ካሜሩን 2021 | ለዓለም ብርሀኑ በጉዳት ከዋልያዎቹ ስብስብ ውጪ ሲሆን አቤል ማሞ በምትኩ ተጠርቷል

ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ከሰሞኑ ሀያ አምስት ተጫዋቾችን የጠሩት አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሀኑን በጉዳት በማጣታቸው በምትኩ የመከላከያው አቤል ማሞን ጠርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኅዳር 6 ከማዳጋስካር ከሜዳ ውጪ ኅዳር 9 ደግሞ አይቮሪኮስትን በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚገጥም ሲሆም በመቐለ ከሰኞ ጀምሮ ዝግጅት ማድረግም ይጀምራሉ። ከተጠሩት 25 ተጫዋቾች መካከል በወዳጅነት ጨዋታ እና በቻን ማጣሪያ የመጀመርያ ተሰላፊ የነበረው ለዓለም ብርሀኑ በቢሾፍቱ ከክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ልምምድ ላይ ሳለ ጉዳት ማስተናገዱ የተሰማ ሲሆን በዚህም ረዘም ላለ ጊዜም ከሜዳ ይርቃል ተብሏል።

በለዓለም ምትክ የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ መጠራቱን አሰልጣኝ አብረሀም መብራቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ ከግብ ጠባቂው አሰልጣኝ ውብሸት ደሳለኝ ጋር መከላከያ በወዳጅነት ጨዋታ ሰበታን 4-1 ገጥሞ ባሸነፈበት ወቅት በጋራ ተመልክተው ባሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ ተጫዋቹ መጠራቱንም ጨምረው ገልፀውልናል፡፡

ሰኞ ረፋድ ላይ ወደ መቐለ ለዝግጅት ካቀና በኃላ ልምምዱን ከሰዓት 10:00 የሚሰራው ቡድኑ ሽመልስ በቀለ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣቱ ወደ ቡድኑ የሚቀላቅል ሲሆን ጋቶች ፓኖም ሰኞ ከገባ በኃላ ወደ መቐለ ያመራል፡፡ ቢኒያም በላይ ግን ጨዋታው ሲቃረብ ቡድኑን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ