛ አሸነፍን፡፡ ሙሉጌታ ከበደ ሃትሪክ ሰርቶ ድል አደረግን፡፡ ይህ የሆነው እንግዲህ በ2974 ነው፤ ከዚያ በፊትም በ1973 እንዲሁ “ልምድ የላችሁም፡፡” ብለው መልሰውናል፡፡ ድጋሚም በዚሁ በልምድ ምክንያት ከምርጫ ውጪ አደረጉን፤ ከእኛ ውስጥ አንድም የተመረጠ ተጫዋች አልነበረም፡፡ የስታዲየም አዳራሽ ውስጥ ሆነን የሚሉንን እየተጠባበቅን ሳለ “ወደ ቤታችሁ ተመለሱ!” ስንባል እኔ እጄን አወጣሁና ‘ጋሼ ለምንድነው እኛ ያልተመረጥነው?’ ብዬ አሰልጣኙን ጠየቅሁ፡፡

አሰልጣኙ ማን ነበሩ?

★ ስሙን እንኳ አልናገርም፤ መውቀስ ይሆንብኛል፡፡ በዚያ ላይ በጣም የምወደው ሰው ስለሆነ ስሙን አልናገርም፤ ስለዚህ አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ “ልምድ የላችሁም!” ማለት ምን ማለት ነው? ‘ልምድ የሚገኘው ከእናት ሆድ ነው እንዴ!’ብዬ ተናገርኩ፡፡ ተሰድቤ ተባረርኩና ወደ ደብረ ማርቆስ መምህርነቴ ተመለስኩ፡፡ ያኔ ገና የ19 ዓመት ወጣት፣ የሁለተኛ ደረጃ መምህር፣ የኳስ ፍቅር የተጸናወተኝ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ በኮተቤ ኮሌጅ የሁለት ዓመት ቆይታዬ ጂኦግራፊን ባጠናም ስለ ስፖርት ሳይንስ ከጓደኞቼ ብዙ እውቀት አካብቻለሁ፤ አንዳንዴ ፕሮፌሰር ሲሳይ ሲያስተምሩ የእርሳቸውን ትምህርት ለመከታተል ስል ክፍላቸው እገባ ነበር፡፡ ከጂኦግራፊ የትምህርት ክፍል ወደ ስፖርት ሳይንስ እንድቀይር ሁሉ ምክር ተሰጥቶኝ እኔ ‘አልፈልግም፡፡’ ብዬ ተውኩት፡፡ በእርግጥም በአሰልጣኞቹ ዘንድ እንደዚያ አይነት አመለካከት ይታይ ነበር፡፡ በወቅቱ በአዲስአበባ፣ አስመራና ድሬደዋ ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጓል፡፡ በእነዚህ ክፍላተ ሃገራት የውድድሩ ግለት ከፍተኛ ነበር፡፡ ትልልቆቹ ክለቦችም እዚያ ይገኙ ስለነበር በእኔ ስሜትና አረዳድ ላይ ተመስርቼ ቅሬታዬ ገለጽኩ፡፡ ድሮ ከእኛ በፊት ከመቐለ ወደ ድሬደዋ የሄዱ ብዙ ተጫዋቾች ነበሩ-እነ አስመላሽና ዳዶን የመሳሰሉት፡፡

አስመላሽ በርሔ 1970ዎቹ መጨረሻ ቡና ገበያን ያሰለጠነው ነው

★ እሱ አየር መንገድ የነበረው አስመላሽ ተስፋዬ ነው፡፡ በጉናም ምክትሌ ሆኖ ለአንድ ዓመት ያህል አብረን ሰርተናል፡፡ ይህኛው አስመላሽ በርሔ መቐለ ተጫውቷል፤ ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይም የብሄራዊ ቡድናችን ተሰላፊ ነበር፡፡ ያን ጊዜ በርካታ ተጫዋቾች ከመቐለ ወደ ኤርትራ ክለቦችም ተጉዘዋል፤ እነ ሃጂ ወደ እምባይሶራ ሄደዋል፣ አህመድ አብደላም እዚያ ተጫውቷል፣ ሃይላት (ግብ ጠባቂ) እዚህ መጥቶ ለመቻል ተሰልፏል፤ ከጅማም መጥተው ምርጫ ውስጥ የተካተቱ ልጆች ነበሩ- ከወለጋም አንድ አስገራሚ ብቃት የነበረው ተጫዋች ነበር-ጎላ ብርሃኔ! ከዚያ ክፍለሃገር ነጎድጓድ የሚባል ጥሩ ቡድንም ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ ስሜትህ ሁኔታዎች እንዲዚያ እንዲመስሉህ ያደርጋል፤ እኔም ጋር ያ ስሜት ቀርቶ ቅር ተሰኝቼ ያን ጥያቄ አቀረብኩ፤ በዚያ ቁጭት የተናገርኩት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ገብረመድህን መጣ- ታዋቂ ሆነ፤ ሙሉጌታም መጣ-ገናና ሆነ፡፡ የክፍለ-ሃገር ልጆች በደንብ ቦታ ያገኙ ጀመር፡፡

ያቺ የቁጭት ጥያቄህ በሒደት ለውጥ አመጣች ማለት ነው፡፡ 

★ ትክክል! የሚገርማችሁ በ1975 ከአንድ መምህር ወዳጃችን ጋር ሆነን ሄድንና ለአንድ አሰልጣኝ ” እሺ እኔን ተወኝ-ይቅር፤ገብረመድህንን ግን ውሰደው፡፡” አልነው፡፡ “ቀጫጫ’ኮ ነው፤ ምን ይጠቅመኛል?” ብሎ መለሰልን፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገብሬን ወሰደው፡፡ እንግዲህ የገብረመድህንን ያህል ብቃት ማየት አይችሉም ነበር-ከአዲስ አበባ ውጪ፡፡ አትፈርድባቸውም፤ ሰዎች ናቸው-ይሳሳታሉ፤ እኔም ይህን የምናገረው ለመውቀስ ብዬ አይደለም፡፡

በተደጋጋሚ ጋሽ ታዴን (አሰልጣኝ ታደሰ ገብረ መድህን) ስታመሰግን ትስተዋላለህ፤ በመጻፍህም ላይ አበርክቷቸውን አንስተሃል፡፡ እስቲ እዚህም እናንሳቸው

★ ጋሽ ታዴ ብዙ የሚያነሳው ሰው የለም እንጂ እጅግ ትልቅ ሰው ነበር፡፡

አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ስለ ልፋታቸውና ውለታቸው ብዙ ይል ነበር፡፡

★ በጭማድ (ጭነት ማመላለሻ ድርጅት) የተጫወቱ ተጫዋቾች ስለ ጋሽ ታዴ ብዙ ማለት ነበረባቸው፡፡ በብዛት እኮ የእሱ ልጆች ነበሩ፡፡ በደርግ ጊዜ ለወጣቶች ተብሎ የተዘጋጀ የክረምት የሁለት ወራት ኮርስ ይሰጥ ነበር፡፡ እኔ ወደ ለገሃር ስሄድ አየዋለሁ፤ ስታዲየም አካባቢ አሁን አውቶቡስ ማቆሚያ የሆነው ቦታና C-ሜዳ ላይ በየቀኑ ወጣቶችን ያሰለጥን ነበር፡፡  በተለይም በክረምት ወቅት ሜዳው ሲጨቀይ አሰፋልቱ ላይ ዘወትር ሲያሰለጥኑ እየተመለከትሁ ጋሽ ታዴን መቅረብ ጀመርኩ፡፡ ኋላ ላይ ጥሩ ጓደኛሞች ሆንን፤ አንድ ኮርስም እኔ፣ ገብሬና እርሱ ሆነን ወሰድን፡፡ ጋሽ ታዴ ምንም ሳይከፈለው ለኢትዮጵያ እግርኳስ የበኩሉን ለማበርከት ለፍቷል፡፡ ወደ መጨረሻ ላይ ፌዴሬሽኑ በቋሚነት ባይሆንም እንደ ሰራተኛ ቀጥሮት መጠነኛ ክፍያ ይፈጽምለት የጀመረ ይመሥለኛል፡፡ ያፈራቸውን ልጆች ስናይ ግን በሃገሪቱ እግርኳስ ደረጃ ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ እንዲያውም “የጋሽ ታዴ ልጆች” ይባሉ ነበር፡፡ ብዙ ልጆችን ለወግ-ማዕረግ አብቅተዋል፡፡ ጋሽ ታዴ ልፋቱ ያልከፈለው፣ ጥረቱ ያልታየለት፣ የእጁን ያላገኘ ትልቅ ባለውለታ ነበር፡፡ አንድም ቀን በአግባቡ ሲታወስ ሰምቼ አላውቅም፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከሌሎቹ ትልልቅ አሰልጣኞች ባልተናነሰ ለጋሽ ታዴም እውቅና መስጠት አለበት፡፡ ያው እግርኳሳችን ባለውለታዎችን ዞር ብሎ የማየት ችግር አለበት፤ ታዴ የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑት ሙያተኞች መካከል አንዱ ነው፡፡

ጋሽ ታዴ በክለብ ደረጃ አላሰለጠኑም

★ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ድሮ እኔ ከመቐለ ከመምጣቴ በፊት ያሰለጠነ ይመስለኛል፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ምናልባት ጭማድን አሰልጥኖ ሊሆን ይችላል፡፡

በሃገራችን እግርኳስ ተጫዋቾቻችን መደበኛ ባልሆነ ሥልጠና ያደጉ ናቸው፡፡ በየሰፈሩ እነዚህን ተጫዋቾች ኮትኩተው ላሳደጉት አሰልጣኞች የሚቸረው ትኩረትም እጅግ አናሳ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ከክለብ አሰልጣኞችና በዙሪያቸው ካሉት ውጪ በየሰፈሩ የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ቁጥር እየተመናመነ ይገኛል፡፡ የእነዚህ ሰዎች አስተዋጽኦ ከግምት ያልገባው ለምንድን ነው?

★ ይህማ እግርኳሳችንን የምንመራበት ደካማ አካሄድ ውጤት ነው፡፡ ክለቦቻችንም “እነዚህ ልጆች ከየት መጡ? ማን አሳደጋቸው?” አይጠይቁም፡፡አስታውሳለሁ- ልጅ እያለን እምባይሶራ ክለብ ከመቐለ ሃጂን ወሰደና ልጁ ይጫወትበት ለነበረው የከተማው ቡድን ሙሉ ትጥቅ ሰጠ፡፡ አሁን ያ አሳዳጊ ክለብን አልያም ግለሰብን የመደገፍ ባህል የለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ተጫዋች ከሐዋሳ ብናመጣ ይህን ተጫዋች እዚህ ላደረሰው አካል ተገቢ ክፍያ መፈጸም አለብን፡፡ እስቲ የሳሙኤል ኤቶን ጉዳይ እናንሳ፦ ተጫዋቹ የተነሳው ከያውንዴ አካዳሚ ነው፡፡ ይህ ማሰልጠኛ ማዕከል ተጫዋቹ ወደ አውሮፓ ሲሻገር የሚገባው ጥቅም በመቶኛ ተሰልቶ ተሰጥቶታል፡፡ እኛ ጋር ደግሞ ጭራሹኑ እውቅና እንኳ አንሰጥም፡፡ ስለዚህ መደበኛ ባልሆነ ሁኔታ በየሰፈሩ ባሉ ሜዳዎች ተጫዋቾችን እያሰለጠኑ፣ ልጆቹን ለትልቅ ደረጃ ለማብቃት እየለፉና በምላሹ ምንም ሳያገኙ ሲቀሩ ሙያውን ይተዉታል፡፡ ይህ ሒደት እግርኳሳችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷልና መቅረት አለበት፡፡

አንድ ተጫዋች የብቃቱ ጫፍ ላይ ሲገኝ መጀመሪያ “ማን ነው ይህን ልጅ ያሳደገው?” ብለን በመጠየቅ አሳዳጊዎችን ማበረታታት እንልመድ፡፡ አስኮ አካባቢ በጣም ጎበዝ አሰልጣኝ አለ፤ በቴሌቪዥን ቀርቦ ሲናገርም ተመልክቼዋለሁ፤ ብዙ ተጫዋቾችን አፍርቷል፤ ነገርግን እውቅና የሰጠው አካል አልተገኘም፡፡ የእግርኳስ አመራሮቻችን ይህን ችግር መቅረፍ መቻል አለባቸው፡፡ እንዲህ ያለምንም ድጋፍ ጠንክረው የሚታትሩትን በማበረታታት ሰዎቹ የሚጎድላቸውን ለማሟላት መሥራት ግድ ነው፡፡ ዘንድሮ አቶ ኢሳይያስ ጅራ መቐለ የመጡ ጊዜ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ “የ<አብርሃም እግርኳስ አካዳሚ>ን ላስጎብኛችሁ…” ብሎ እኔ በሌለሁበት ይዟቸው ሄደ፡፡ አቶ ኢሳያስም “…..ስለለፋህ፣ ይህን ጥረት ስለምታደርግም፣ስለ እግርኳሱ ስለምታስብ፣…” ብለው ለአካዳሚው አስራ አምስት ኳሶች አበረከቱ፡፡ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቁጥሩ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ እውቅናው ግን ብዙ ነው፡፡ እዚያ ድረስ መጥተው አካዳሚዬን ስለጎበኙ ፕሬዘዳንቱን በጣም ነው ያደነቅኋቸው፡፡ ማንም ሰው ያንን አላደረገም፤ አይደለም የሃገሪቱ ፌዴሬሽ አመራር መቐለየ ያሉት ክለብ ኃላፊዎች እንኳ መጥተው አላዩንም፡፡ ይህን እርምጃ ማድነቅ አለብን፡፡ አቶ ኢሳያስ የእኔን ብቻ ሳይሆን የሌሎች አሰልጣኞች አካዳሚንም ጎብኝተዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ በቅርቡ ወደ ሐዋሳ ተጉዘው የአሰልጣኝ ከማል አህመድን አካዳሚዎችንም ቃኝተዋል፡፡

★ አዎን! የጋሽ ሰውነት ቢሻውንም ማሰልጠኛ ማዕከል አይተዋል፡፡ አቶ ኢሳያስ ይህን የሚያደርጉት ከውስጣቸው በመነጨ ፍላጎት ነው፡፡ ሌሎቹም ይህን ተግባር መከወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የላይኛው እግርኳስ መሰረት ወደ ሆነው ታችኛው እንቅስቃሴ ወረድ በማለት እዚያ ላይ የሚሰሩትን ማነቃቃት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ፕሬዘዳንቱ ጥሩ እየሰሩ ነው፤ ፌዴሬሽኑ ግን እንደ ተቋም በጥልቀት ማሰብ አለበት፡፡

በስም መመሳሰል የአሰልጣኞቹ ማንነት እንዳይምታታብን ይህንንም ግልጽ ብታደርግልን፦ 1960ዎቹ መጀመሪያ አየር መንገድ ቡድንን የመሩት አቶ ታደሰ ወልደአረጋይስ ምን አይነት አሰልጣኝ ነበሩ

★ ኦ! እሱ ከእነ መንግስቱ ወርቁ ጋር የሰራ አንጋፋና ትልቅ አሰልጣኝ ነው፡፡ ታደሰ ወልደአረጋይ እነ ገብረመድህን ኃይሌ የተሰባሰቡበትን ምርጡን ወጣት ቡድን አሰልጥኗል፡፡ በእርግጥ እኔን አላሰለጠነኝም፤ አላስተማረኝም፡፡ ከጓደኞቼ ስለእርሱ የምሰማው ግን እጅግ በጣም በራሱ የሚተማመን ጠንካራ አሰልጣኝ እንደነበረ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በጣም አድናቂው ነኝ፡፡

1996 መጨረሻ አሰልጣኞች የትምህርት ዝግጅታቸውንና የሥራ ልምዳቸውን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ኮሚቴ እያቀረቡ ደረጃ ይሰጣቸው ነበር፡፡ አላማው ምንድን ነበር? በውሳኔውስ ታምንበታለህ?

★ አዎ! በደንብ አምንበታለሁ፤ የአሰልጣኞችን ደረጃ ማውጣት ግድ ነው፡፡ ባለሙያዎች ደረጃችንን ማወቅ ነበረብን፤ አለበለዚያ ሁሉም አዋቂ ነው የሚሆነው፡፡ አሁንም ነገሮች የተቀላቀሉበት ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ የሥልጠና ብቃት፣ የትምህርት ዝግጅት፣ ልምድና የመሳሰሉት በመስፈርትነት ተይዘው ደረጃ መሰጠቱ አግባብ ነው፡፡

በሰለጠነው ዓለም ዘመናዊ እግርኳስ ላይ ይህ አይነቱ አሰራር አለ? 

★ ይኖራል! የግዴታ ይኖራል፡፡

እዚያ ደረጃ ሰጪው አካል ማን ነው?

★ የ<Licensing System> ያላቸው አህጉራዊ ኮንፌዴሬሽኖች ናቸው ደረጃ የሚሰጡት፡፡ ለምሳሌ በአፍሪካ ካፍ A-Licence,B-Licence,C-Licence እያለ ይሰጣል፡፡ እነዚህን የሥልጠና ፈቃዶች ሳያሟሉ ትልቅ ክለብና ብሄራዊ ቡድን ማሰልጠን አይቻልም፡፡ ካፍ ከፊፋ ወስዶ እየሰራበት ነው፡፡ በእርግጥ በ2010 ነው የተጀመረው፤ ያኔ ግብጽ ሄደን በካይሮ ሰልጥነናል፡፡ ከእኔ በፊት መንግስቱወርቁና ካሳሁን ተካ የካፍ ኢንስትራክተሮች ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ መንግስቱ የፊፋም ኢንስትራክተር ነበር፡፡ በ2010 ይህ የ<Licensing System> ሲጀመር ገብረመድህን እና እኔ ተመረጥን፤ ገብሬ በፋይናንስ ምክንያት ቀረ፤ እኔ ካይሮ ሄድኩ፡፡  ከዚያ በፊት በታንዛኒያም ስብሰባና ሥልጠና ተሰጥቶ ነበር፤ እሱን ሌሎች ባለሙያዎች ሄዱ፡፡ በካይሮው ስልጠና <Licencing> ከ<C> እንደሚጀመር ተረዳን፣ በፊፋ ህግ መሰረትም <Professional Licence> ሳይያዝ <Professional Club> ማሰልጠን እንደማይቻል አወቅን፡፡ ከዚህ አንጻር በ1997 የተወሰነው ውሳኔ ትክክል ነበር፡፡ ደረጃ አሰጣጡ እና የአመላመል ሥርዓቱ  ነው እንጂ ትክክል ያልሆነው ጅምሩ አግባብ ነበር፡፡

ይህ ደረጃ ሲወጣ ታዲያ አንተ የትኛው እርከን ተሰጠህ?

★ ያኔ ጉና ነበርኩ፤ ሁለተኛው ደረጃ ተሰጠኝ፡፡ በተለያዩ አምስት ቀለሞች የተቀለሙ የመለያ ደብተሮችም ነበሩ፡፡ በወቅቱ ብዙም የውጭ ሥልጠናዎች አልወሰድኩም ነበር፡፡ ደረጃው ከመውጣቱ በፊት ከጋሽ አስራት ኃይሌና ጋሽ ሃጎስ ደስታ ጋር ኡጋንዳ በሰር ቦቢ ቻርልተን የተሰጠውን ሥልጠና ውስጃለሁ፤ በአፍሪካ በጣም ታዋቂ የነበረው ጋናዊው የፊፋና ካፍ ኢንስትራክተር ጋምፊ የሰጠውን ኮርስም ከእነ ጋሽ ታዴ ጋር ተከታትያለሁ፤ ከእነዚያ በቀር የውጪ ሃገር ትምህርት ዕድል አልነበረኝም፡፡በጃን ሜዳ ደግሞ ዶ.ር ተስፋዬ ጥላሁን የሰጡትን የስድስት ወራት ኮርስ ምድር ባቡር እያለሁ ነው የተሳተፍኩት፡፡ እናም እነዚህ-እነዚህ ወረቀቶችና የሥልጠና ልምዴ ታይቶ ሁለተኛ ደረጃ ተሰጠኝ፡፡ ደረጃ ከሌለ እድገት አይኖርም፡፡ ስለዚህ የደረጃ ምደባ መኖር አለበት፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ ጥላሁን “… የኢትዮጵያ እግርኳስ ለምን እንደማይጠቀምባቸው አይገባኝም፡፡ብለህ በሁለተኛው መጽሃፍ ላይ የጠቀስኳቸው ባለሙያ ናቸው

★ አዎን! ዶ.ር <Professional Licence> ያለው፣ የ<UEFA>ን <A-Licence> ያገኘ ትልቅ የእግርኳስ ሰው ነው፡፡ ዶ.ር ተስፋዬ አሁን በቼክ ሪፐብሊክ ይኖራሉ፤ በቅርቡም ወደ ሃገሩ መጥቶ ሰሞኑን ነው ወደ አውሮፓ የተመለሰው፡፡

ያኔ ደረጃ በመውጣቱ በአሰልጣኞቹ ዘንድ ውዝግብ ተፈጥሯል፤ ውሳኔውም ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፤ ለምን?

★ አሰራሩ ከራስ ጥቅም አኳያ ስለታየ ነዋ! “ለኔ የሆነ ደረጃ ይሰጡኛል…ያ ከሆነ ደ’ሞ…ያሳጣኛል” የሚል የጥቅም ስሌት ላይ ስለተገባ ነው እንጂ ሌላ ምንም ምክንያት አልነበረውም፡፡ ለምሳሌ፦ አንዱ አሰልጣኝ ዝቅተኛ የትምህርት ዝግጅት ካለው በሥራ ልምዱ ከፍተኛ ማስረጃ ሊያቀርብ ይችላል፤ ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት ኖሮት ደግሞ ዝቅተኛ ልምድ ያለውም ሊኖር ይችላል፤ ይህን አመጣጥነን ደረጃ መሥጠት ነው-በቃ፡፡ በካፍ ህግ ለአንድ አሰልጣኝ <C-Licence> መያዝ ግዴታ ነው፡፡ ይህን ማግኘት የሚቻለው ደግሞ በፈተና ሆነ፤ ይህ ደግሞ በልምድ ረጅም ዓመት ያገለገሉትን አሰልጣኞች የማያሳልፍ ሊሆን ነው፡፡ ስለዚህ ለእነርሱ “የአምስት ቀን የማካካሻ ሥልጠና (Equivalent Course) እንዲወስዱ ይደረግና ያለፈተና ሰርተፍኬቱ ይሰጣቸዋል፡፡” ተባለ፡፡ ከዚያ ላይሰንሱ ሲመጣ የአሰልጣኞች ስብሰባ ተጠራ፡፡ “ውሳኔው እኛን ለመጣል ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፡፡” ብለው ትልልቅ አሰልጣኞች የላይሰንስ አሰጣጥ ሥርዓቱን ተቃወሙ፤ በሬዲዮ ነው የሰማሁት፡፡ እኔ ደግሞ ከካይሮ የ<Equivalent Course> መረጃው ከካፍ ቴክኒካል ዳይሬክተር ተደውሎ ተነግሮኛል፤ ቢጋብዙኝ ኖሮ ሄጄ አብራራላቸው ነበር፡፡

አንድ የ<Refreshment Course> ስሰጥ ከፊትለፊት ትልልቆቹ አሰልጣኞች ነበሩ፡፡ ‘ምን ማለታችሁ ነው? “ደረጃ አይውጣ!” ማለት’ኮ አንደግ ማለት ነው፡፡ ለእናንተ አንጋፎቹ ደግሞ በአዲሱ የካፍ አሰራር ይህኛው የ<Equivalent Course> ወጥቶላችኋል፡፡ ከሃያ ዓመታት በላይ ስላሰለጠናችሁ በዚህ ኮርስ ተሳትፎ ብቻ ላይሰንሱ ይሰጣችኋል፡፡’ ብዬ ነገርኳቸው፡፡ ባለ ልምድ አሰልጣኞች በፈተናና በትምህርት ዝግጅት ተብሎ ከ<Licensing System> ውጪ መሆን የለባቸውም፡፡ በዚያ በኬድ ኖሮ አንዱ አልፎ ሌላው ይወድቃል፡፡ ምክንያቱም በቂ የትምህርት ማስረጃ አልነበራቸውም፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም አላቀረቡም፡፡ በፊት-በፊትማ በአሰልጣኞች መካከልም መቧደን ታይቷል፡፡ ቀደም ሲል በተጫዋችነት አሳልፈውና ውጪ ተምረው የመጡት አሰልጣኞች እንዲሁም እዚሁ ቆይተው በሙያቸው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱት አሰልጣኞች መካከል ከፍተኛ ቁርሾ እንዳለ እንሰማ ነበር፡፡ እኔ ለሁለቱም ወገኖች ጥሩ ቅርበት ስለነበረኝ የምሰማቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ እዚህ የነበሩት ” እነዚህ ከት/ቤት የመጡ…”ብለው ይንቋቸዋል፤ እነዚያም ” እነዚህ… ይህን እግርኳስ ገደሉት፡፡” እየተባባሉ እንደማይስማሙ አውቅ ነበር፡፡

ደረጃ የመስጠት አሰራሩ አሁን ቀርቷል አይደል?

★ አዎ! ቀርቷል! <Licence> ስላለ ደረጃው ቀርቷል፡፡

እግርኳሳችን እና የኋሊት ርምጃውየተሰኘው መጽሃፍህ ላይ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመሆን በሚደረገው ሒደት እስከ መደለል የሚደርሱ አሰልጣኞች እንዳሉ ጠቅሰሃል፡፡ እውነት ሥራውን ፈልገው ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ አሰልጣኞች አሉ?

★ ሞልተው! የየራሳቸውን ቡድን ይዘው ቦታውን ለመቆጣጠር ይሞክራሉ፡፡ ብሄራዊ ቡድንን ማሰልጠን እንደ ሹመትና ሽልማት የምናየው ሰዎች አለን፡፡ ነገርግን እጅግ ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን የተረዳሁት እኔም ካየሁት በኋላ ነው፡፡ ‘ለዚያ ቦታ ብቁ ነበርኩ? አልነበርኩም?’ ብዬ ሁሉ ማሰብ ጀምሬ አውቃለሁ፡፡ብሄራዊ ቡድን ማሰልጠን እንደ አንድ <Achievement> ሊታሰብ ይችል ይሆናል፡፡ ሰዎችን በመደለል ይዘህና ተሽሎክሉከህ ሲሆን ግን ጥፋት ነው፡፡ መስመሮች እየገጣጠምክ በ<ኔትወርክ> መግባት ስኬት ሳይሆን ውድቀት ነው፡፡ በዚያ ላይ ስራው ከባድ በመሆኑ ሳይታመንብህ ሲቀር ተባረህ ነው የምትወጣው፡፡  ደፋሮች ግን ተሽሎክሉከው እዚያ ደረጃ መገኘትን ይፈልጋሉ፡፡ ቴክኒክ ኮሚቴ ሆኜ የሞከሩ ሰዎችን አውቃለሁ፤ ተቃውሞ አቅርቤ ከወጣሁባቸው ምክንያቶች መካከለም አንዱ ይኸው ጉዳይ ነበር፡፡ በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ሆነን ስንመረጥ ሃገራችንን በሙያችን ልናገለግል እንጂ አንድ ሰው መጥቶ ያለሙያው ” እንዲህ ሥራ፤ ይህን አድርግ!”ሊልህ አይደለም፡፡ በወቅቱ የፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ “እገሌን ልንመርጥ ስለሆነ እዚህ ላይ ፈርም!” ሲሉኝ ስብሰባ ላይ “እምቢ!” አልኩና ራሴን ከቦታው አገለልኩ፡፡ አንዳንዶቹ በዚያ ውሳኔዬ እስካሁንም እንደ ጠላት ያዩኛል፡፡ በጊዜው ሁሉም የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት “ከአንተ ጋር ሆነን እኛም ራሳችንን ከስራ እናገላለን፡፡” ብለው ነበር፡፡ ‘እናንተ ቆዩ፤ አድማ ይመስላል፡፡’ ብዬ ወጣሁ፡፡ አሁን-አሁን ክለብም እኮ በድለላ እየተገባ ነው፡፡

አሁን ደግሞ ከቀደምት አሰልጣኞቻችን መካከል አንዳንዶቹን እያነሳን እንጨዋወት፡፡ እስቲ ስለ አንጋፋው ሐጎስ ደስታ አውጋን

★ ጋሽ ሐጎስ ደስታ የአየር ኃይል ቴክኒሻን ነበር፡፡ ማስተር ቴክኒሻን የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ በርቀትም ቢሆን እርሱን የማውቀው ገና አየር ኃይልን እያሰለጠነ ሳለ ነበር፡፡ በደምብ መግባባት የጀመርነው እኔ ጉናን ማስልጠን ጀምሬ ከብሄራዊ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ካለፍን በኋላ ነው፡፡ ያን ጊዜ ብዙ ልምድ አልነበረንም፤ ስለዚህ በ1987 እና 1988 አካባቢ የየካቲት በዓላት ሲከበሩ ከአስመራ ጠንካራ ክለቦችን እየጋበዝን እንጫወት ነበር፡፡ ከደሴና ኮምቦልቻም እንዲሁ ግጥሚያዎች አድርገናል፡፡ ይሁን እንጂ ከመቐለ ውጪ ካሉ ትልልቅ ክለቦች ጋር የመፋለም ልምድ አላደበርንም፡፡በትግራይ ክልል ሻምፒዮና እንኳ ገብረመድህን የነበረበትና በፊት የመቐለ ምክር ቤት ከዚያ ደግሞ ትራንስ የተባለው ቡድን እና እኛ እያደግን ሄድን፤ በእርግጥ የትግራዩ መብራት ኃይልም ነበር፤ ኋላ ግን ፈረሰ፡፡ ከእነዚህ ክለቦች በላይ ሌሎች ፈታኝ ቡድኖችን አናውቅም፡፡ ፕሪሚየር ሊጉን ስንቀላቀል ደግሞ ከአስመራ አልታሃሬ የሚባል ቡድን ጠርተን በስቅለት ቀን አሸነፍን፤ ሁልጊዜ የሚያሸንፉን እነርሱ ነበሩ፡፡ ስናሸንፋቸው ግን ጥሪ አቀረቡልን፡፡

ከዚያም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በ1990 ግንቦት ሊጀመር እኛ በመስከረም ወር ኤርትራ ሄደን ተጫወትን፡፡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ እኛ አዲስ አበባ፥ ትራንስ ደግሞ ድሬዳዋ ተመደብን፡፡ ቀጥለን በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ መጣን፤ ክለባችን በከፍተኛ መነሳሳት ላይ ይገኝ ነበር- ዳንኤል ጸሃዬ፣ የማነ፣ ተካ፣ እስጢፋኖስ፣….. ሌሎችም ጥሩ ጥሩ ልጆች የታዩበት ጊዜም ሆነ፡፡ እንደመጣን ሙገርን 4-2 ረታን፤ በሌሎች ጨዋታዎችም ድል አድርገን ወደ ስምንቱ የፕሪምየር ሊግ ቡድኖች ተቀላቀልን፡፡ በወቅቱ የካሳሁን ተካ መድንና የሐጎስ ደስታ መብራት ሃይል ትልልቅ ቡድኖች ነበሩ፡፡ የልምምድ ሜዳ ስናፈላልግ ጋሽ ሐጎስን ጠየቅነው፤ በፍጥነት “የመለማመጃ ሜዳ ፍቀዱላቸው፡፡” አለ፡፡ በነጻ ፈቀዱልን፤ እዚያ መሥራት ጀመርን፡፡ የመጀመሪያ የወዳጅነት ግጥሚያ ስናደርግ የያኔውን ኤሌክትሪክ ማንም አይገዳደረውም፤ አለቆቼን “ከመብራት ሃይሎች ጋር ልንጫወት ነው፡፡” ብዬ ጠርቼ እነርሱም ከመቐለ ድረስ መጥተው ጨዋታውን ታድመዋል፤ የጋሽ ሐጎስ ቡድን እኛን 7-1 ቀጠቀጠን፡፡

እንግዲህ ከመብራት ኃይል ጋር በአንድ ሊግ ልንወዳደር ነው፡፡ ” ታዲያ በፕሪሚየር ሊጉ እንዴት ልንችላቸው ነው?” አልን፡፡ የሚገርመው ልጆቻችን በሰፊ የግብ ልዩነት ተሸንፈውም ከፍተኛ የመነሳሳት ስሜት ላይ ነበሩ፡፡ “በምን በለጡን?” ውይይት ጀመርን፤ ተጫዋቾቼ ስለ መብራት ሃይል ተጫዋቾች ሲመሰክሩ ” እጅግ በጣም ይሮጣሉ፤ አይቆሙም፤ ልንይዛቸውም አልተቻለንም፡፡” አሉኝ፡፡ እውነታቸውን ነበር፡፡ ያኔ አንዋር ያሲን፣ ኤልያስ ጁሃርና ሌሎቹን የቡድኑ ተጫዋቾች መቆጣጠር ከባድ ነበር፡፡ “እንዴት እንደእነርሱ መሆን ያቅተናል?” ብለን በሳምንቱ ድጋሚ እንድንጋጠም ጠየቅናቸው፤ ተስማሙ፤ ተጫወትን፤ 1-1 አቻ ተለያየን፡፡ ጨዋታው ሲያልቅ ልጆቼ ተዘረሩ፡፡ የተጋጣሚያቸውን Intensity ለመቋቋም ባደረጉት ጥረት ዝለዋላ! ግን በቡድናችን ተስፋ ኖረን፡፡ አዕምሮ ከተቀየረ’ኮ ሌላው ቀላል ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ግን በጋሽ ሐጎስ ጥረት የተሳካ ነው፡፡ ከታጋዮች የወረስነው ጥሩ የግምገማ ባህል ነበረን-አለቆቻችን ያስተላለፉልን ነው፡፡  ቁጭ ብለን እንገማገማለን፤ በዚህ ጊዜ ተጫዋቾች አሰልጣኞቻቸውንም አይምሩም፡፡ ይህ ልማድ በመካከላችን ጥሩ መስተጋብር ፈጥሯል፡፡  ኋላ ግን ብዙ ልጆች ከሌሎች ክለቦች እየተቀላቀሉን ሲመጡ ያ የግምገማ ባህላችን ደፈረሰ፡፡ በሆቴል ውስጥ አንድ ላይ የመቆየት ሥርዓታችንም ጥብቅ ነበር፡፡ ጋሽ ሐጎስ ለእኔ ጥሩ መምህሬ ሆነ፤ በቅርብ ስለማገኘውም እያንዳንዱ ልምምዳችንን እንዲያይ እጠይቀዋለሁ፡፡ ጋሽ ሐጎስ ሰፊ እውቀት ነበረው፡፡ እያሸነፍከውም ቢሆን ያስተምርሃል፤ ስህተትህን በግልጽ ይነግርሃል፤ ድል አድርገኸውም እንኳ መጥቶ-አቅፎ ይስምሃል፤ እንደ ሌላው ፊቱን አጥቁሮ አይሄድም፡፡ በአጠቃላይ ሐጎስ <Professional Coach> ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ከአለቆቼ ጋር ተጣልቼ ሳለሁ ሄዱና ለሃጎስ ” አሰልጣኝ ልንቀይር አስበናል፡፡” አሉት፡፡ “አይ! ከአብርሃም በላይ ማንንም አታገኙም፡፡” ብሎ መለሰላቸው፡፡ ኃላፊዎቹ ራሳቸው ነው የነገሩኝ፤ ሃጎስ ያላቸውን አጫወቱኝ፡፡ ‘ልታባርሩኝ ነበር እንዴ?’ብዬ ስጠይቃቸው “አስቸገርከና ታዲያ!” የሚል ምላሽ ሰጡኝ፡፡ በእርግጥም ኃይለኛ ነበርኩ፤ ትዕዛዝ አልቀበልም፤ በራሴ መንገድ ብቻ እጓዛለሁ፤ እናም አሁኔ ላይ ሆኜ ሳስበው አስቸጋሪ እንደነበርኩ ይገባኛል፡፡ እርሱ ግን ይህን ያህል እኔ ላይ እምነት አሳድሮ ከመባረር ታደገኝ፡፡ ጋሽ ሐጎስ ደስታ እጅግ ቅን ሰው ነበር፡፡ ሃገሪቱ ሳትጠቀምበት አለፈብን፡፡ ደብሮምን ሳገኘውም ‘እባክህ! ሐጎስን መሥለህ ውጣ!’ እለዋለሁ፡፡ ደብሮም ቡና ከመግባቱ በፊት በጉና ነው ይበልጥ ታዋቂ የሆነው፡፡ ከኒያላ ወደ ጉና ተዘዋውሮ መቐለ ላይ ቡናን ስናሸንፍ ደብሮም አስገራሚ ብቃት አሳየ፤ ትዝ እንደሚለኝ ስዩም አባተ ያነጋገረው ያኔ ነው-ከዚያ ቡና መጣ፡፡

ከመኩሪያ አሸብር ጋር የነበረህስ ግንኙነት

★ (አሰልጣኝ አብርሀም መኩሪያ አሸብርን የሚጠራው <መኩሪ> እያለ ነው፡፡) መኩሪ በጣም ወዳጄ ነበር፡፡ እጅግ ጥሩ ሰው ነው፡፡ በአንድ ድርጅት ውስጥ ሰርተናል-ምድር ባቡር- እሱ ድሬዳዋ፥ እኔ አዲስ አበባ፡፡ ከባለቤቱ፣ ልጆቹና መላ ቤተሰቡ ጋር ቤተሰብ ሆነናል፡፡ ድሬዳዋ ስሄድ የሚቀበለኝ እርሱ ሲሆን በአዲስ አበባው ምድር ቢሮ አለቃዬ የነበረው አቶ አባይነህ ደግሞ ከመኩሪ ጋር ቤተሰብ ናቸው፡፡ በእነርሱ አማካኝነት ተቀራረብን፤ እግርኳሱ ደግሞ የበለጠ ወዳጅነታችንን አጠናከረው፡፡ የተለያዩ ኮርሶችን አንድ ላይ ወስደናል፤ እንዲያውም ጋሽ ታዴም አብሮን ነበር፡፡ መኩሪ ሲበዛ የዋህና ደግ ስብዕና ነበረው፡፡ ጠንካራ አሰልጣኝም ነበር፡፡ ከምስራቅ ኢትዮጵያ በተለይም ድሬዳዋና ሐረር አካባቢ የወጡ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች የእርሱ ፍሬ ናቸው፡፡ ከስሩም እነ አሰልጣኝ ግርማ ጥንቅሼ እና ገዛኢ <B-ቡድኑ>ን በማሰልጠን ያግዙታል፡፡ በክለቡ በርካታ ተጫዋቾችን አውጥቷል፤ በምድር ባቡር ቴክኒክ ክፍል ውስጥ የሚሰራ የኤሌክትሪክ ባለሙያም ነበር መኩሪያ አሸብር፡፡ መጀመሪያ በምስራቅ ጀርመን ቀጥሎም በምዕራብ ጀርመን ሄዶም እግርኳስ ተምሯል፡፡ መኩሪ የእነ ሰውነት ቢሻው <Batch> ነው፤ እኔ ትንሽ ከእነርሱ ዝቅ እላለሁ፡፡ እንዲያውም መኩሪያና ሰውነት እንደ ካሳሁን ተካ በሁለቱም ጀርመኖች ተምረዋል፡፡ ሁለቱ በደንብ የሚታወሱት መኩሪያ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ሰውነት ደግሞ በምክትልነት እየሰሩ በ1987 የአፍሪካ ዋንጫ በተሳተፈው ከሃያ ዓመት በታች ወጣት ቡድን ነው፡፡

ገዛኸኝ ማንያዘዋልስ?

★ ገዘኸኝን እርሻ ሰብል እያለ በሩቁ ነው የማውቀው፤ በ1980ዎቹ መጨረሻ በመድንም በጣም አስገራሚ ቡድን ነበረው፡፡ እነ አብርሃም ብስራትና አሰፋ ሲማን ያካተተው ቡድን የገዛኸኝ ነበር፡፡ ብዙ ቅርበት ግን አልነበረኝም፡፡


ክፍል አራትን ለማግኘት ይህን ይጫኑ :point_right: ክፍል 4